ማኅበራዊ መዋቅራችን አጓጉል ነው። ከደስታ ይልቅ ኀዘንን ለማስታመም ይቀለናል። ከእልልታ ይልቅ ለከንፈር መጠጣ የሚያፈጥነን ይመስላል። በሰው ደስታ ከምንደሰተው ይልቅ፣ ሰዎችን ለተሻለ ፍላጎታቸው ከምንገፋቸው ይልቅ፣ በኀዘናቸው የምንማቅቀው ይበዛል፤ ከፍላጎታቸው ምንገፈትራቸው ይልቃል። በደግ ቀን፥ ስም ስንሰጣጥ፣ ስንፈራረጅ ነው የምንውለው። ደሞ ትንሽ ችግር ሲደቁሰን፥ “ወንድሜ እህቴ” ስንባባልና ስንረባረብ ለጉድ ነው የምናስቀናው።
ለምሳሌ፥ አይበለውና እግሬ ቢቆረጥ ሳር ቅጠሉ ያዝናል። ያየ የሰማም ከንፈር መምጠጡ አይቀርም። ደግሞ፥ ይበለውና ዘናጭ መኪና ብገዛ በጣም ጥቂቶች ናቸው የደስታዬ ተካፋይ የሚሆኑት።
ከማስታውሰው…
ሳልጠይቀው፣ አንድም ቀን… ‘ሞካሪ’ እና ‘የትርፍ ሰዓት ሞንጫሪ’ ነኝ እንጂ፥ አፌን ሞልቼ እንደ ማዕረግ (title) እንኳን ‘ጸሐፊ’ ነኝ የማልልበትን ጉዳይ አንስቶ ሲያንቆለጳጵሰኝ የኖረ ሰው፣ የሆነ ቀን… ከጀርባዬ በመጻፍ ባህርዬ የተነሳ፣ በክፉ በደግ ሲያነሳኝ ከርሞ፣ የሰማሁ ሲመስለው ደግሞ፥ ነገሩም ውኀ እንዲያነሳለት እኔን ማጣጣልና ማንቋሸሽ ተጨማሪ ሥራው ያደርገዋል።
“ይሄን ያህል ምን አጠፋሁና ነው? እርሱ ቦታ አልሄድኩ። ሀሳቡን ካፉ ነጥቄው አልጻፍኩበት። መጻፍ እንደው ክህሎት (skill) ነውና፥ ፍላጎቱ እና የተወሰነ ተሰጥኦው ካለ ያድጋል። ደግሞ ባይሆንስ፥ እኔ ሀሳቤን ብገልጽና ያመንኩበትን ብናገር ኑሮውን አላዘባርቅበት። “በርታ…ይሄን ደግሞ እንዲህ አሻሽለው” ቢል ምናለ?” ምናምን እያልኩ ከራሴ ጋር አወራ እና እተወዋለሁ።
እሱ አይተወውም።
ሌላ ላስታውስ…
ስለ ሥራ ማጣት እየተወራ ነው። እኔም ሥራ ፍለጋ ላይ ነበርኩ። የደረሰባችሁና የደረሰላችሁ እንደምታውቁት፥ አብዛኛው ሥራ በዝምድና እና በፖለቲካ አቋም ሁኔታ ነው የሚወሰነው።
ከወዳጆቼ ጋር ሰብሰብ ብለን፥ እኔም የራሴን ልምድ ተናገርኩ። “ለስንትና ስንት ጊዜ የሥራ ማመልከቻ ባስገባም፥ ማንም ጠርቶኝ አያውቅም። ግን…” አልኩ። ሲስተሙንም መኮነኔ እና ምሬቴን መግለጼም ጭምር እንጂ፥ በዋናነት ስለራሴ ማውራቴ፣ ወይም የሚታዘንልኝን ናፍቄም አልነበረም።
“ግን” ያልኩበትን አፍም ሳልሰበስብ፥ “ኦህ… እንደዛ ነው እኮ። ምን ታረገዋለህ?” ምናምን ተባለ። ወዲያውም “ወዳጄ” የምለው ሰው፣ ለኪነጥበቡ ቅርብ የሆነ (እንደመፍትሄም ጭምር መሆኑ ነው) “ግን ለምን ጽሁፉን seriously አትወስደውም። የሙሉ ጊዜ ጸሐፊ ብትሆን ነው ሁሌ የማስበው። በእጅ ያለ ወርቅ አታርገው። እንግሊዘኛም ጥሩ ነህ። You know, እንደዛ ቢሆን እኮ…”
እንደማላደርገው ስለማውቅ፥ “ኧረ እኔ እኮ ለሙሉ ጸሐፊነት የሚያበቃ አቅሙ የለኝም። ጭራሽ እንግሊዘኛ።” ምናምን ብዬ ላሽ አልኩት።
የእርሱን ምክር ጋብ አድርጌ፥ “ግን ተመስገን ነው! እስካሁን የምሰራው አላጣሁም። በራሴው ጥረት ተነጋግሬ እና ተደራድሬ በተሻለ ደመወዝ ነው የምሰራው። እኔው ነኝ እንዲቀጥሩኝ የማግባባው። ነገሩ ይገርማል እንጂ ምንም አላጣሁ።” ስል፥
“እስኪ ስለራስህ ሌላ ሰው ያውራ።” ብሎ ኩም ሊያረገኝ ይሞክራል። (በጣም ግልጽ ከሆነ ነው ይሄ።) ካልሆነ ደግሞ፥ “ኡፍ እሱ ደግሞ ጉራው መከራ” ምናምን ተብዬ ጫት ማባያ እና ቡና ማጣጫ እሆናለሁ።
“ቆይ ግን እኔው ራሴ ስለተንከራተትኩትና ስላወጣሁት ጥረት ማን ነው ማውራት ያለበት? ራሴን ሸጬ ሳበቃ አሻሻጤን በተመለከተ ልምድ ቢቀስምስ እርሱ ነገ የኔን መንገድ ተከትሎ በተሻለ ዋጋ ለተሻለ ቦታ ራሱን ይሸጥም አልነበር? እሱም ቢቀር ስለሆነልኝ ባመሰግንስ ምን አለ? ወይስ ወዳድቄ ሥራ ፈትቼ ብኖር ደስ ይለው ነበር? ስንገርም” ብዬ ተውኩት።
ኖርን ኖርንና… በራሴ ገንዘብ፣ በራሴ ትርፍ ጊዜ የጫርኳቸውን ሰብስቤ መጽሐፍ ማሳተሜን ተከትሎ፥ “ኑ ጸበል ቅመሱ” ብዬ የምረቃ ድግስ መጥራቴ ሲወራ፥
“አበደ ፈረሴ” አለ። ከጀርባዬ ዘለዘለኝ። ሚስቱን እንደቀማሁበት ሁሉ ጉዳዩ እኔው ሆንኩኝ። አንዳች አገራዊ ጉዳይ እንደተስተጓጎለ ሁሉ በየሄደበት፣ በየወዳጆቻችን ፊት አማኝ። የአጻጻፌን አስጸያፊነትና የባህርዬን መጥፎነት አተተ። አልሰማሁትም እንጂ፥ ወላ “ይቅርብህ” ሊለኝም ዳዳው። …እንግዲህ በትርፍ ሰዓት የሞከርኩትን የማያደንቅ “ወዳጄ” ነው “የሙሉ ሰዓት ጸሐፊ ሁን” ሲለኝ የነበረው።
“ምነው ይሄን ያህል፥ ግፋ ቢል ያለመነበብ እጣ ፈንታ ቢገጥመኝ፣ ወይ ደግሞ ጥሩ መጽሐፍ እንዴት እንደማይጻፍ መማሪያ ብሆን ነው እንጂ… የአገር ሀብት መዝብሬ አላሳተምኩ። እሱ ግን ብዋረድ ብቻ ነው ሚደሰተው?” ብዬ ሥራዬን ቀጠልኩ።
ፕሮግራሙ ያማረ ሲሆንም፥ እንዲህ ሆነ።
ተነቦ ገንቢ feedback ሳገኝም፥እንዲህ ሆነ።
አያርገውና፥ “ተበድሬ አሳትሜው ነበር። እና ሙሉ ለሙሉ ከሰርኩኝና የሰው ገንዘብ እንዴት እንደምመልስ ቸገረኝ።” ብለው ኖሮ፥ እርግጠኛ ነኝ “እናዋጣለት” ባይልም ገንዘቡን መልሼ የማገኝበትን መንገድ ለመጠቆም ይሞክር ነበር።
‘እንዲህ ያለውን ነገር ብናሻሽል የተሻለ እንኖርና ኀዘናችንም ይቀል ነበር’ እላለሁ።
====
የአቡኪ ሞት ሰቅጥጦኝ ስባዝን ነው ‘randomly’ ይሄን ይሄን የማስበው።
ብልጭ ድርግም አለ። በወጣትነቱ ሄደ። ሞት አዲስ ሆኖ በመጣ ቁጥር ቢያስደነግጥም፥ ነገም እንዲሁ ነን እኛ።
ነፍሱን በአጸደ ገነት ያኑራት!

ልበ ቀናው ወዳጃችን ይህ ነበር። 😥