ተራማጁን ጥሎ. . .
አጥንቱን ረብርቦ፣ ሥጋውን ደልድሎ፣
ተራማጁን ይዞ. . .
እግር ከወርች አስሮ፣ ካ’ለም በቃኝ ዱሎ፣
ይገነባል ሌላ፤
ወፌ ወፌ ላላ. . .
ይውላል ሲያሽላላ፣ ሲገርፍ ያንን ገላ፤
ያንን ለጋ ብልት፣ ያን ልስልስ ሰውነት፣
ያንን ጉስቁል ዛላ፣
ወፌ ወፌ ላላ. . .
ተራማጁን ጠምዶ፣
ከጎጆው አሳ’ዶ፣ ከሰው ቀዬ ጥሎ፤
ድንጋዩን ፈንቅሎ፣ አፈሩን ፈልፍሎ፣
መንገዱን ጠርቅሞ፣ ይቀይሳል ሌላ፣
ወፌ ወፌ ላላ. . .
ሕያዉን አባርሮ፣ ግዑዝ ይቆልላል፣
ታዛውን ጠርምሶ፣ ሌላ ይቀልሳል፤
አለት ይከምራል፣ አፈር ያላቁጣል፣
ይህን አፈናቅሎ፤ ያንን ያሳፍራል፣
ጠርሙስ እየፈጨ፣ ጠርሙስ ይጋግራል፤
ኑሮውን ጠርምሶ፣ ሰዉን አፈናቅሎ. . .
ሌላውን ያሰፍራል፣ ቋሚውን መንግሎ፣
ወፌ ወፌ ላላ. . .
ጎጆሽ የቆመበት፣ የታል ያንቺ ባላ?
የታል ቅርንጫፉ? የቤትሽ ከለላ?
ስንጥር፣ ዝንጣፊው? የማደሪያሽ ጥላ?
የታል መጋረጃው፥ – የጓዳሽ ከለላ?
ወፌ ወፌ ላላ. . .
ለእኔ ይተርፋል ብዬ የተመካሁበት
ቢጋርደኝ ብዬ፥ ቢያስጥለኝ ከበላ፣
ቢያተርፈኝ ካውላላ የተጠለልኩበት
የማደሪያሽ ጥላ፤
የታል ያንቺ ባላ? የታል የእኔ ገላ?
የታል ያ ሰውነት? – ሰዉን አጫራሹ፣
– ጎጆ አስቀላሹ፣ አብራሪው በራሪው፥
– አፍራሹ፣ አዳሹ፥. . . ያ ዘንካታ ገላ?
የታል ያ ዝማሬ? የታል ያ ቅላፄ? የታል ያ ሽለላ?
ወፌ ወፌ ላላ፥
ብር በይ ወደ እኔ፥ (እንዲህ ተጎሳቁለሽ) ወፍ ሳያይሽ ሌላ፣
የቃረምሽው ካለ፣ ማዕድ እንካበብ፣ ነይ አብረን እንብላ።
ከሌለም እንተኛ፣ – ተቃቅፈን እንጥፋ፣
– እስክንነቃ ድረስ፣ ሌሊቱ እስኪገፋ፣
እናንጋ፥ ባንድ አልጋ! እናውጋ በይፋ!
እየቋጨን አምሮት፣ እየቋጠርን ምኞት፣ እየሰፋን ተስፋ፣
እንዲህ እንጨዋወት. . .
ወፌ ወፌ ላላ. . .
እስከጊዜው ድረስ፥ እስኪመታ መላ፣
ይኸኛው ተገፍቶ፣ እስኪተካ ሌላ!
/ዮሐንስ ሞላ (2008) “የብርሃን ሰበዞች” ገጽ 64 – 65/