አምናለሁ… ይነጋል!

የሰው ደም ማየት አልችልም! መፈጠሬን ያስጠላኛል! ነስር ባቅሙ ቀኔን ይቀማኛል። ከስፖርት እንኳን ቦክስ አልወድም። ሁለት የማይተዋወቁ ሰዎች፣ ለመብት ትግል አይደለ፣ ለዳቦ አይደለ፣ ለጨዋታ ብለው እንኳን እንዲሁ ተያይዘው ሲተናነቁ ሳይ አልችልም። አቅመ ቢስ ነኝ! ደም ሳይ ያዞረኛል! (ይገርመኛል! እንዲህ ሆኖ እንኳን ትክክለኛው የወታደርነት ዲሲፕሊን ይማርከኛል። ‘ሳድግ ወታደር እሆናለሁ’ እል ነበር። እንደልጅ ምኞቴ ያላደረገብኝ አምላክ ይመስገን!)
 
ይኸው ብሎ ብሎ ስለሞት አሳሰበኝ። ሰው ከሥራ፣ ከተሳትፎዎች፣ ከስልጣን እና ከሌሎች ጉዳዮች ላይ ራሱን በገዛ ፈቃዱ እንደሚያሰናብት ሁሉ፥ በአግባቡ መኖር እና ማኖር ያልቻለ ሰው፥ ራሱን ከኑሮ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ የሚያሰናብትበትን ስነልቡና አሰላሰልኩት። ስለዘላለማዊ ሕይወት ተብሎ መስበክ ይቅር ይባል ይሆናል እንጂ፥ ብዙ ራሳቸውን ማጥፋት የሚገባቸው ሰዎች ንጹሐንን በግፍና በገፍ እያጠፉ ነው። ራስን ከሥራ ብቻ ሳይሆን፥ ከኑሮም ላይ ማግለል እና “በቃኝ” ማለት እንደሽንፈትና ራስ ወዳድነት ብቻ መቆጠር የሚገባው አይደለም። አንዳንዴ ከንቱነትን እና የራስን ጭካኔ ማሸነፍም ነው። ለራስ ክፋት እጅ መስጠት ነው።
 
ሰው እንዴት የሰው ደም ለማፍሰስ ከእንቅልፉ ይነሳል??? ሰው እንዴት የእለት እቅዱ ውስጥ “መግደልና መደብደብ” ይኖሩታል??? ሰው ሲያሰቃዩ ውለውስ እንዴት ያንቀላፋሉ?? ከዚህ ሞት አይሻልም?! ሺህ ዓመት አይኖር! ሀብት ንብረትም ያልፋሉ! የራስ ዛሬ ባይስተዋል፥ የአምባገነን ጎረቤት ትናንት እንዴት ይዘነጋል?? ድምጾችስ በታፈኑት ልክ እንደሚፈነዱስ እንዴት ሳያውቁ ቀሩ??
 
እናም እመኛለሁ…
 
ምንም እንኳን፥ ፍትህ ሳይፈጸምበት ወንጀለኛ እንደዋዛ እንዲሞት ባልደግፍም (አሁን የአቶ መለስ የተቀላጠፈ ሞት እንዴት እንደሚያንገበግበኝ! ነገር ዓለሙን ቆጣጥሮት፣ ሸሩን ተብትቦ ከነወንጀሉ፣ ፍትህ ሳይፈጸምበት ሄደ። ነፍስ ይማር!) ብዙ ባለስልጣናት የንጹሀንን ደም ማፍሰስ ካላቆሙ፣ እስርና ግድያውን አቁመው ለመነጋገር ካልቀረቡ፥ ራሳቸውን ከኑሮ ላይ እንዲያገልሉ እመኛለሁ። ከቤተመንግስት እና ዙሪያዋ ብዙ የራስ ማጥፋት (suicide) ወሬዎችን ብሰማ እመኛለሁ።
 
ወታደሩስ፥ ይሄ ሁሉ ሰው አደባባይ ወጥቶ ተቃውሞውን ሲያሰማና ጥያቄዎችን ሲያነሳ፥ እንዴት እንደ አንድ ኗሪ “ምንድን ነው?” ብሎ ላይጠይቅ ቻለ? ስለተባለ ብቻ እንዴት ይተኩሳል? የመንግስት ወዳጆችና ካድሬዎች ቢሆኑስ፥ የፈለገውን ያህል በሆድ ቢተበተቡ፣ ይህንን ሁሉ ግፍ እያዩ እንዴት ተቃውሞ አያሰሙም? ተቃውሞ ማሰማቱ ቢቀር፥ እንዴት አፋቸውን ሞልተው ለመንግስት ይከራከራሉ? አንድ ሰው የስንት አውቶብስ ዋጋ አለው? ቁስንስ የሚፈበርከው ሰላም ያገኘ የሰው ልጅ አእምሮ አይደለም? አንድ ሰላም ባስ ቢቃጠል ነጠላ አሸርጣችሁ “እዬዬ” ስትሉ የነበራችሁ፥ በሁለት ቀናት ከመቶ በላይ ሰው ሲገደል ምን ተሰማችሁ??
 
መቼስ ዝም ብለው ደም እያፈሰሱ፣ እያሰሩ እና እየገረፉ በሰላም መኖር አይቻልም። የንጹህ ሰው ደም ሰማየ ሰማያትን ሰንጥቆ ያስተጋባል! እስካንገት ደርሶም ያንቃል! በምድረ በዳ መቅበዝበዝም ገንዘባቸው ይሆናል! የጊዜ ጉዳይ ነው እንጂ፥ መልካምም ሆነ ክፉ ሥራ ዋጋውን ያገኛል!
 
አምናለሁ…. ይነጋል!!!
 
#Ethiopia #StopKillingCivilians #OromoProtests #AmharaProtests

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s