ስትቀልድበት አብሮ መሳቁ የልብ ልብ ሰጥቶህ ከሆነ እዚህ ያደረሰህ ተሳስተሃል። የሚጎዳውን እና የሚጠቅመውን መርምሮና ለይቶ ተገቢውን ምላሽ ይሰጣል እንጂ፥ የጉራጌ ማኅበረሰብ በንቃት (consciously) ኗሪ ነው። ለዚያም ነው ሥራን ካለመናቅና በኅብረት ከመንቀሳቀስ አንስቶ፣ ሰብአዊ መብቱን ተጠቅሞ፥ ገና ድሮ በየክፍለ አገራቱ ተንቀሳቅሶ እስከመኖር የደረሰው።
አርአያ የሚሆን የቁጠባ ባህሉም፣ በነጻነትና በስርዓት የመኖሩ ውጤት ነው። የዚያኑም ያህል ደግሞ፥ በየደረሰበት በፍቅርና በሰላም ተቻችሎ በመኖሩ ይወሳል እንጂ በክፉ አይነሳም። ባለማወቅ ቢያንጓጥጡበትና የሕይወት መመሪያውን ባለመገንዘብ ቢቀልዱበት፣ አብሮ እየሳቀ ዝም ብሏቸው ኖሮ፥ ውሎ አድሮ በክፉ በደግ ማንነቱን በሥራው ነው የሚያሳየው።
ግፍና ጭቆናን ማንም አይወድም። የበደልን ቀንበርም ማንም እስከዘላለሙ ችሎ አይሸከምም። የጉራጌ ማኅበረሰብም ሥራ የመውደዱን እና ሰላም የመሻቱን ያህል አምባጓሮ ውስጥ ራሱን ለማግኘት አይፈልግም እንጂ፥ “በሰላምና በሽምግልና ማኅበራዊ ችግሮቻችንን እንፍታ” ሲል እምቢ ብለውት ሲረግጡት ይረግጣል። ረግጬህ ልግዛህ ሲባል አሻፈረኝ ይላል። ሕግና ስርዓትን ዘርግቶም ባህሉን አክብሮ ኗሪ ነው።
በማኅበረ ፖለቲካው በጉራጌዎች የተደረጉ እምቢባይነቶች ሞልተዋል (እንዲህ እንደዛሬው ሰው በጎጥ ተከፋፍሎ ‘የአማራ’ ‘የጉራጌ’ መባባል ሥር ሳይሰድ በፊት፥ በ’ኢትዮጵያዊነት’ ስምና ስሜት። በአገራዊ አጀንዳ ‘የጉራጌ ተቃውሞ’ የሚባል ኖሮ አያውቅም። ያው ሀሳቡም መጤ ነው)። ከኢትዮጵያዊነት ጉዳዮች ባሻገር ከድል በኋላ ወደ ሥራ ስለሚሄድ፣ ታሪክም በባለጊዜዎች ስለሚመዘገቡ እንጂ ብዙ ታሪኮች አሉ። የተጻፈውም ቢሆን በበቂ ሁኔታ መስካሪ ነው። ፊታውራሪ ሀብተጊዮርጊስ ዲነግዴስ ጨቦና ጉራጌ አውራጃ አይደል ተወልደው ያደጉት! በየዘርፉ ዞር ዞር ብለህ ታዘብ፥ የሕይወት ታጋዮች ሞልተውልሃል፡
ከቤትህ ዙሪያ ልስማ ካልክ የአባቴ አባት በጣልያን ተሰቃይቶ መገደሉን እናቴ ትተርክልሃለች። ተተኩሶበት ሳይሆን፣ ተይዞ፣ ዐይኑ ተጎልጉሎ እና ሌላ ሌላም ስቃይ ደርሶበት መሞቱን የነበረ ያህል ታወራልሃለች። (አባቴ “ያኔ 12 ዓመት ብሆን ነው” ይላል።)
ልብ አድርግ! ስለአባቴ አባት ነው፥ እናቴ እሷ ሳትወለድ ስለሞተው አያቴ የተነገረውን ታሪክ የምትተርክልህ። እንጂማ አባቷም ቀላል አልነበሩም። ደርሼባቸው ከአንደበታቸውም ሰምቻለሁ።
“መድፍና መትረየስ ጥይት ሲጓረሱ
አሳላፊ ነበር የማሩ ገረሱ” ስለተባለለት ደጃዝማች ገረሱ ዱኪ፣ አባ ቦራ (አያቴ አገልጋዩ ሆነው አሳልፈዋል) እና ስለጀግኖች አርበኞች ተጋድሎ፥ የታሪክ መጽሐፍ ማንበብ ሳልጀምር በፊት ከእርሳቸው ነበር የምሰማው።
በቅርቡ ታሪኳ በሰፊው የተነገረላት ሴታዊት (feminist)፣ የቃቄ ውርድወትን ተመልከትና ያልተዘመረላቸውን ሌሎች ብዙዎችን አስብ። ‘አይ ዘመኑ ወዲህ ይቅረብልኝ’ ካልክ፥ የተደላደለ ኑሮውን ትቶ በረሀ የገባው ዶ/ር ብርሃኑ ነጋም አለልህ። (እንግዲህ ጉራጌ ጥርስ ከነከሰብህ፣ “ከፈለግክ ዱላም እንማዘዝ” ካለህ፥ ምን ክፉ ብትሆን እንደሆነ ራስህን መፈተሽ ነው።) “ቆይ እስኪ እንየው” ብሎ ተስፋ ባለመቁረጥ በሰላም የሚማጸን ከፈለግክ ደግሞ፥ ዶ/ር ያዕቆብ ኃይለማርያም ይጠቀሱልሃል። (እንግዲህ ልብ አድርግ፣ ጫፍ ጫፉን ነው የማወራልህ። መሀል መሀሉን ገምተው።)
ወዳጄ፥ አለማወቅህንማ በከንቱ ዘለፋ አትጋርደው!
Stop your racist remarks against the Gurage people!, or die now with it!
#Ethiopia #StopKillingCivilians