ከዓመት ከምናምን በፊት…
“አብሬያቸው ብሰራ” ከምላቸው፣ ጥሩ ስሜት ካሉኝ መሥሪያ ቤቶች መካከል በአንዱ የሥራ ማስታወቂያ መውጣቱን ጋዜጣ ላይ ተመልክቼ ለማመልከት አሰብኩና የትምህርት እና የሥራ ማስረጃዎቼን አደራጅቼ ሄድኩ። (መቼም አብዛኛው ቅጥር በፖለቲካ አቋም፣ በትውውቅና በዝምድና እንደሆነ ባላጣውም፥ በምናልባት ነበር ሙከራው።)
ከወጡት ሶስት የሥራ መደቦች እኔ ለማመልከት የፈለግኩት “managing director” ይል የነበረውን የሥራ መደብ ነበር። (ቀሪዎቹ ሁለቱ Data Encoder እና Secretary ነበሩ።) መስፈርቱን በበቂ ሁኔታ ስለማሟላ “ለቃለ መጠይቅ ፈተና ቢጠሩኝ እንኳን…” የሚል ጉጉት ነበረኝ።
ቢሮው ደረስኩኝና የሰው ሀብት አስተዳደሯን (መሰለችኝ) “ጤና ይስጥልኝ፣ የሥራ ማስታወቂያ አይቼ ለማመልከት ነበር።” አልኳት።
“Data encoder ነው?” አለችኝ። (ሶስተኛው መደብ ‘secretary’ ስለነበረ ሴቶችን ብቻ መጠበቋም አብሽቆኝ ነበር።)
“አይ ለማኔጂንግ ዳይሬክተር መደብ ነው።” አልኳት።
ገለማመጠችኝ አይገልጸውም።
“ማስታወቂያውን በደንብ አይተኸዋል? መስፈርቱ ብዙ ነው።” አለችኝ።
“አዎ! ስለማሟላ ነው የመጣሁት። ዶክመንቶቼን ይዣቸዋለሁ።” አልኳት።
“ማስተርስ ዲግሪ ነው የሚጠይቀው።” አለች።
“Sure, አለኝ” አልኩ።
“በአስተዳደር መደብ የሰራም ይላል…” አለች
“አዎ ሰርቻለሁ። እንደውም አሁን የምሰራውም በአስተዳደር መደብ ነው።”
አልተዋጠላትም። ዶክመንቶቼን እየተቀበለችኝ፣ “ብዙ ሰው አመልክቷል። ባትደክም ግን ጥሩ ነበር” ብላ አጉተመተመች። ማኅተሞቹን አፍጥጣ መመርመር ያዘች።
“ቆይ ግን ምን ዓይነት ሰው ጠብቀሽ ነበር?… ለማኔጂንግ ዳይሬክተርነት የሚያመለክተው ሰው እንዴት መሆን አለበት ብለሽ ነው?” አልኳት።
መልስም አልሰጠችኝም።
ተናድጄ ቀጠልኩ። “ሁኔታሽ ደስ አይልም። ብቀጠር እኮ ምናልባት አለቃሽ ነው የምሆነው።” አልኩ።
እርሷ እቴ ምንም አልመሰላት። (በልቧ “ኡኡቴ” ሳትልም አይቀር)
‘ስወጣ የቅርጫት ሲሳይ ታደርገዋለች።’ ብዬ ባስብም የተቀበለቻቸውን ዶክመንቶች ዝርዝር መመዝገቢያዋ ላይ መዘገበችኝ እና ፈረምኩ።
“ሳስበው ስራውን ብዙም አልፈልገውም። ለፈተና መጠራቴን ግን እፈልገዋለሁና ዶክመንቴ ቅጥር ኮሚቴው እጅ መድረስ አለመድረሱን እከታተላለሁ። ደህና ይዋሉ።” ብያት ሄድኩኝ።
* * *
ከወራት በፊት ደግሞ…
ለአንድ የአደራ መልእክት… የቤትና የቢሮ እቃዎች ሱቅ ሳይ፥ ተልኬ የነበረውን መግዛት የነበረብኝ እቃ ትዝ ብሎኝ ገባሁና ዞር ዞር ብዬ አይቼ፥
“ይሄ ስንት ነው?” አልኳት።
“ለቤት ነው የሚሆነው” አለችኝ።
በልቤ “ሆ” ብዬ… “አዎ እኔም ለቤት ነው የፈለግኩት።”
“ማለቴ ለመኖሪያ…”
“አዎ እኮ ለመኖሪያ። ቤት ያለውና የሌለው በድምጽ ይለያል እንዴ?” እንደጨዋታ ነበር ያሰብኩትና ያልኩት።
የተጋነነ ብር ነግራኝ… አያይዛ፥ “ግን ከዚህ ወረድ ብሎ አንድ ቤት አለ። ጠይቀሃል እዛ። ይረክስልሃል።” ብላኝ እርፍ።
* * *
በዚህ ሰሞን…
የሰው አገር ጠብ እርግፍ ሲታይ ደግሞ፥ የሚገዛውን እና የማይገዛውን፣ የሚመጥነውን እና የማይመጥነውን ሰው በዐይን አይተው የሚለዩት የአገሬ ልጆች በዐይኔ ዞሩ። የአገር እና የአገር ልጅ ነገር እንደው ባሰቡት ቁጥር ግርም ይላል፤ …ይኼ ይኼም እንደ ደህና ቁምነገር ይናፍቃል!
አልኩኝም… ወይ ጉድ!!!