ሰማዕቱ እርገጤ…

አንድ ፍሬ በቅሎ ምድርን ያመሳት፣
እርገጤ ነበረ፥ ‘ሰይጣን በከረባት’
አካባቢው ላይ ውስጥ ውስጡን የነበሩ “እድሩ ይፍረስ ” የሚሉ ድምጾች በይፋ መሰማታቸው ቀጠሉ። የእድሩ አመራሮችም ሥራ አስፈጻሚ አባላቱን በጥሩንባ እና በመሰል የእድሩ ጯኺ ንብረቶች ታግዘው፣ የቀዬውን ጆሮ ከማዘናጋት አንስቶ በሚቻለው ሁሉ ነገሩን ማለባበስ፣ አፎቻቸውን ማበስ እንደሚኖርባቸው ትዕዛዝ ሰጥተው ደፋ ቀና ይላሉ። እድርተኛውን ያነቃው ‘የጎረቤት እድሮች፣ የሰርግ እቃ አከራዮችና የሰርግና ምላሽ ወጣኞች ሴራ ነው’ እያሉም ያወራሉ። ይህን ያህል ንቀውታል!
 
በየቦታው “እድሩ ብዙዎችን ቤት አልባ አድርጓል፣ መዝገብ ያዥነትና ጥሩንባ ነፊነት እንኳን ሥራ ማስያዝ ባለመቻሉ ሰዎች ከቀዬው እየተሰደዱ ነው፣ ግማሾቹም በእስርና በተስፋ መቁረጥ ነው ያሉት። ከጥሩንባ ነፊዎቹ በቀር አፋችንን ለጉሞናል። ድንኳን ጥገናውና ምስር ለቀማው ሳይቀር በወገንተኝነት እና አባላት ለእድሩ ባላቸው አቋም የተነሳ ነው የሚሰጠው፣ የእድሩ ቋንቋ ተናጋሪዎች የአመራር ቦታዎቹን መያዛቸው ሌላውን ጎድቶታል፣ የእድርተኞቹን የማንነት ጥያቄና የዝምድና ሁኔታ በአግባቡ አልመለሰም፣ ወላ የአባላቱን ሚስቶች አመራሩ ካልወሸምኩ ይላል፣ እድሩን ወደ አንድ ቤተሰብ የመውሰድ አዝማሚያ ይታይበታል፣ ወዳጆቻችን ለእድሩ እድሜ መርዘም ተብሎ እየተገደሉና እየታሰሩብን ነው። እድሩ ሞታችንን እንጂ ሌላ ምንም አይፈልግም። በየለቅሶ ቤቱ የፍራሽ ተሰብስበን ስንቀመጥም መከልከል ጀምሯል። ይፍረስልን!” የሚሉ መልእክቶች ይስተጋባሉ።
 
ከቁጩ ባለራዕዩ ኮሚቴ ደግሞ “የእርገጤን ራዕይ እናስፈጽማለን። ከምንግዜውም በላይ የእርሱን አደራ ተቀብለን ብዙ ሰዎችን በመግደል የእድሩን ህልውና ማስጠበቅ ያለብን ሰዓት ላይ ነው የምንገኘው። ትምክህተኛ እና ጠባብ እድርተኞችን ሳንሰማ በምንታወቅበት የጭካኔ እና የግድያ ሞያ ላይ አቅማችንን ማረጋገጥ ይኖርብናል። ፍትሀትና የቀብር ፀሎት ፈጻሚ የሀይማኖት አባቶችን በሾርኒ ልከን ከአባላቱ ጋር ሰላም የተፈጠረ በማስመሰል አዘናግተን እንዳይለመደው አድርገን እናዳፍነዋለን።
 
ስህተት እንዳንሰራ! በሰላም መፍታት የእኛ እድር ባህል አይደለም። የእርገጤ አጥንት ይወጋናል። እርገጤ በእኛ ዘንድ በተሰጠው የቅዱስነት ማዕረግ የተነሳም አባላቱ ‘ተገለጠ’ ቢባሉ ስለሚያምኑ በጥሩንባ ነፊው በኩል በወቅቱ ሁኔታ ላይ ንግግር አደረገ ብለን እናሰራጫለን። እንግዲህ አመራሩ ከሌለ እድሩ ይፈራርሳልና ለራሳችን ብለን መንቀሳቀስ አለብን። እድሩ በቀብር ስራ ሲጠመድ ሁሉም ቦታ ቦታው ይገባል።” በማለት ተነግሮ ለተግባራዊነቱ ዋተቱ።
 
* * *
 
ሲተኮስ አድሮ ዋለ።
 
ከእድርተኞች ወገን
 
ብዙ ሰው ሞተ!
 
ብዙ ሰው ቆሰለ!
 
ድምጹንና ዋይታውን የሰማ ብዙ ሰው ተነሳ!
 
እኔ በክላሲካሉ ታጅቤ እንቅልፌን ተኛሁ።
 
ከአመራሮቹ ወገን ደግሞ ከመግደልና ከመደብደብ ከተረፈ ጉልበት፣ ለድግስ ሲተራመስ ነው ያደረው። ድስቱ ሲንጋጋ፣ ጭሱ ቤቴን ሲያውደው ልስማ እንጂ ምን እንደሆነ አላወቅኩም ነበር።
 
* * *
 
“ተነስ ዛሬ ስራ የለም። እርገጤ የዓመት ናቸው! እስኪ ደጃቸውን ስመን እንምጣ።”
 
“የምን ደጅ… ” አልኩ በእንቅልፍ ልቤ።
 
“የሰማዕቱን እርገጤ ነዋ። ተነስ በረከታቸው ያድርብናል።”
 
“አድሮብን የለ? ብዙ ሞቶ፣ ብዙ ቆስሎ አደርን እኮ።”
 
“እርገጤ ይገስጹህ!” ብላ ሽጉጧን ስትፈልግ ተነሳሁና ጥቁር ልብስ ሳጣ ያገኘሁትን ለብሼ ወጣሁ።
 
መንገድ እንደጀመርን ስለሰማዕቱ የሰማሁት ትዝ አለኝ። እሳቸው በሞቱበት ቀን ነጭ የለበሱ ‘መናፍቃን’ ላይ የሆነው ትዝ አለኝ። ነጭ የማንለብስበት የእርገጤ ንግስ ቀን መሆኑ ትዝ አለኝ። በራዕያቸው መሰረት የሚፈስ ደም ፈልጌ ልብሴን አቀለምኩትና እፎይ ብዬ ከምዕመኑ ጋር በቀይ ተቀላቀልኩ።
 
* * *
 
አቶ እርገጤ በአንምባገነንነታቸው የታወቁ የእድሩ ዳኛ ነበሩ።
 
ሰዉን ሁሉ ሰጥ ለጥ አድርገው ገዝተው መዋጮዎችንና ድጎማዎችን ያሰባስቡ ነበር።
 
ምላሳቸውም ረጅም ስለነበረ ነገሩን ሁሉ አሳስረው ቁጭ ያደርጉታል።
 
ሲገድሉ፣ ሲያስሩ፣ ሲያባርሩ፣ ሲያቆስሉ፣ ሲያስለቅሱ፣ ገንዘብ ሲሰበስቡ… ኖረው ኖረው፣ ከዕለታት ባንዱ ቀን እንደማንም ሞቱ ተባለ።
 
ሰፈሩ በዋሽንት ዜማ ደነቆረ።
 
ሁሉም እየወጣ ደነከረ።
 
የለቅሶው ጉብኝት እስከ ግምጃ ቤት ድረስ ክፍት ሆኖ ነበር። የለቅሶ አዋጅ ተጠርቶ ግማሹ የሞተበትን እያሰበ፣ ግማሹ ኑሮውን እየሳበ፣ ቀሪው ደግሞ ዝም ብሎ በማስመሰል ደረቱን ደቃ። ፀጉሩን ነጨ። እንባ ረጨ። በእድሩ የተረሳው ሁሉ “እኛን ለማን በትነውን?” ብሎ አለቀሰ።
 
ዓመት ተከበረ።
 
2 ዓመት ተዘከረ።
 
3 ዓመት ተጨፈረ።
 
4 ዓመት ተደነከረ።
.
.
.
እድሩ ፈርሶ መንፈሳቸው በገዳይ አመራሮች ላይ አደረ። ራዕያቸውን ወንጀለኞች
ወረሱት። ሽፍቶች ይዘውት በየጫካው ገቡ።
 
* * *
 
እግዜር ነቀለዎ፣ ቁርጥ ቀንዎ ደርሶ፣
ሰምሮልዎት ሳያዩ፣ አንድነቷ ፈርሶ፤
ስር እየሰደደ፣ ሕብረቷ ታድሶ፥
ሲረግጧት ኖራለች እንኳንስ ያለርሶ፤
የበተኑት ክፋት፣ የዘሩት አብቅሎ
ደም ሲያላቅስ አለ በየደጁ ሾሎ፤
ራዕይውንማ ሰይጣንም ይጽፋል
መተኮሱንማ ሽፍታም ይተኩሳል፣
ሞቶ አልሞት ያለ ግን እንደርስዎ የታል?
ዓለሜ ነበረ፣ እልል በቅምጤ
ከስር ተመንጉሎ ቢነቀል እርገጤ።
በሚል እንጉርጉሮ ታጅቦ ሰፊው ሕዝብ አመራር ዘመዶቻቸው ከጻፉት ገድል ላይ መርጦ ገደላቸውን ያነባል። በደላቸውንም በልቡ ይጽፋል።

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s