እናፍቃለሁ… የውዳሴ እና የምስጋና ግጥም የምጽፍለት መሪና ስርዓት እንድናገኝ። እኩል ተወዳድሬ የምሰራበትና፣ በታማኝነት “ይኸው ይሄን ያህል ገቢ አገኘሁ። ተመኑን ቁረጥና አገሪቷን አቅናበት፣ ሕዝቡን አንቃበት።” ብዬ የምገብርለት ስርዓት፥ ካፌ ቆጥቤ በሰጠሁት ብር ዱላና መሳሪያ ገዝቶ፤ በጠራራ ፀሐይ በ“ለምን አየሁህ” ደምፉ፣ ሕዝብ የሚደበድብበት ወግ የሚቀርበት ቀን ይናፍቀኛል።
በሰላም ወጥቶ መግባት፣ በስርዓት መኗኗሩ፤ …ማንበብና መጻፍ መቻሌን ማማረር፣ ማየትና መስማቴን መራገም የማቆምበት ቀን፤ …በገዛ መኝታ ቤቴ ስነቃ፣ በገዛ አገሬ ጎዳናዎች ስራመድ እንግዳነት የማይሰማኝ፤ …በነጻነት ስሜት፣ የነጻነትና የፍቅር ግጥሞችን ብቻ የምጽፍበት ቀን ይናፍቀኛል። ጥበቃዬ ከዳር ደርሶ፣ መገናኘትን ማንቆላጰስና፣ የሰው ልጆችንና መኖርን ማወደስ እናፍቃለሁ።
ያረገዘች በሰላምና በጤና የምትገላገልበት፣ የተወለደ የሚያድግበት፣ ያደገም የነፍሱን መሻት የሚከውንበት፣ ሰው ተምሮ የሚያገለግልበት፣ በስተርጅናም በክብር ቆይቶ በደስታ የሚሰናበትበት ኑሮ እናፍቃለሁ። ፅዱና አረንጓዴ አዲስ አበባና ሌሎች ክፍላተ አገራት… ተመጥኖ በተሰጣት ቀንና ማታ ለ13 ወራት በጸሐይ አሸብርቃ፣ መስከረም ሲጠባ አደይ አበባና የመስቀል ወፍ የሚያጌጡባት ዘረኝነት ያላጠቃት ኢትዮጵያ ትናፍቀኛለች። ወጣቶች በተስፋ መቁረጥ የማይኖሩባት፣ እናቶች ለልመና የማይወጡባት፣ ህጻናት በየጎዳናው የማይበተኑባት አገሬ ትናፍቀኛለች።
ይገርመኛል፥ “መጽሐፎችህ ጨለምተኞች ናቸው” ሲሉኝ፤ “ግጥሞችህ፣ እንዲሁም ፌስቡክ ላይ የምትለጥፋቸው ጽሁፎች ጨለምተኞች ናቸው።” ሲሉኝ። ኑሮዬን የሚያውቁት ይመስል ቀለምና የብርሃን ዓይነት ሲመርጡለት ሳይ ይገርመኛል። “እንዲህ አጠቋሩረኸው ስታበቃ “የብርሃን” ማለትህ ሽሙጥ ነው?” ይሉኛል፤ …ብርሃን መውደዴን፣ ብርሃን መናፈቄን ሳያውቁ። ሀሳቤን መግለጼን እንጂ፥ መንጻት፣ መጥቆራቸውንስ አውቃለሁ? ብርሃንን መተረክስ አይቀልም?
ደግሞ “ጆ ሁለቱንም መጽሐፍቶችህን በ3 ዓመታት ልዩነት ልክ ግንቦት 8 ያደረግከው ለምንድን ነው?” ተብዬ ለብዙኛ ጊዜ ተጠየቅኩኝ። ባጋጣሚዎች ሳልመልሰው ያልፋል። ምክንያቴን የልደት ቀኗ ግንቦት 8 ለሆነችው ወዳጄ Kal Kidan ብቻ ነበር ነግሬያት የማውቀው። “የ1981 ዓመተ ምህረቱ መፈንቅለ መንግስት ናፋቂ ሆነህ ነው እንዴ?” ብሎ ያስፈገገኝም አለ። ዛሬ ላውራው እስኪ…
“ብርሃን ብርሃን” ማለቴ፣ መጽሐፎቼን ግንቦት 8 ለማስመረቅ መፈለጌም፥ በግንቦት 7 ቀን፣ 1997 ቁጭት የተደባለቀበት ትዝታ ነው። ብርሃን ናፍቄ ነበር። ‘ምርጫው ለውጥ ያመጣልናል፣ ከዴሞክራሲ ጋርም ያስተቃቅፈናል’ ብዬ፣ በከፍተኛ መጓጓት እና መቁነጥነጥ ውስጥ ሆኜ ነበር ደርሶ ማለፉን የምጠብቀው። ሰው ለመምረጥ እንደዚያ ይስገበገባል?? (ዴሞክራሲ ግን ለምን የማናውቀው ቦታ የሄደብንና መምጫውን የማናውቅ ዘመድ ይመስለኛል?)
የግንቦት7 ማግስት…ግንቦት 8ን ለብስራት ነበር ያለምኳት፤ ለለውጥ እና ለነጻነት ግጥሞች ነበር ተስፋ ያደረግኳት፤ ለመተቃቀፍና በደስታ እንባ ለመራጨት ነበር ያሰብኳት። የብርሃን ነዶዎች ዙሪያዬን እየከበቡ ያቃዡኝ ነበረ። በኑሮዬ ጣሪያ ቀዳዳዎች ሾልከው ሾልከው ወለል ላይ የቆሙ የብርሃን በትሮች፥ የተስፋ ምርኩዝ ሆነውኝ ያጽናኑኝ ነበረ። እንደ“ይቺን ብላ! ዶሮ ማታ”… ‘ሲነጋ ባህሩ ይከፈልልንና ተሻግረን አገራችን እንገባለን።’ እል ነበር ለራሴ።
ፍትህ ተከብሮ፣ ሰዎች ዋጋ እንደተከፈለባቸው በክብር ሲኖሩ እየታየኝ ብቻዬን ያስወራኝ እንደነበረ የትናንት ያህል ትዝ ይለኛል። እኩል፥ ልቀላቀል የምችለው ከሙስና የፀዳ የሥራ ዓለምና መመረቄም ይናፍቁኝ ነበር። በልቤ፥ የምጽፋቸውን የደስታ ግጥሞች እያሰብኩ በቀብድ ‘poegasm’ ላይ ደርሼ አውቃለሁ። …ይናፍቁኛል እነዚያ ጊዜያት! ወደው የማያገኙትን ሰው ሲጠብቁ፥ ቁርጡ ቀን ባያልፍ ያስሸልላል። የወዳጅ ዘመድ “አይዞህ”… “እየጠበቅኩ ነው” የማለት ማጽናናት ጫፍ ላይም አይደርስም።
ሲነጋ ግን እንዳይሆኑት ሆኖ ዛሬም ድረስ “እህህ” እያስባለን ያለ ነገር ተከሰተ። ጭራሽ 5 ዓመት ተቆጥሮ ጉድ አፍርቶና ጎምርቶ “100% ተመርጠናል” ብለው አረፉት። ይኸው ቀን ጠብቆ የታፈኑ ድምጾች በየቦታው ስርዓቱን ሲያወግዙ ተሰሙ። ምላሹም “እንካ ቅመስ” ሆነ። በጸሐይ ደም የትም ፈሰሰ። እስሩም ድብደባውም በገፍ ሆነ።
ሆኖም፥ “ኧከሌ ታሰረ” ሲባል፥ “አርፎ አይቀመጥም ነበር።” ይሉ የነበሩ ሰዎች ዐይናቸው ተገለጸ። “እነ ኧከሌ በጸረ ሽብር አዋጁ ክስ ተመሰረተባቸው” ሲባል “የሆነ ነገር ሳያኖርማ…” ይሉ የነበሩ ሰዎች ከእውነታው ጋር ተፋጠጡ። “ፖለቲካና ኤሌክትሪክ በሩቁ” የሚሉ ወዳጆች፥ በግድ ዙሪያቸው ስለሚከናወነው ነገር ማወቅ፣ መጠየቅና ምሬትን መግለጽ ጀመሩ። የጭቆና መብዛት፥ የግዱን የነዋሪዎችን ዐይን ይገላልጣል።
ይኼ እንደ ጥሩ ጭላንጭል ኾኖ ያጽናናል እንጂ፥ የተደረገብን ነገር፣ ለመናገር ያከብዳል። ዝም ለማለትም ይጨንቃል። መናፈቅ ግን አይከለከልም! …ዛሬም ብዙ ብዙ ነገር እናፍቃለሁ! ጊዜና ባለጊዜ አልፈው፥ እንደምርጫ 97 ተስገብግቤ ቀበሌ ሄጄ የምመርጥበት ሰልፍና፣ በልቤ ስዬው እንደነበረው ዓይነት የምርጫ ማግስት እናፍቃለሁ!
አንሙትማ!