‘የአስተማሪ ምግብ…’

ዩኒቨርስቲ አስተምር የነበረ ጊዜ…
 
ከእለታት ባንዱ ቀን ቡና ልጠጣ ወጥቼ ጠረጴዛ የተጋራኋቸው ሁለት ባልደረቦቼ ብስጭትጭት ብለው ሲያወሩ ሰማኋቸው።
 
“ምንድን ነው እሱ?” አልኩኝ ከመቀመጤ።
 
“እንዴት እንዴት እንደጠገቡ እኮ…” አለኝ አንዱ።
 
(በኋላ ግራ ቀኙን ስቃርም የገባኝ ሁሉም በየጠረጴዛው ያወራ የነበረው ይህንኑ ጉዳይ ነበር።)
 
“እነማን ናቸው ደግሞ?”
 
“ሌላ ማን ይሆናል? እነዚህ የተረገሙ ናቸዋ”ብሎ ተማሪዎች ወደሚራመዱበት አቅጣጫ አገጩን ቆለመመው።
 
“ተማሪዎቹ? …ምን ተባለ ደግሞ?” አልኩት እንዲህ መነጋገሪያ የሆነውን ጉዳይ ለመስማት አቆብቁቤ።
 
“እዚህ ላውንጅማ ድርሽ አይሏትም። እንደውም በዲሲፕሊን ኮሚቴ መከሰስ አለባቸው።” አለኝ።
 
“ጋይስ እኛም እኮ መምህራን ነን። እንስማውና አብረን እንቃጠል።” አልኩ።
 
“ምን ባክህ፥ ሁለት ሴቶች ከውስጥ እየወጡ፣ አንዲት ጓደኛቸውን… ‘ተመለሽ ተመለሽ፥ ምግብ አልቋል’ አሏት። ‘ምንም’ ስትል፥ ‘አይ ያለው ለአስተማሪ የሚሆን ብቻ ነው’ አሏት። እንዲሰማ ጮክ ብላ…” አለኝ።
 
አተራረካቸውና አበሰጫጨታቸው ዘና አድርጎኝ ስለነበር፥ “እንግዲህ ተማሪዎች ላውንጅ ሄዶ በልቶ፣ የተማሪን ምግብ የመግዛት አቅም አለን ማለት ነው። በፊት እንኳን፥ አንዱ ጋ ለትምህርት ሲኬድ የፈረደባት ካሪና ተገዝታ “እኔም ተምሬ መጣሁ” አስብላ ታስሸልል ነበር።” ብዬ እንደመሳቅ አልኩ። አልሳቁልኝም። ተናደዋል።
 
እንግዲህ “ለአስተማሪ የሚሆን ለተማሪ የማይሆን” (that teachers can’t afford, but students) የምግብ ዓይነት መኖሩ ነበር እንዲያ ያተከናቸው።
 
ቀን ተቆጥሮ ተማሪዎቹም ተከሰሱ አሉ።
 
“ሁለተኛ እንዳይለመዳችሁ” ተብለው በማስጠንቀቂያ ደብዳቤ ሳይቆነጠጡም አልቀሩም። ወዲያውም፥ የካፌው በራፍ ላይ “ለተማሪዎች አይፈቀድም” ዓይነት ትኩስ ማስታወቂያ ተለጥፎ ነበር።
 
ይኸው ባለፈው ወር የመምህራን ደመወዝ መጨመሩን ሰምተን
 
“እኛ ማስተማር ስናቆምማ የማይሻሻል ነገር የለም” የሚል ቅናት ባይሸነቁጠንም፥… 🙂
 
መንግስት የሆነ ያህል መቶ ብር “ጨመርኩ” ያለ ጊዜ፥ ከወሬው እኩል፥ የቤት አከራዮቻችን የጨመሩብን ብር ትዝ ብሎኛል። በዚያ ሰሞን ነጋዴዎች እንዴት እንዴት እንደሆኑም አይረሳኝም።
 
እና ጓዶች ጭማሪው ከወጪ ቀሪ እንዴት ነው?
 
ከተማሪ ጋር ያጋፋል?
 
የተማሪን የምግብ ምርጫ ያስቀምሳል?
 
የገቢ ግብር ማሻሻያ አዋጅም ከሀምሌ 1 ጀምሮ በሚገኝ ገቢ ላይ ተፈጻሚ እንዲሆን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባስቸኳይ በጠራው ስብሰባ ላይ አዋጅ አጽድቋል አሉ። ምን አስቸኮላቸው? 🙂
 
በነገራችን ላይ፥ ዜናው ላይ የተዘገበው ከቅጥር እና ከኪራይ ለሚገኙ ገቢዎች ነው። ከንግድ ስለሚገኙ ገቢዎች የተባለ ነገር የለም። የተጨማሪ እሴት ታክሱ እንደው ዞሮ ሸማቹ ላይ የሚጨመር ነውና በተዘዋዋሪ ተቀጣሪውን ነው የሚመለከተው። #Ethiopia
ሰላም!

ከመንግስት ደጋፊዎች ጋር ያለብኝ ችግር፥

ኢአዴግን ስለሚደግፉ ነው?
አይደለም!
 
በፖለቲካ ዝንባሌያቸው ወይም በገዢው ፓርቲ አባልነታቸው ነው?
አይደለም!
 
ይልቅስ፥
ደጋፊነታቸውን ተጠቅመው ግፍንና በደልን ማውገዝ ቀርቶ፥ እንዳልተፈጸመ ሁሉ ችላ ስለሚሉ ነው!
ሁሉን ነገር በዘረኝነት መነጽር ተመልክተው፥ “ወገኔን የነካ ይነካ” ስለሚሉ ነው!
በአባልነታቸውና የደጋፊነት ጠባያቸው የተነሳ ብቻ ጥቅማ ጥቅሞች ሲደረጉላቸው ተስገብግበው ሆዳቸው ውስጥ ስለሚከቱ ነው!
በፖለቲካ ተሳትፏቸው ተመዝነው በምሁራን ላይ ሳይቀር ህልቅና ሲሰጣቸው ትንሽም ሸምቀቅ ሳይሉ በአምባገነንነት ለመሰልጠን ስለማይፈሩ ነው!
መንግስትን ቅዱስ ስለሚያስመስሉ ነው!
የምንኖረውን የኑሮ ዓይነት አገላለጽ ሊያስተምሩን ስለሚፈልጉ ነው!
አገሪቱ ከእድገትና ልማት ውጭ ምንም ችግር አይወራባትም ስለሚሉ ነው!
የሀሳብ ጥልቀትንና የአነጋገር ብስለትን መጠንከር ስለሚፈሩ ነው!
ለማይረባ ጥቅም ብለው ወዳጆቻቸውን አሳልፈው ስለሚሰጡ ነው!
መንግስትን የቤተሰብ ጉባኤ ስለሚያምታቱትና ተቃዋሚዎችን ሁሉ ጠላት እና ፀረ ሰላም ስለሚያስመስሉ ነው!
ትግሬ ሁሉ ኢህአዴግ፣ ኢህአዴግም የትግሬ ብቻ (mind you, ሕወአት አላልኩም።) እንደሆነ ለማስመሰል ስለሚኳትኑ ነው!
አገሩም የመንግስትና የደጋፊዎቹ ብቻ እንደሆነ ስለሚያምኑና፣ በዛቻ፣ በማስፈራሪያ እና የተለያየ ዓይነት ጥቃት በመፈጸም ሊያሳምኑን ስለሚታገሉ ነው!
በገዛ አገራችን ላይ ሁሉን ነገር እኛ ብቻ እናውቅላችኋለን ስለሚሉ ነው!
ወዘተ!
—–
ሕዝብ እንደው “በቃን!” ካለ ሰንብቷል! ምናለ በከንቱ ከመውተርተርና ሕዝብ ከመፍጀት እነሱም ገገማነቱ እና በውሸት ቅንብር መባዘኑ ‪#‎በቃን‬ ብለው በሰላሙ ቢወያዩና ልባቸውን መልሰው ስህተቶቻቸውን ስለማረም ቢያስቡ? በዘውግ ፌደራሊዝም ስም የዘሩትን እያጨዱ ነው። አሁን “ጆሮ ዳባ ልበስ” ብለው ኖረው፥ በማለቅለቅ ላይ ያሉ ጥቅመኛ ኮካዎች እና ሹመኞች ሁሉ የሰብዓዊ መብት ታጋዮች ሆነው መጥተዋል። ግን ምስኪኑን ሕዝብ በግፍ ማጨዱን ቢያቆሙ ምናለ?
የዘረኝነት አስተሳሰብ ይውደም!
 
#Ethiopia 

የወዳጅን ሞት ሰምቼ ስባዝን…

ማኅበራዊ መዋቅራችን አጓጉል ነው። ከደስታ ይልቅ ኀዘንን ለማስታመም ይቀለናል። ከእልልታ ይልቅ ለከንፈር መጠጣ የሚያፈጥነን ይመስላል። በሰው ደስታ ከምንደሰተው ይልቅ፣ ሰዎችን ለተሻለ ፍላጎታቸው ከምንገፋቸው ይልቅ፣ በኀዘናቸው የምንማቅቀው ይበዛል፤ ከፍላጎታቸው ምንገፈትራቸው ይልቃል። በደግ ቀን፥ ስም ስንሰጣጥ፣ ስንፈራረጅ ነው የምንውለው። ደሞ ትንሽ ችግር ሲደቁሰን፥ “ወንድሜ እህቴ” ስንባባልና ስንረባረብ ለጉድ ነው የምናስቀናው።
 
ለምሳሌ፥ አይበለውና እግሬ ቢቆረጥ ሳር ቅጠሉ ያዝናል። ያየ የሰማም ከንፈር መምጠጡ አይቀርም። ደግሞ፥ ይበለውና ዘናጭ መኪና ብገዛ በጣም ጥቂቶች ናቸው የደስታዬ ተካፋይ የሚሆኑት።
 
ከማስታውሰው…
 
ሳልጠይቀው፣ አንድም ቀን… ‘ሞካሪ’ እና ‘የትርፍ ሰዓት ሞንጫሪ’ ነኝ እንጂ፥ አፌን ሞልቼ እንደ ማዕረግ (title) እንኳን ‘ጸሐፊ’ ነኝ የማልልበትን ጉዳይ አንስቶ ሲያንቆለጳጵሰኝ የኖረ ሰው፣ የሆነ ቀን… ከጀርባዬ በመጻፍ ባህርዬ የተነሳ፣ በክፉ በደግ ሲያነሳኝ ከርሞ፣ የሰማሁ ሲመስለው ደግሞ፥ ነገሩም ውኀ እንዲያነሳለት እኔን ማጣጣልና ማንቋሸሽ ተጨማሪ ሥራው ያደርገዋል።
 
“ይሄን ያህል ምን አጠፋሁና ነው? እርሱ ቦታ አልሄድኩ። ሀሳቡን ካፉ ነጥቄው አልጻፍኩበት። መጻፍ እንደው ክህሎት (skill) ነውና፥ ፍላጎቱ እና የተወሰነ ተሰጥኦው ካለ ያድጋል። ደግሞ ባይሆንስ፥ እኔ ሀሳቤን ብገልጽና ያመንኩበትን ብናገር ኑሮውን አላዘባርቅበት። “በርታ…ይሄን ደግሞ እንዲህ አሻሽለው” ቢል ምናለ?” ምናምን እያልኩ ከራሴ ጋር አወራ እና እተወዋለሁ።
 
እሱ አይተወውም።
 
ሌላ ላስታውስ…
 
ስለ ሥራ ማጣት እየተወራ ነው። እኔም ሥራ ፍለጋ ላይ ነበርኩ። የደረሰባችሁና የደረሰላችሁ እንደምታውቁት፥ አብዛኛው ሥራ በዝምድና እና በፖለቲካ አቋም ሁኔታ ነው የሚወሰነው።
 
ከወዳጆቼ ጋር ሰብሰብ ብለን፥ እኔም የራሴን ልምድ ተናገርኩ። “ለስንትና ስንት ጊዜ የሥራ ማመልከቻ ባስገባም፥ ማንም ጠርቶኝ አያውቅም። ግን…” አልኩ። ሲስተሙንም መኮነኔ እና ምሬቴን መግለጼም ጭምር እንጂ፥ በዋናነት ስለራሴ ማውራቴ፣ ወይም የሚታዘንልኝን ናፍቄም አልነበረም።
 
“ግን” ያልኩበትን አፍም ሳልሰበስብ፥ “ኦህ… እንደዛ ነው እኮ። ምን ታረገዋለህ?” ምናምን ተባለ። ወዲያውም “ወዳጄ” የምለው ሰው፣ ለኪነጥበቡ ቅርብ የሆነ (እንደመፍትሄም ጭምር መሆኑ ነው) “ግን ለምን ጽሁፉን seriously አትወስደውም። የሙሉ ጊዜ ጸሐፊ ብትሆን ነው ሁሌ የማስበው። በእጅ ያለ ወርቅ አታርገው። እንግሊዘኛም ጥሩ ነህ። You know, እንደዛ ቢሆን እኮ…”
 
እንደማላደርገው ስለማውቅ፥ “ኧረ እኔ እኮ ለሙሉ ጸሐፊነት የሚያበቃ አቅሙ የለኝም። ጭራሽ እንግሊዘኛ።” ምናምን ብዬ ላሽ አልኩት።
 
የእርሱን ምክር ጋብ አድርጌ፥ “ግን ተመስገን ነው! እስካሁን የምሰራው አላጣሁም። በራሴው ጥረት ተነጋግሬ እና ተደራድሬ በተሻለ ደመወዝ ነው የምሰራው። እኔው ነኝ እንዲቀጥሩኝ የማግባባው። ነገሩ ይገርማል እንጂ ምንም አላጣሁ።” ስል፥
 
“እስኪ ስለራስህ ሌላ ሰው ያውራ።” ብሎ ኩም ሊያረገኝ ይሞክራል። (በጣም ግልጽ ከሆነ ነው ይሄ።) ካልሆነ ደግሞ፥ “ኡፍ እሱ ደግሞ ጉራው መከራ” ምናምን ተብዬ ጫት ማባያ እና ቡና ማጣጫ እሆናለሁ።
 
“ቆይ ግን እኔው ራሴ ስለተንከራተትኩትና ስላወጣሁት ጥረት ማን ነው ማውራት ያለበት? ራሴን ሸጬ ሳበቃ አሻሻጤን በተመለከተ ልምድ ቢቀስምስ እርሱ ነገ የኔን መንገድ ተከትሎ በተሻለ ዋጋ ለተሻለ ቦታ ራሱን ይሸጥም አልነበር? እሱም ቢቀር ስለሆነልኝ ባመሰግንስ ምን አለ? ወይስ ወዳድቄ ሥራ ፈትቼ ብኖር ደስ ይለው ነበር? ስንገርም” ብዬ ተውኩት።
 
ኖርን ኖርንና… በራሴ ገንዘብ፣ በራሴ ትርፍ ጊዜ የጫርኳቸውን ሰብስቤ መጽሐፍ ማሳተሜን ተከትሎ፥ “ኑ ጸበል ቅመሱ” ብዬ የምረቃ ድግስ መጥራቴ ሲወራ፥
 
“አበደ ፈረሴ” አለ። ከጀርባዬ ዘለዘለኝ። ሚስቱን እንደቀማሁበት ሁሉ ጉዳዩ እኔው ሆንኩኝ። አንዳች አገራዊ ጉዳይ እንደተስተጓጎለ ሁሉ በየሄደበት፣ በየወዳጆቻችን ፊት አማኝ። የአጻጻፌን አስጸያፊነትና የባህርዬን መጥፎነት አተተ። አልሰማሁትም እንጂ፥ ወላ “ይቅርብህ” ሊለኝም ዳዳው። …እንግዲህ በትርፍ ሰዓት የሞከርኩትን የማያደንቅ “ወዳጄ” ነው “የሙሉ ሰዓት ጸሐፊ ሁን” ሲለኝ የነበረው።
 
“ምነው ይሄን ያህል፥ ግፋ ቢል ያለመነበብ እጣ ፈንታ ቢገጥመኝ፣ ወይ ደግሞ ጥሩ መጽሐፍ እንዴት እንደማይጻፍ መማሪያ ብሆን ነው እንጂ… የአገር ሀብት መዝብሬ አላሳተምኩ። እሱ ግን ብዋረድ ብቻ ነው ሚደሰተው?” ብዬ ሥራዬን ቀጠልኩ።
 
ፕሮግራሙ ያማረ ሲሆንም፥ እንዲህ ሆነ።
 
ተነቦ ገንቢ feedback ሳገኝም፥እንዲህ ሆነ።
 
አያርገውና፥ “ተበድሬ አሳትሜው ነበር። እና ሙሉ ለሙሉ ከሰርኩኝና የሰው ገንዘብ እንዴት እንደምመልስ ቸገረኝ።” ብለው ኖሮ፥ እርግጠኛ ነኝ “እናዋጣለት” ባይልም ገንዘቡን መልሼ የማገኝበትን መንገድ ለመጠቆም ይሞክር ነበር።
 
‘እንዲህ ያለውን ነገር ብናሻሽል የተሻለ እንኖርና ኀዘናችንም ይቀል ነበር’ እላለሁ።
 
====
 
አቡኪ ሞት ሰቅጥጦኝ ስባዝን ነው ‘randomly’ ይሄን ይሄን የማስበው።
ብልጭ ድርግም አለ። በወጣትነቱ ሄደ። ሞት አዲስ ሆኖ በመጣ ቁጥር ቢያስደነግጥም፥ ነገም እንዲሁ ነን እኛ።
ነፍሱን በአጸደ ገነት ያኑራት!
13342971_646994268791366_2197683848191752176_n
ልበ ቀናው ወዳጃችን ይህ ነበር። 😥 

የሁለት ዓለም…

አብሮ መኖር ማለት፥
“ተማርጦ መሻለም”፣ “መርጦ ማየት” ማለት፣ ሆኖ ተቸግረን፣
አለን……. ከአንድ የአበባ ማሳ እኩል ተበትነን፤
 
እናንተ ቀንቷችሁ፥ አበባ መርጣችሁ፣ አበባ ስታዩ፣
ከቀለም ቀለሙ፥ ስትቀጥፉ ከቢጫው፣ ስትቀጥፉ ከቀዩ፤
 
እኛ ግንድ ለግንድ (በምን ያል እርግማን) ከእሾህ ስንታከክ፣ ሲያቆስለን ስቃዩ…
ከአበባ ማሳ ላይ በኬሚካል ብዛት ጤናውን እያጣ፣
_ለቁጥቁጥ ደመወዝ፣ ለኩርማን እንጀራ፥ የሰው ልጅ ባታዩ፣
ምስኪኑ ገበሬ፥ በገዛ መሬቱ በጨፈቃ ተመን፣ “ካሳ” ተቆርጦለት
ቱጃር ካንጣለለው የአበባ እርሻ ላይ በ“ጥበቃ” መደብ ከበራፍ ላይ ዋዩ…
ጎልተው እየታዩን ከቀለማት ደምቀው፣ ከጽጌያት ልቀው፣
መልካት አፈትልከው፣ በግፍ መሀል ወጥተው፤
 
እናንተ ከማሳው ባገኛችሁት ሲሳይ፣ በአበባ አጀባ፣
ከምስኪን ሴት ልብ ውስጥ ልባችሁ ሲገባ፣
በምናብ ሲሰመር፥ አንሶላው ሲፈረሽ፣
(ስጋ ነፍስ ሲለያይ፣ ትራስ ተንተርሶ)
በስሜት ሲቀመር፥ “ሰበረልዎ” ሲዜም፣
(ሰባራ እንኳን ቢሆን በምላስ ታድሶ)
 
እኛ እናስባለን የሰቀቀን ዜማ፥
በአበባዮሽ መሀል የተሰነቀረ፣
_በአበባ ተከ’ቦ፣ በናፍቆት ሚሰማ
 
“እንኳን ቤትና የለኝም አጥር፣
እደጅ አድራለሁ ኮከብ ስቆጥር”
 
ስትል ባታይቱ፣
ጊዜ እና ጊዜያዊ ገሸሽ ያደረጓት፣ ባለመሬቲቱ።
 
“ንፍሮ ቀቅዬ ብላ ብለው
ጉልቻ አንስቶ ጎኔን አለው”
 
ስትል ምስኪኒቱ፣
የባለስልጣኑ፣ የባለጉልበቱ፣ ታማኝ ባለቤቱ።
 
ጆሯችን ይገባል፣ እናዳምጣለን፥
ምርጫ ተቸግረን፣ ተረግመን! ተለክፈን!
 
/ዮሐንስ ሞላ/

ወፌ ወፌ ላላ

ተራማጁን ጥሎ. . .
አጥንቱን ረብርቦ፣ ሥጋውን ደልድሎ፣
ተራማጁን ይዞ. . .
እግር ከወርች አስሮ፣ ካ’ለም በቃኝ ዱሎ፣
ይገነባል ሌላ፤
ወፌ ወፌ ላላ. . .
 
ይውላል ሲያሽላላ፣ ሲገርፍ ያንን ገላ፤
ያንን ለጋ ብልት፣ ያን ልስልስ ሰውነት፣
ያንን ጉስቁል ዛላ፣
ወፌ ወፌ ላላ. . .
 
ተራማጁን ጠምዶ፣
ከጎጆው አሳ’ዶ፣ ከሰው ቀዬ ጥሎ፤
ድንጋዩን ፈንቅሎ፣ አፈሩን ፈልፍሎ፣
መንገዱን ጠርቅሞ፣ ይቀይሳል ሌላ፣
ወፌ ወፌ ላላ. . .
 
ሕያዉን አባርሮ፣ ግዑዝ ይቆልላል፣
ታዛውን ጠርምሶ፣ ሌላ ይቀልሳል፤
አለት ይከምራል፣ አፈር ያላቁጣል፣
ይህን አፈናቅሎ፤ ያንን ያሳፍራል፣
ጠርሙስ እየፈጨ፣ ጠርሙስ ይጋግራል፤
ኑሮውን ጠርምሶ፣ ሰዉን አፈናቅሎ. . .
ሌላውን ያሰፍራል፣ ቋሚውን መንግሎ፣
ወፌ ወፌ ላላ. . .
 
ጎጆሽ የቆመበት፣ የታል ያንቺ ባላ?
የታል ቅርንጫፉ? የቤትሽ ከለላ?
ስንጥር፣ ዝንጣፊው? የማደሪያሽ ጥላ?
የታል መጋረጃው፥ – የጓዳሽ ከለላ?
ወፌ ወፌ ላላ. . .
 
ለእኔ ይተርፋል ብዬ የተመካሁበት
ቢጋርደኝ ብዬ፥ ቢያስጥለኝ ከበላ፣
ቢያተርፈኝ ካውላላ የተጠለልኩበት
የማደሪያሽ ጥላ፤
የታል ያንቺ ባላ? የታል የእኔ ገላ?
የታል ያ ሰውነት? – ሰዉን አጫራሹ፣
– ጎጆ አስቀላሹ፣ አብራሪው በራሪው፥
– አፍራሹ፣ አዳሹ፥. . . ያ ዘንካታ ገላ?
የታል ያ ዝማሬ? የታል ያ ቅላፄ? የታል ያ ሽለላ?
 
ወፌ ወፌ ላላ፥
 
ብር በይ ወደ እኔ፥ (እንዲህ ተጎሳቁለሽ) ወፍ ሳያይሽ ሌላ፣
የቃረምሽው ካለ፣ ማዕድ እንካበብ፣ ነይ አብረን እንብላ።
ከሌለም እንተኛ፣ – ተቃቅፈን እንጥፋ፣
– እስክንነቃ ድረስ፣ ሌሊቱ እስኪገፋ፣
እናንጋ፥ ባንድ አልጋ! እናውጋ በይፋ!
እየቋጨን አምሮት፣ እየቋጠርን ምኞት፣ እየሰፋን ተስፋ፣
እንዲህ እንጨዋወት. . .
ወፌ ወፌ ላላ. . .
እስከጊዜው ድረስ፥ እስኪመታ መላ፣
ይኸኛው ተገፍቶ፣ እስኪተካ ሌላ!
 
/ዮሐንስ ሞላ (2008) “የብርሃን ሰበዞች” ገጽ 64 – 65/

በአቅመቢስነት :-/

13507048_1604998063164033_3307705846976265661_nቀንቶት የሰው አገር ያየ ግን እንዴት ለአገሩ አይቀናም?? የሰውን አገር ስርዓት የተመለከተ ሰው እንዴት ለአገሩ ያንን አይመኝም?? የሰው አገርን የሰው ልጅ አከባበር ያስተዋለ ሰው ቀጥሎ እንዴት ሰውን ለማዋረድ (በዚያም ራሱን ለማዋረድ) ይፈቅዳል?? ባለስልጣናቱ በየስብሰባው፣ በየሽርሽሩ እና በየሰበብአስባቡ፣ በየተረተሩና ሸንተረሩ ሲንቀዋለሉ፥ እንዴት ነው… መንገዱን፣ ጽዳቱን፣ ስርዓቱን፣ ልምላሜውን፣ ጥጋቡን፣ ቅንነቱን፣ ሌላ ሌላ መልካሙን ሁሉ አገር ቤት ጭነው ስለመሄድ የማይቋምጡት??
 
ይገርማል! ሰው አገር ውስጥ ሰው ቢታመም፥ አስፈላጊውን ህክምና ከሰጡ በኋላ ነው ስለቢል የሚያወሩት፤ እንጂ ነፍስ ውጪ ግቢ የሚልን ሰው ህክምና አይነፍጉም። ዴሞክራሲያዊ ስርዓት በሰፈነባቸው አገራት፥ ፍትህ ይከበር ዘንድ፥ በወንጀል የሚፈለግ ሰው እንኳን እንደዋዛ በሞት ሲሰናበት ይበግናሉ። ቢችሉ አስታመው፣ አሻሽተው ነው ለፍትህ የሚያቀርቡት። (አሁን ለምሳሌ፥ ይሄን ሁሉ ነቀርሳ የተከሉት የቀድሞው ጠ/ሚ ሞት ልብ ተብሎ፣ በንጹህ አእምሮ ቢታሰብ እንዴት ያበግናል? እንዲሁ እንደጻድቅ ማሸለባቸው ሲታሰብ እንዴት ያንገበግባል? መቼስ ነፍስ የእግዚአብሔር ነውና ከሞት በኋላ አይፋረዱ ነገር!)
 
እነሱ ስለመንገድ እንጂ ስለተራማጅ ሰው ማውራት እርማቸው ነው። ስለህንጻ እንጂ ስለሰውነት መባዘን ሞታቸው ነው። …እንደው ህንጻና መንገዱንም በቅጡ በሰሩት እኮ! ሰው አገር ያለውን የመንገድ ስርዓት በቀዱት! ለፓርኪንግ (ለዚሁ ብቻ በታነጹ) ስንትና ስንት የተንጣለሉ ህንጻዎች ውስጥ ተሹሎክሉኮ መኪናውን ያቆመ ባለስልጣን፥ አገሩ ላይ ስለልማት ሲያወራ እንኳን፣ ጥራት እና ደረጃ እንኳን ህቅ አያደርገውም? “ልማት ልማት፣ እትት ብትት፣ ጸረ ልማት ኃይሎች…” ሲገርም! ሲያሳፍር!
 
“ኮንዶሚነም ተሰራ” ቢባል፥ ግማሹ በዝምድና እና በፖለቲካ ተሳትፎ ተደልድሎ የተረፈው፣ በስንትና ስንት ስለት እና ጾም ጸሎት በሚደርስ ዕጣ እንኳን፥ “ፈረሰ አልፈረሰ”፣ ሌት ተቀን በስጋት ነው። ደግሞ ሰው ስብሰባ ጠርቶ፣ ሰው አገር የታለፈ እና፣ ሌላ ሰው እንዲያነሳው በክብር የትም የሚጣል ጥሪት (ኩርሲ፣ ጠረጴዛ፣ መሶብ፣ ሶፋ፣ ብፌ፣ ቴሌቪዥን፣ አልጋ፣ መደርደሪያ፣ ሌላም ሌላም… ) ላይ ቤት መናድም አለ። የከርታታን ሰው፥ ተስፋንም፣ ጉጉትንም፣ ጥረትንም አብሮ መቅበር አለ። ከዚያ ሰላማዊን ሰው አውሬ ማድረግ! “ምን ልብላ” ብሎ ሥራ ሲፈልግ፥ ፈርዶበት አግኝቶት ለመንግስት ያፈነደደንና ሆዱን ለመጠቅጠቅ ሰፊውን ህዝብ በከንቱ ያስለቀሰ እና ያስቀመየን ምስኪን ፖሊስ ማስበላትና ደሙን በከንቱ ማፍሰስ! :-/
 
ከዚያ፥
 
“ሳሩን በልቶ ውሀውን ጠጥቶ የተኛውን በሬ፣
ጎትጉተው ጎትጉተው አደረጉት አውሬ” ይዘፈናል።
 
አንድን በሀሳብ የሚሞግት ተቃዋሚን ሰው፣ እሱንም በሀሰት ወንጅለው እንደማይገባው በግፍ ያንገላቱትን፣ ለህክምና እንዳይጓዝ በማገድ ማሰቃየት ክፋት እንጂ ሌላ ምን ይሆናል?? ከአገር ቢወጣ ምን እንዳይጎዳቸው ነው?? መቼስ አገር ውስጥ ሆኖ ከእንግዲህ ድኖ ለእነርሱ ሰው አይሆናቸው። ወጥቶ እንዳይቀር ሰጉ?? ምነው ይሄን ያህል፥ ሺህ ዓመት አይኖር! ሺህ ዓመት በድለው እና አሳቅቀው አይነግሱ! በየትኛውም አገር ታሪክ ከዚህ ቀደም ሲበድሉ የነበሩት ቀናቸው ሲደርስ ከቅጣት አለፉ??
 
ወዳጄ ሀብታሙ አያሌው የምታምነው አምላክ ይቅደምልህና በምህረቱ ይጎብኝህ! ቅድስት ማርያም ትዳብስህ! ልባቸውን ያራራልህና ወጣትነትህ ለቤተሰብህና ለህልምህ ይትረፍ!