ኢትዮጵያ ለታንዛኒያ 400 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል ለመሸጥ የሚያስችል ስምምነት ልታደርግ ነው
አዲስ አበባ ነሀሴ 20/2008 ኢትዮጵያ ለታንዛኒያ 400 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል ለመሸጥ የሚያስችል ስምምነት ልታደርግ ነው።
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈፃሚ ኢንጅነር አዜብ አስናቀ ለኢዜአ እንደገለጹት ሁለቱ አገሮች የሽያጭ ስምምነቱን በሚቀጥሉት ሳምንታት ያከናውናሉ።
ኢትዮጵያ ለታንዛኒያ የምታቀርበው የኤሌክትሪክ ሃይል በኬንያ በኩል የሚያልፍ በመሆኑ በኬንያና ታንዛንያ መካከል የሚደረግ ስምምነትም እንዳለ ገልጸዋል።
ከኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ኃይል ገዝተው መጠቀም የጀመሩት ሱዳን፣ጁብቲና ኬንያም ተጨማሪ ኃይል መጠየቃቸውን ኢንጅነር አዜብ ተናግረዋል።
አገራቱ ከውድና አካባቢን ከሚጎዳ የሃይል አጠቃቀም ይልቅ ኢትዮጵያ የምታመርተውን ታዳሽ ኃይል ለመጠቀም ያላቸው ፍላጎት እየጨመረ መሆኑን ገልጸዋል።
በቀጣይ አረጋቱ የጠየቁትን የኃይል ፍላጎት ለማቅረብ ተጨማሪ መስመሮችና የማከፋፈያ ጣቢያዎችን ለመሥራት ጥናት እየተደረገ መሆኑንም ጠቁመዋል።
እንደ ኢንጂነር አዜብ ገለፃ 200 ሜጋ ዋት ኃይል ፍላጎት ላላት ኬንያ ኃይል ለመስጠት የመስመርና የማከፋፈያ ጣቢያ ግንባታ ፕሮጀክት ተፈርሞ ወደ ሥራ ተገብቷል።
ኢትዮጵያ ለጎረቤት አገራት እያቀረበች ያለችው የኤሌክትሪክ ኃይል የአገራቱን ኢኮኖሚያዊ ግንኙነት በማጠናከርና የልማት ትስስሩን በማፋጠን ላይ ይገኛል።
ግንባታው በቅርቡ የተጠናቀቀውና 1 ሺህ 870 ሜጋ ዋት ሃይል የማመንጨት አቅም ያለው ጊቤ ሦስት ሃይል ማመንጫ አሁን ላይ 900 ሜጋ ዋት እያመነጨ ነው።
በአሁኑ ወቅት ጊቤ ሦስትን ጨምሮ በአገሪቱ ያሉት ግድቦች የሚያመነጩትን አቅም ለመጠቀም የሚያስችል የሃይል ማስተላለፊያ መስመሮችና ጣቢያዎችን አቅም የማሳደግና አዲስ የመዘርጋት ሥራ በመከናወን ላይ ይገኛል።
ታላቁን የህዳሴ ግድብ ጨምሮ በግንባታ ላይ ያሉ ሌሎች ፕሮጀክቶች ሲጠናቀቁ ኢትዮጵያ ለሌሎች አገራት የምታቀርበው ኃይል እንደሚጨምር ይጠበቃል።
ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ቀንድ ባሻገር ሩዋንዳና ብሩንዲ ለመሳሰሉ በጣም ውድና ታዳሽ ያልሆነ ኃይል ለሚጠቀሙ አገራት እንዲሁም ለሰሜን አፍሪካ፣መካከለኛው ምስራቅና አውሮፓ የማቅረቡ ዕቅድ አላት።
ታንዛንያ ከጅቡቲ፣ሱዳንና ኬንያ በመቀጠል ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሃይል የምታገኝ አራተኛዋ አገር ትሆናለች።