ህም!…ከምላስሽ ጸጉር!

ምን ያል እንቆቅልሽ ነው? ምን ያለ፥ የጊዜ ታ’ምር?
ካንድ ገጽ ላይ የሰው ልጅ፥ ልዩ ልዩውን ‘ሚቆፍር?
በመሳ የኑሮ መስመር፣ ያልሰፈረውን ሚያማትር?
እንደምን አስፈነደቀው፥ አንዱን ያስነባው መከራ?
ሌላውን “በለው” አስባለው፥ ለእናት የተባለ ሴራ?
 
እንደምን ሜዳ መሰለው፥ ለአንዱ የኾነው ተራራ?
ሜዳውስ እንዴት ዳገተ፥ እንደምን ታይቶ ተፈራ?
ዳገቱስ እንዴት መደደ፣ ገዳዩን ሽምጥ አስኬደ?
የጠላው ሰው ተሸልሞ፣ ወዳጅ እንዴት ተዋረደ?
 
ክቡር ሰውነት ለዓለሙ፥ እንደምን ላንዱ ቀለለ?
አንዱን ባስጨከነው ግፍ፣ እንደምን ሌላው ዋለለ?
 
የወገኑን ደም ሊያጎርፍ፥ እንደምን ወገን ታጠቀ?
ገላ ገላውን ሊወጋ፥ ምን ቢያዘው ጦሩን ሰበቀ?
 
ደም አይቶ አቅሉን የሳተው፣ ለለቅሶ እየማቀቀ፣
እንደምን ወገኑ ችሎ፥ ሰማዩ ዝቅ እስኪል ሳቀ?
 
አንዱን ያረገፈው አተት፣ አንዱን ያሻመደው መተት፣
እንደምን ሌላውን ጋርዶት፥ አለባብሶት ዋለ ኮተት?
 
ይኽ ነው ችሮታሽ በቃ?
ለታማኝ ልጆሽ ውለታ? ዘግኖ ማሸከም ሲቃ?
ይኸው ነው እናት ዓለም፥ የቃልኪዳንሽ ቀለም?
ገዳይ ደምቆ ሟች ሊለቀም?
ወዳጅ አመዳይ ለብሶ፣ ባንዳ በልዩ ሲቀልም?
በዋይታ ቤትሽ ሲያጣጥር፣ “እህህ” ወገን ሲታመም?
 
አይሆንም!
ህም!…ከምላስሽ ጸጉር!
 
አይኖርም ቀኑ ቆፍንኖ፣ ይነጋል አይቀርም ዳምኖ፥
ጠቋቁሮ ዶፉን ያዘንባል፣ ለጠላት መከራ ጭኖ፤
ያድጠዋል የቆመበት፥ ጽዋው ሲፈገነፍል ሞልቶ፣
ዋጋውን ያነሳል ዋትቶ፣ ትፍግፍጉ አየር ጠርቶ
ይመዘናል በሚዛኑ፥ ተቅበዝብዞ፣ ተንከራርቶትቶ፣
በግፍ ሲያድል እንደኖረ፣ በየምድረበዳው ዋትቶ፤
 
ወገን ሳይደግፍ ሳያቀና፣ አይቀር የሰው ገላ ጎብጦ፣
ሰውነትን ሳይገነባ፣ አይቀር የሰው ስጋ ቀልጦ፣
ላያወዛ ላያሳምር፣ አይቀር የንጹህ ደም አጥጦ፣
በኩራት ላያስጎማልል፣ አይቀር የቻይ ገላ ተረግጦ፤
 
ቃል ነውና!
ፋሽስት ቅሌቱን ሊረከብ፥ ከሰጠበት እጥፍ ቁና፣
አሸባሪው ተሸብሮ፣ ሕይወት በመልካም ሊቀና።
 
ህም!…ከምላስሽ ጸጉር!
 
/ዮሐንስ ሞላ/