በትጥቅ ትግል አምናችሁ አባል የሆናችሁበት ወይም በተግባር የምትደግፉት ፓርቲ ለሌላችሁ ከኢትዮጵያ ውጪ የምትኖሩ ዲያስፖራ ወዳጆች… የኢትዮጵያ ምድር እንዲህ በደም እና በእንባ ቅይጥ እየታጠበች፣ ሰላማዊ ሰው እንደቅጠል እየረገፈ፣ ሰላም ፍለጋ የወጣው ሰው ደሙ ፈስሶ የትም እየቀረ፣….
“የአገሬ ወጣት ሆይ ስማኝ። ሀይልህ በእጅህ ነው። እንዳትመለስ። በለው። ፍለጠው። እስከመቼ ሲገድሉህ ዝም ትላለህ? በል ተራው ያንተ ነውና ግደል! ሊመታህ የመጣውን ቀድመህ ምታው።” ብሎ መምከር የምትጽፉትን ያህል ቀላል ነው? እንደኳስ፥ በስልክ ተቀርጾ በተላለፈ ‘ወጣቶች ከፖሊስ ሲሸሹ የሚታይበት’ ቪዲዮ ላይ፥ – “አዪ… በለው! በለው! ወደ ግራ፣ ወደ ቀኝ… ለምን ሸሸህ? ባትሮጪ እኮ ፖሊሱ ይስትሽ ነበር። ስለዚህ ዱላውን ትቀሚው ነበር።” ዓይነት የኮሜንታተር ሚና መውሰድ አይከብድም?
ያንን ለምን እዚያው በአካል ያለው ሰው እርስበርሱ አይባባለውም? ነው እንጂ፥ ልክ ነው ልክ አይደለም እያልኩ አይደለም። እነሱ ወደው ፈቅደው ሲያደርጉት “አታድርጉ” ማለት አይሆንም። ነገር ግን፥ የሁኔታውን ምስል ለመከሰት እንኳን ምቹ ባልሆነበት ርቀት ላይ ሆነው፥ እንዲህ ያለ አዝማችነት አይከብድም ወይ?
ሰው አገር ስትኖሩ፥ የአገራችሁ ጉዳይ ሥራ አስፈትቷችሁ፣ ቀኑን ሙሉ እሱን ስታስቡና ስታሰላስሉ ለመዋል እንደማትችሉ ግልጽ ነው። ረጋ ባለ ምድር ላይ ንጹህ አየር ስትተነፍሱ እና ስትንሸራሸሩ ውላችሁ፥ እንደ መደበሪያ ፌስቡክ ላይ ብቅ ስትሉ ብቻ…… “አትነሳም ወይ! ድል የሕዝብ ነው። ሕዝቤ ሆይ ስማኝ፥ ተጋፈጣቸው። አውሬዎቹ ቢገድሉህም ታሪክ ይፋረድሃል።” ብሎ የታጋይ እንቅልፍ መተኛት አይከብድም? ቀኑን እንዴት ነው የምታሳልፉት? ምሽቱንስ?
ደሙ ሲንዠቀዠቅ ፎቶ ተነስቶ፣ በማኅበራዊ ትስስር ድረገጾች ላይ ደሙ ደግሞ ደጋግሞ ሲፈስ የሚውለውን ሰው ፎቶ ከማጋራት ባሻገር፥ “ቁስሉን መጠገኛ።” የሚሆን እንኳን “ምን ላድርግ?” ሳይሉ፥ የሞተውንም እንዲሁ፣ ለቤተሰቦቹ ክብር ተብሎ እንኳን ፊቱ ሳይሸፈን፣ እንዲሁ ብቻ ከሩቅ ሆኖ እየተቀባበሉት ሆይ ሆይ ሲሉ መዋልና፣ እሱን ‘አክቲቪዝም ነው’ ብሎ ማለፍ ብቻ ከባድ አይሆንም?
እንዲህ ባለ ቀውጢ ሰዓት፥ የስጋ ወንድሞቻችሁ/እህቶቻችሁ ጋርስ ደውላችሁ “በሉ ሰብሰብ በሉ። አርፋችሁ ቁጭ በሉ። የወያኔ ሲሳይ እንዳትሆኑ። መቼስ እግዚአብሔር ያመጣውን እሱ እስኪመልሰው ድረስ።” ብላችሁ ታስጠነቅቃላችሁ? ወይስ እንደፌስቡኩ ሁሉ “አንተ ሽንታም! አትወጣም ወይ? ሂድና ግደል ወይም ለነጻነትህ ሙት” ብላችሁ ታጀግናላችሁ?
እሺ ይሄም ይቅር። ያላችሁ የነጻነት ጥማት “በለው በለው” ከሚለው ድምጻችሁ ውስጥ ፈልገን እንስማው። ታዲያ ግን፥ በትጥቅ ትግል ማመናችሁ ካልቀረ፣ እንዲህ በሩቁ “በለው በለው” ከማለት ቀረብ ብሎ ትግሉን መቀላቀል እንዴት አላሰባችሁም? ከፌስቡክ ታጋይነት ባለፈ ማለቴ ነው። ለምሳሌ፥ ወደአገር ቤት ሄዶ፣ ራሱን መስቀል አደባባይ ላይ አቃጥሎ ዜና እንዲሰራለት የማድረግ ዓይነት ታጋይነት? ወይ ደግሞ፥ ጠቅልሎ ሄዶ ባገኙት አጋጣሚዎች ሁሉ ከፌደራል ፖሊሶች ጋር ፊት ለፊት የመመታታት ዓይነት ታጋይነት? “ሽንታም” ማለቱ እንደሚቀላችሁ ሁሉ፥ የእናንተን ጀግንነት ደማችሁን እያፈሰሳችሁ ማሳየት?
እንደውም፥ ዲያስፖራው ሰብሰብ ብሎ ሄዶ ኢትዮጵያ ውስጥ ሰልፍ አድርጎ ሲተኮስበት ድንጋይ ወርውሮ የተወሰነው ደም ቢፈስ፣ ለሚዲያ ሽፋኑም ጠቅሞ ከፍተኛ የለውጥ ስትራቴጂ ሊሆን ይችላል እኮ! (አንድ ሰው ብቻውን ሰልፍ ቢያደርግ ትኩረት እንደሚስበው ሁሉ።) ለማታገሉም ቢሆን እንዲህ ከሩቅ ሆኖ አቅጣጫ ሲቀይስና አሰላለፍ ሲተች የነበረ ሰው ውጤታማ ሳይሆን አይቀርም።
ባጭሩ፥ ለምንድን ነው ወደ ኢትዮጵያ የማትሄዱት?? ምንድን ነው የቸገራችሁ? – የአውሮፕላን ቲኬት መግዣ?? እንዳትሞቱ/እንዳትታሰሩ ፈርታችሁ እንዳይባል፥ እዚያ የሚሞተውን ሰውም እየገፋፋችሁት ነውና እንደዛ አላሰብኩም። ማለቴ፥ ሕይወቱን ለነጻነት አሳልፎ ለመስጠት ዝግጁ ያልሆነ ሰው፥ እንዴት ሰዎች የራሳቸውን ሕይወት አሳልፈው እንዲሰጡ ከሩቅ ሆኖ ጥሪ ያቀርባል??
ሌላ በጣም በሚደንቅ ነገር ደግሞ አክቲቪዝሙን ስታደርጉ፥ አሁን ላይ እንኳን፥ “እኔ አገሬ መግባት እፈልጋለሁ ባክህ” ብላችሁ በራሳችሁ ስም ሳይሆን፣ በanonymous ስም የምትጠቀሙ መኖራችሁ ነው። ጥቃት መርሮት የወጣን ሰው ፎቶ ለአክቲቪዝም መጠቀም አግባብ ከሆነ፥ የራስን ስም ለአክቲቪዝም መጠቀም የሚከብደው ለምንድን ነው??
እንዲህ በትጥቅ ትግል እና በፈለገው ደም መፍሰስ ለውጥ የምትፈልጉ ከሆነ፥ አገር ቤት መግባት ምንም ዓይነት ስጋት አያጭርባችሁም መቼም። (ከለውጥ በኋላ የምትኖረውን የተረጋጋች አገር ከመናፈቅ ወይም ዓለም ከማማለሉ በቀር? ወይ ደግሞ ከምትወዷቸው ቤተሰቦቻችሁ የመለየት ስጋት?) ታዲያ ለምን አትመለሱምና ትግሉን አትቀላቀሉም? ይህን ለማድረግ ጠብታ ሀሞት ካጣችሁ ደግሞ፥ ወይ ደግሞ ኤርትራ ሄዳችሁ ግንቦት ሰባትን ለምን አትቀላቀሉም? …በነገራችን ላይ፥ ቢያንስ እነሱ ጋርስ አባል ናችሁ? በገንዘብ ትደግፏቸዋላችሁ? ወይስ እንደተለመደው “ሁሉንም ማቃለል! የዕለቱን እሳት አይቶ ማቀጣጠል!” ነው መመሪያችሁ?
ክብር አገር ቤት ሆናችሁ ለመብታችሁ እና ለነጻነታችሁ መከበር ቆርጣችሁ ለቆማችሁ፣ በምትችሉት ሁሉ ግፍን ለምትቃወሙ! የደማችሁ መፍሰስ በከንቱ እንዳይሆን፥ ፈጣሪ ያግዛችሁ! ሰላማችሁ ይብዛ!
ክብር ሰው አገር ሆናችሁ በምትናገሩት የለውጥ መንገድ ሁሉ በተግባር ለምትኖሩ!
#Ethiopia #EthiopiaProtests #OromoProtests #AmharaProtests #StopKillingCivilians