በአቅመቢስነት :-/

13507048_1604998063164033_3307705846976265661_nቀንቶት የሰው አገር ያየ ግን እንዴት ለአገሩ አይቀናም?? የሰውን አገር ስርዓት የተመለከተ ሰው እንዴት ለአገሩ ያንን አይመኝም?? የሰው አገርን የሰው ልጅ አከባበር ያስተዋለ ሰው ቀጥሎ እንዴት ሰውን ለማዋረድ (በዚያም ራሱን ለማዋረድ) ይፈቅዳል?? ባለስልጣናቱ በየስብሰባው፣ በየሽርሽሩ እና በየሰበብአስባቡ፣ በየተረተሩና ሸንተረሩ ሲንቀዋለሉ፥ እንዴት ነው… መንገዱን፣ ጽዳቱን፣ ስርዓቱን፣ ልምላሜውን፣ ጥጋቡን፣ ቅንነቱን፣ ሌላ ሌላ መልካሙን ሁሉ አገር ቤት ጭነው ስለመሄድ የማይቋምጡት??
 
ይገርማል! ሰው አገር ውስጥ ሰው ቢታመም፥ አስፈላጊውን ህክምና ከሰጡ በኋላ ነው ስለቢል የሚያወሩት፤ እንጂ ነፍስ ውጪ ግቢ የሚልን ሰው ህክምና አይነፍጉም። ዴሞክራሲያዊ ስርዓት በሰፈነባቸው አገራት፥ ፍትህ ይከበር ዘንድ፥ በወንጀል የሚፈለግ ሰው እንኳን እንደዋዛ በሞት ሲሰናበት ይበግናሉ። ቢችሉ አስታመው፣ አሻሽተው ነው ለፍትህ የሚያቀርቡት። (አሁን ለምሳሌ፥ ይሄን ሁሉ ነቀርሳ የተከሉት የቀድሞው ጠ/ሚ ሞት ልብ ተብሎ፣ በንጹህ አእምሮ ቢታሰብ እንዴት ያበግናል? እንዲሁ እንደጻድቅ ማሸለባቸው ሲታሰብ እንዴት ያንገበግባል? መቼስ ነፍስ የእግዚአብሔር ነውና ከሞት በኋላ አይፋረዱ ነገር!)
 
እነሱ ስለመንገድ እንጂ ስለተራማጅ ሰው ማውራት እርማቸው ነው። ስለህንጻ እንጂ ስለሰውነት መባዘን ሞታቸው ነው። …እንደው ህንጻና መንገዱንም በቅጡ በሰሩት እኮ! ሰው አገር ያለውን የመንገድ ስርዓት በቀዱት! ለፓርኪንግ (ለዚሁ ብቻ በታነጹ) ስንትና ስንት የተንጣለሉ ህንጻዎች ውስጥ ተሹሎክሉኮ መኪናውን ያቆመ ባለስልጣን፥ አገሩ ላይ ስለልማት ሲያወራ እንኳን፣ ጥራት እና ደረጃ እንኳን ህቅ አያደርገውም? “ልማት ልማት፣ እትት ብትት፣ ጸረ ልማት ኃይሎች…” ሲገርም! ሲያሳፍር!
 
“ኮንዶሚነም ተሰራ” ቢባል፥ ግማሹ በዝምድና እና በፖለቲካ ተሳትፎ ተደልድሎ የተረፈው፣ በስንትና ስንት ስለት እና ጾም ጸሎት በሚደርስ ዕጣ እንኳን፥ “ፈረሰ አልፈረሰ”፣ ሌት ተቀን በስጋት ነው። ደግሞ ሰው ስብሰባ ጠርቶ፣ ሰው አገር የታለፈ እና፣ ሌላ ሰው እንዲያነሳው በክብር የትም የሚጣል ጥሪት (ኩርሲ፣ ጠረጴዛ፣ መሶብ፣ ሶፋ፣ ብፌ፣ ቴሌቪዥን፣ አልጋ፣ መደርደሪያ፣ ሌላም ሌላም… ) ላይ ቤት መናድም አለ። የከርታታን ሰው፥ ተስፋንም፣ ጉጉትንም፣ ጥረትንም አብሮ መቅበር አለ። ከዚያ ሰላማዊን ሰው አውሬ ማድረግ! “ምን ልብላ” ብሎ ሥራ ሲፈልግ፥ ፈርዶበት አግኝቶት ለመንግስት ያፈነደደንና ሆዱን ለመጠቅጠቅ ሰፊውን ህዝብ በከንቱ ያስለቀሰ እና ያስቀመየን ምስኪን ፖሊስ ማስበላትና ደሙን በከንቱ ማፍሰስ! :-/
 
ከዚያ፥
 
“ሳሩን በልቶ ውሀውን ጠጥቶ የተኛውን በሬ፣
ጎትጉተው ጎትጉተው አደረጉት አውሬ” ይዘፈናል።
 
አንድን በሀሳብ የሚሞግት ተቃዋሚን ሰው፣ እሱንም በሀሰት ወንጅለው እንደማይገባው በግፍ ያንገላቱትን፣ ለህክምና እንዳይጓዝ በማገድ ማሰቃየት ክፋት እንጂ ሌላ ምን ይሆናል?? ከአገር ቢወጣ ምን እንዳይጎዳቸው ነው?? መቼስ አገር ውስጥ ሆኖ ከእንግዲህ ድኖ ለእነርሱ ሰው አይሆናቸው። ወጥቶ እንዳይቀር ሰጉ?? ምነው ይሄን ያህል፥ ሺህ ዓመት አይኖር! ሺህ ዓመት በድለው እና አሳቅቀው አይነግሱ! በየትኛውም አገር ታሪክ ከዚህ ቀደም ሲበድሉ የነበሩት ቀናቸው ሲደርስ ከቅጣት አለፉ??
 
ወዳጄ ሀብታሙ አያሌው የምታምነው አምላክ ይቅደምልህና በምህረቱ ይጎብኝህ! ቅድስት ማርያም ትዳብስህ! ልባቸውን ያራራልህና ወጣትነትህ ለቤተሰብህና ለህልምህ ይትረፍ!

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s