አብሮ መኖር ማለት፥
“ተማርጦ መሻለም”፣ “መርጦ ማየት” ማለት፣ ሆኖ ተቸግረን፣
አለን……. ከአንድ የአበባ ማሳ እኩል ተበትነን፤
እናንተ ቀንቷችሁ፥ አበባ መርጣችሁ፣ አበባ ስታዩ፣
ከቀለም ቀለሙ፥ ስትቀጥፉ ከቢጫው፣ ስትቀጥፉ ከቀዩ፤
እኛ ግንድ ለግንድ (በምን ያል እርግማን) ከእሾህ ስንታከክ፣ ሲያቆስለን ስቃዩ…
ከአበባ ማሳ ላይ በኬሚካል ብዛት ጤናውን እያጣ፣
_ለቁጥቁጥ ደመወዝ፣ ለኩርማን እንጀራ፥ የሰው ልጅ ባታዩ፣
ምስኪኑ ገበሬ፥ በገዛ መሬቱ በጨፈቃ ተመን፣ “ካሳ” ተቆርጦለት
ቱጃር ካንጣለለው የአበባ እርሻ ላይ በ“ጥበቃ” መደብ ከበራፍ ላይ ዋዩ…
ጎልተው እየታዩን ከቀለማት ደምቀው፣ ከጽጌያት ልቀው፣
መልካት አፈትልከው፣ በግፍ መሀል ወጥተው፤
እናንተ ከማሳው ባገኛችሁት ሲሳይ፣ በአበባ አጀባ፣
ከምስኪን ሴት ልብ ውስጥ ልባችሁ ሲገባ፣
በምናብ ሲሰመር፥ አንሶላው ሲፈረሽ፣
(ስጋ ነፍስ ሲለያይ፣ ትራስ ተንተርሶ)
በስሜት ሲቀመር፥ “ሰበረልዎ” ሲዜም፣
(ሰባራ እንኳን ቢሆን በምላስ ታድሶ)
እኛ እናስባለን የሰቀቀን ዜማ፥
በአበባዮሽ መሀል የተሰነቀረ፣
_በአበባ ተከ’ቦ፣ በናፍቆት ሚሰማ
“እንኳን ቤትና የለኝም አጥር፣
እደጅ አድራለሁ ኮከብ ስቆጥር”
ስትል ባታይቱ፣
ጊዜ እና ጊዜያዊ ገሸሽ ያደረጓት፣ ባለመሬቲቱ።
“ንፍሮ ቀቅዬ ብላ ብለው
ጉልቻ አንስቶ ጎኔን አለው”
ስትል ምስኪኒቱ፣
የባለስልጣኑ፣ የባለጉልበቱ፣ ታማኝ ባለቤቱ።
ጆሯችን ይገባል፣ እናዳምጣለን፥
ምርጫ ተቸግረን፣ ተረግመን! ተለክፈን!
/ዮሐንስ ሞላ/