መንግስት ቢኖር…

የምር መንግስት ቢኖረን ኖሮ፥ ይህኔ በሬድዮና በቴሌቪዥን የሚታጀብ፣ ሰንደቅ ዓላማ ዝቅ የሚደረግበት ብሔራዊ ኀዘን ላይ ነበርን። ግን ያው፣ ሕዝቡ ራሱ ብሔራዊ ሐዘን ተጠራርቶ ቁጭ ብሏል።
 
“የገደለው ባልሽ
የሞተው ወንድምሽ፣
ሐዘንሽ ቅጥ አጣ
ከቤትሽ አልወጣ” ሆኖ አላመች አላቸው እንጂ፥ ለራሳቸው ፍጆታ ሲሉ እንደከዚህ በፊቱ ሁሉ እኛ የጠራነውን ብሔራዊ ሐዘን ያዳምቁ ነበር።
 
አሁን እንደው የመለስ ሞት በምን ሚዛን ተሰፍሮ ነበር፣ “በመንግስት ጥበቃ ስር ናቸው።” ተብሎ ሲታሰብ፣ በጥይት እና በእሳት ተጠባብሰው ከሞቱ ወገኖች ልቆ በዋሽንት ስንደነቁር የነበረው? ሲሆንስ አዲስ ዓመትን ጠብቆ እስረኞችን መፍታት የሚጠበቅ ነበር።
 
እሺ እሱም ቅንጦት ሆኖ ይቅር። የቤተሰብን ልብ ሰቅሎ ማሰቃየት ምን ይባላል? ባገራችን ደንብ እንደው የሰው ክቡርነት በሞት ደምቆ ይገለጻል። እርም ሳይወጣ ምግብ አይበላም። የከፋ ቅያሜ ቢኖር እንኳን አስከሬን ቆመው ያሳልፏል።
 
የሟች ወገኖች እናቶች እንዴት ሆነው ይኾን? የእናት እና የልጅ ተፈጥሯዊ ትስስር ጥልቅ ስለሆነ፥ የሞቱት እስረኞች እናቶች ይኽኔ ቁርጡን ሆዳቸው ይነግራቸዋል። (እናቴ በሌለሁበት ጠንከር ያለ እንቅፋት ቢመታኝ ታውቃለች።)
 
ታዲያ ግን ምን ብለው “ልጄ ሞቷል” ብለው ለቅሶ ይቀመጡ? ስሜቱን የማያውቅ ሰው እንደአሟራች ቢቆጥራቸውስ ይፈረድበታል። ምን ብለውስ “ልጄ ደህና ነው” ብለው ይረጋጉ። ስሜቱን የማያውቅ ሰው እንደግብዝ ቢቆጥራቸውስ ይፈረድበታል? ልጆቻቸው ሞቱ/ኖሩ ቁርጡን ሳያውቁ እንዴት ያንቀላፋሉ? ወዳጅ ዘመድ ጓደኛስ እንዴት እህል ይወርድለታል?
 
ሕዝብ በመንግስት በዚህ ልክ ይጠላል? “የድሃ ድሃዎች” አሉ ቃል ሲያሳምሩ እና ወሬ ለመቀሸር ሲሯሯጡ።
 
የክፉ ክፉዎች!!
 
ሕዝብ
——-
የእምቧይ ድርድር ካብ፥ እሾህ የማያጣ፣
ንጉሥ ሲደብረው፣
¬ ጭቃ ሹም ሲከፋ፣ ባለሟል ሲቆጣ፣
እንኳን ወሬው ቀርቶ፥ ዝምታው ‘ሚያስቀጣ፤
 
ኩራቱ ‘ሚያስጨንቅ — እንደ እመቤት ኩርፊያ፣
መቻሉ ‘ሚያስገፋ፣ ‘ሚያስደምር ከትቢያ፤
 
ወንበር ‘ሚያነቃንቅ፥ — የሰላሙ ዜና፣
መንግሥት የሚያሸብር፥ — የነፍሱ ጽሞና፤
 
ሳቁ ‘ሚያጠራጥር፤ ትንፋሹ ‘ሚያስገምት፣
እርምጃው ‘ሚለካ፤ ሩጫው ‘ሚያስፎትት፤
 
ሕዝብነት—
— ከንቱነት!
 
/ዮሐንስ ሞላ (2005) የብርሃን ልክፍት/

የንፍገት ጥግ

ከእለታት ባንዱ ቀን አምባገነን ገፍተው፣ ከጫካ ብቅ አሉ… ለመላ ለዘዴ፥ በሽለላ ብዛት፣ በዲስኩር ጋጋታ፣ ባዋጅ አጥር ብዛት፥ የሚሻል መሰሉ… ‘ዴሞክራሲ ሰፍኗል፣ ተናገሩ… ጻፉ፣ ተከራከሩ’ አሉ…
 
ገና በማለዳው፥ እንኳን የጻፈውን፣ ሊጽፍ ያሰበውን በፀረ ሽብር ህግ በቁም አሸበሩ… ‘በሽብርተኝነት ጠረጠርኩኝ’ ብለው ማለፊያውን ለቅመው፣ ሰብስበው አሰሩ፣…. ለተጠርጣሪው ሰው ማስረጃ ፍለጋ፣ ማስረጃ ቅመራ ላይ ታች ተባረሩ… በሰማይ በምድሩ ቧጠጡ፣ ዳከሩ… ወለሉን ቆፈሩ፣ ግድግዳውን ጫሩ… አልበቃ ብሏቸው ጊዜ ለፈጠራ፣ ለክስ ቅሸራ፥ በቀጠሮ መዓት፣ ገነቡ ተራራ… በእግረ ሙቅ እጅ አስረው፣ ከሰሩት አቀበት እያመላለሱ፣ አሳዩ መከራ…
 
ሲኖሩ ሲኖሩ…
ከእለታት ባንዱ ቀን፥ ‘እሳት ተነሳ’ አሉ ከእስር ቤት ምግብ ቤት… ‘ሊያመልጡ ሲሉ ነው’ ብለው በመተኮስ፣ የቻሉትን ጣሉ… አማራጭ በማጣት፣ የቀረውም ሸሸ ወደ ላንቃሙ እሳት… ‘ይህን ያህል ሞተ’ ተብሎ ተወራ፣ ከተጠቂውና ካጥቂው መንግስት ጎራ፣ ተዛብቶ ቆጠራ… ‘ከሞቱ ተረፉ’ የተባሉትንም ጭነው አጋዟቸው እስር ቤት ቀየሩ… በቤተሰብ ለቅሶ፣ በወዳጆች ዋይታ ታፈነ አየሩ… ቆዘመ መንደሩ…
 
ሳይነገር መርዶ… አስከሬን ሳይሰጥ… ከጥቃቱ የዳነም እንደተጨነቀ ሰላሙን ለማውራት… ተቆጠሩ ቀናት… ‘ቄሱም ዝም፣ መጻፉም’….. እርም ሳይወጣ፣ ያለው ሳይታወቅ ልብ እንደሰቀሉ… ‘አገሩ ሰላም ነው… በእውቀት ተቃወሙን’ ብለው አላገጡ፣ የቀለም ቀንዶችን፥ የቻሉትን አስረው፣ የቻሉትን ገፍተው እንዳላቀለጡ።
 
#Ethiopia
 
ምንም እንኳን የማውቃቸው ታሳሪዎች ባይኔ እየዞሩ እረፍት ቢነሱኝም፥ በሀቅ ሲመዘን ተጎጂው ሁሉ እኩል ነው። እግዚአብሔር ለተጨነቁትና ላዘኑት ሁሉ ብርታት ይስጥ። መርዶአቸው ባይሰማም፥ የሞቱትም በሰላም ይረፉ! የሰማዕትነትን አክሊል ያቀዳጅልን!

መስከረም ሳይጠባ!

እግዜር ኀዘን ስፈር፣
እግዜር አልቃሽ ቁጠር
አስለቃሹን መዝግብ፣
በግርማ መንግስትህ
እግዜር ዋይታ ዘግብ፣
መከራውን አስብ፤
 
እግዜር ለቅሶ ለካ
ያልቃሹን ዐይን ንካ፣
ዳብሰው በመዳፍህ
አፍርስ ንቀል ሳንካ፣
ተቆጣው በቃልህ
አስለቃሹን ስበር፣
ደህነኛውን ተካ፤
 
አደይ አበባ እንካ፥
ውሰድ ጽጌያቱን
ተወው ያንን ዋርካ፣
በደግ ቀን ላንተ
ከዛፉ ጥላ ሥር
ውዳሴ እንድንሰፍር
ቃል እንድንቆጣጥር፣
አበባ እንድንለቅም፣
ጨዋታ እንድንገጥም
‘እኔክሽ እኔካ’
ጎንጉነን እንግጫ፥
የምናርፍ ጊዜ፥
ከጌቶች እርግጫ፤
 
ሲከፋን ተደፍተን፣
እንድናለቅስበት
ተሰብስበን በእምነት
ተጣምረን በእውነት፣
ደርድረን ምስክር
ከሰማይ ከምድር፣
እሮሮ እንድንቀምር፥
ተውልን ሰማዩን
ንቀለው ፀሐዩን
አዲስ ትከልልን፤
ሳናርፍ ከመከራ፥
እንባ ጋብ ሳይል
አንዴም ሳያባራ፣
ስንዘም፥ በምሽቱ
ስንወድቅ በጠራራ፣
“ማራናታ” ስንል
ሰርክ ስንጣራ…
 
ጊዜ ተፈትልኮ፣
ክረምት አልፎ በጋ፥
ሺህ መአልት ጨልሞ፥
አንዴም ሌት ሳይነጋ፣
ጳጉሜን ሆነ እኮ
ዘንድሮም ቀደመህ፣
አዲስ ዓመት መጣ፤
ሰለቸን ሺህ ዘመን
በ“እህህ” ማቃሰት
ጎዳን እምቧይነት፣
መኖር እሾህ ታክኮ
መቀለብ በጎመን…
 
አሮጌው ድስት ይውጣ፣
እግዜር ብረድስት ላክ፥
ብርቱ አብሳይ አምጣ፣
‘ሕዝብህን አድነው
ርስትህንም ባርክ’
ሰቆቃውን ክላ፣
ቤቱን ዘይት ሙላ
እግዜር ቀማሽ ስደድ፣
አልጫው ይጣፍጥ፣
ይነስነስበት ጨው፥
በሰላም ይላቆጥ፣
ይመለስበት ሰው፣
 
እንቁጣጣሽ እንበል
ዕንቁው ለዓለሙ፣
ጣጣው ያማረበት
የሰው ልጅ ሰላሙ!
 
ጅብ ከደጅ ሲያደባ
የሰው ደም ተጠምቶ
ይቀበር ከጉድባ፤
 
እግዜር ገድብ እንባ
እግዜር ሀሴት አስባ፣
መስከረም ሳይጠባ!
 
/ዮሐንስ ሞላ/

ስለደም…

ሕይወት እንደዚህ ናት። አንዳንዱ ‘ይጠብቃል’ ሲባል፥ ደም ለማፍሰስ በአዋጅ ታጥቆ ይነሳል። ሌላው ደግሞ ደም ለሚያስፈልገው ደም ለመሰብሰብ ያስተባብራል።

በተለይ በዚህ ጊዜ ብዙ ደም ያስፈልገናል። በየሁኔታው የተጎዱ ብዙዎች ስላሉ፣ መስጠት የምንችለውን ጥቂቱን ለመስጠት እጃችንን በመዘርጋት ብዙ ሕይወቶችን ከሞት እንታደጋለን። ከሰው ልጆች ጋር አብሮነታችንን በተግባር እንገልጻለን። ነገ ደግሞ አቡጊዳ ሮታራክት ክለብ 35ኛው የደም ልገሳ ፕሮግራሜን አከናውናለሁ ብሏልና፥ የምትችሉ ሁሉ በመሄድ በመልካሙ ተግባር እንድታሰተፉ ይሁን። ነገ የማትችሉ፣ ወይም በሌላ ቦታ ያላችሁ ደግሞ፥ በያላችሁበት ወይም በቻላችሁበት ጊዜ ደም እንድትለግሱና ለሰው ልጆች ደስታ አስተዋጽኦ እንድታደርጉ ይሁን።

የነገው መርሀ ግብር ቦታ: ስታዲየም ብሔራዊ የደም ባንክ
ሰዓት: 2:30 – 12:00

አስተባባሪዎቹን እናመሰግናለን!

14192653_10208858338767262_8093716728756210687_n

የቂሊንጦ እስር ቤት እሳት

ቂሊንጦ እስር ቤት ውስጥ እሳት ተነስቶ እንደነበር እና፣ የእስር ቤቱ በሮች ተዘግተው ለረጅም ደቂቃዎች የቆየ ተኩስ ሲሰማ እንደነበረ ሰማን። መቼም ሴት ጠያቂ እንኳን እስከሞዴስ ድረስ ተፈትሾ በሚገባበት እስር ቤት ውስጥ ማን ማን ላይ ተኮሰ? ማን እሳት ለኮሰ? የሚል ጥያቄ ውስጥ አይገባም። (በድንገት የተነሳ የእሳት አደጋ ከሆነ፥ ምን ተኩስ አስከተለው? ብዬ ነው።)
ደግሞ እነ Daniel Berhane “ግርግሮች እየተቀዛቀዙ በመሄዳቸው የተደናገጡት የግንቦት 7 የውስጥ አርበኞች የሀገሪቱን እስር ቤቶች በእሳት መለኮስ ስራዬ ብለው ተያይዘውታል።” በማለት ተናግረዋል። እንዲህ ያለው “ሳያጣሩ ወሬ እና ውንጀላ” እሳቱ የሴራ መሆኑን ያመለክታል። (ከልምድ እንደምናውቀው፥ ምናልባት ጩኸት ለመቀማት እና ነገሩን ሁሉ ‘የአሸባሪዎች ዓላማ’ ለማለት? ምን ጣጣ አለው ለነሱ… በየታክሲው እና በየሆቴሉ ቦምብ እየጠመዱ ‘ፀረ ሰላም ኃይሎች’ ሲሉ እናውቅም የለ?)
 
በግንቦት ሰባት ስም ያሰሯቸውን እስረኞች ለመወንጀል ነው ‘የግንቦት 7 የውስጥ አርበኞች’ የሚባለው? ደግሞ ግንቦት ሰባት፥ ይኽን ያህል አቅም ያላቸው፣ ‘እስከሚኒስትር ዲኤታ ድረስ ሰርገው የገቡ’ የውስጥ አርበኞች እንዳለው እየገለጹ ከሆነ የመጠላትን ወሰን አያሳይም? (እንግዲህ ገና ትናንት ነው 100 ፐርሰንት የተመረጡት) ‘አሸባሪ’ ብሎ ስም ማውጣት ብቻውን ሰውን አሸባሪ ያደርገዋል እንዴ? ይኼን ያህል ኢህአዴግ በሊዝ አልገዛን። የምን ነገር ሲተበትቡ መኖር ነው?!
 
ለማንኛውም እርሱው ከየቤቱ እና ከማኅበረሰቡ ጉያ ፈልቅቆ ላሰራቸው ንጹሐን፣ ለያውም ገና በክርክር ላይ ያሉ፣ መንግስት ሙሉ ሀላፊነቱን ይወስዳል!!
 
ቸሩን ወሬ ያሰማን!
 
ቃጠሎውን በተመለከተ የዋዜማ ሬድዮን ዘገባ ቀጥሎ ያንብቡ። 

fire-on-Kilinto-presion.jpgዋዜማ ራዲዮ-ተቃዋሚ የፓለቲካ አመራሮችን እና ጋዜጠኞችን ጨምሮ ከሶስት ሺህ በላይ እስረኞችን የሚይዘው የአዲስ አበባ ቅሊንጦ ማረሚያ ቤት በእሳት ጋየ።

በፌደራል ማረሚያ ቤቶች አስተዳደር ስር የሚገኘው የቂሊንጦ ጊዜያዊ የእስረኞች ማቆያ ዛሬ ጠዋቱን በግቢው በተነሳ የእሳት አደጋ ቃጠሎ የደረሰበት ሲሆን ቁጥራቸው ያልታወቁ ታራሚዎች መጎዳታቸውን የዓይን እማኞች ገልፀዋል፡፡

የእሳት አደጋው የተነሳው ጠዋት ሶስት ሰዓት ገደማ እንደነበር እና ቃጠሎውን ተከትሎም የተኩስ ድምፅ በተከታታይ መሰማት መቀጠሉን በአካባቢው የነበሩ እማኞች ለዋዜማ ተናግረዋል፡፡ እሳቱ የተቀሰቀሰው የቂሊንጦ እስር ቤትን ከሚጎራበተው የአዲስ አበባ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርስቲ አቅጣጫ እንደሆነም ያስረዳሉ፡፡ ጥቂት ቆይቶ የአስተዳደር ቢሮዎች እና አዳራሽ ወደሚገኙበት ቦታ እንደተዛመተም ያብራራሉ፡፡

ለዩኒቨርስቲው የሚቀርበው የእስረኞች ቦታ በእስር ቤቱ አጠራር ዞን አንድ ተብሎ የሚታወቀው ቦታ ነው፡፡ በተለምዶ ወደ ሶስት ሺህ ገደማ እስረኞችን በውስጡ የሚይዘው የቂሊንጦ እስር ቤት በሶስት ትልልቅ ዞኖች የተከፋፈለ ነው፡፡ ምርጫ 2007ን ተከትሎ አነስተኛ የሆነ እና በቆርቆሮ የተሰሩ ማረፊያ ቤቶችን የያዘ አራተኛ ዞን የተገነባ ሲሆን በፖለቲካ ሰበብ ለእስር የተዳረጉ እሰረኞችን ከሌሎች ለመለየት በሚል አንድ አነስተኛ ዞን በቅርቡ ተጨምሯል፡፡

ቃጠሎው በየቦታው መስፋፋቱን ተከትሎ የእስር ቤቱ ፖሊሶች ዙሪያውን ከበው መተኮስ መጀመራቸውን እና የእስረኞች የጩኸት ድምጽ ከርቀት ሁሉ ጎልቶ ይሰማ እንደነበር በቦታው የነበረ የዋዜማ ምንጭ ይናገራል፡፡ ተኩሱ ለ40 ደቂቃ ያህል ግድም መቆየቱንም ይገልጻል፡፡ የተኩሱን ድምጽ የሰሙ በአቅራቢያው የሚገኙ የፌደራል የፖሊስ ኃይሎች ከጥቂት ጊዜ በኋላ መድረሳቸውንም ያስረዳል፡፡

በአንድ ኤፍ ኤስ አር ሙሉ የተጫኑ ፖሊሶች ወደ ግቢው ሲገቡ ተመልክቻለሁ የሚለው የዋዜማ ምንጭ በትንሹ በአምስት ፒክ አፕ መኪኖች የተጫኑ ተጨማሪ ፖሊሶችም ወደ ቦታው ሲያመሩ ማየቱን ይገልጻል፡፡

የተኩስ ድምጽ መሰማት ሲጀመር ከእስር ቤቱ አጠገብ በመሆን ለእስረኞች የሚፈቀዱ ሸቀጣ ሸቀጦችን የሚሸጡ የመንገድ ዳር ነጋዴዎች በፍጥነት መበታተናቸውን ሌላ የዓይን እማኝ ትናገራለች፡፡ የእስረኛ ጠያቂዎች ጉዳዩን ለማጣራት ወደ ቦታው ሲጠጉ ፖሊሶች ይመልሷቸው እንደነበርም ታስረዳለች፡፡

እኩለቀን ሊሆን ግማሽ ስዓት እስኪቀረው ድረስ በእስር ቤቱ ቅጥር ግቢ ውስጥ ከፍተኛ ተኩስ ይሰማ የነበረ ሲሆን ወደ እስር ቤቱ የሚያስኬዱ መንገዶች ሁሉ በፀጥታ ሃይሎች ተዘግተዋል።

ቅሊንጦ ከፍተኛ ጥበቃ ማረሚያ በኦሮሚያ ክልል የተነሳውን ህዝባዊ ተቃውሞ ተከትሎ የሽብር ክስ የተመሰረተባቸው የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ ፓርቲ ምክትል ሊቀመንበር አቶ በቀለ ገርባን ጨምሮ በርካታ የፓለቲካ አመራሮች ፣ የኢትዮጵያ የሙስሊሞች ጉዳይ መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ ከፊል አባላት እንዲሁም ጋዜጠኞች ለአመታት የፍርድ ሂደታቸውን ታጉረው የሚከታተሉበት ስፍራ ነው።

በእስር ቤቱ ደንብ መሰረት የቅዳሜ እና እሁድ የእስረኞች መጠየቂያ ሰዓት ለግማሽ ቀን የተገደበ ነው፡፡ ጠያቂዎች ሁለት ሰዓት ተኩል አከባቢ ስማቸው እና የሚጠይቁትን ሰው አስመዝግበው ወደ ግቢው እንዲገቡ ይፈቀድላቸው ነበር፡፡ ቀናቱ የዕረፍት ቀን እንደመሆናቸው መጠን እና በርካታ ጠያቂዎች የሚስተናግዱበት በመሆኑ ብዙዎች በእስር ቤቱ አካባቢ የሚገኙት ማልደው ነው፡፡

በጠያቂዎች በኩል በዛሬው ዕለትም ተመሳሳይ ሁኔታ እንደነበር የዓይን እማኞች ይናገራሉ፡፡ በፖሊሶች አማካኝነት ከቦታው እንዲርቁ የተደረጉት ጠያቂዎች እና የአካባቢው ሰዎች በአንድ በኩል ከጥሩነሽ ቤጂንግ ሆስፒታል እንዳያልፉ መደረጉን እና በሌላኛው አቅጣጫ ደግሞ ሄንከን ቢራ ፋብሪካ ጋር መንገድ መዘጋቱን ያብራራሉ፡፡

ከእስር ቤቱ የሚትጎለጎለውን ጭስ በርቀት ሆነው የሚያስተውሉት ጠያቂዎች እና የአካባቢው ነዋሪዎች አምቡላንሶች ወደ ቂሊንጦ እየተመላለሱ የተጉዱ ሰዎችን ጭነው በፍጥነት ወደ ህክምና መስጫ ቦታዎች ሲሄዱ መመልከታቸውን ያስረዳሉ፡፡ አምቡላንሶቹ መጀመሪያ ላይ በቂሊንጦ አቅራቢያ ወደሚገኘው ጥሩነሽ ቤጂንግ ሆስፒታል ሲገቡ ይታዩ የነበረ ሲሆን በስተኋላ ላይ ግን ሞልቷል በማባሉ ተጎጂዎችን ይዘው ወደ ቃሊቲ አቅጣጫ ሲሄዱ እንደነበር ይገልጻሉ፡፡

እስካሁን ድረስ ቁጥራቸው ያልታወቀ ታራሚዎች መጎዳታቸው ቢነገርም ትክክለኛ መረጃ ማግኘት ግን አዳጋች ሆኗል፡፡ አደጋው መከሰቱን ያመነው የአዲስ አበባ እሳትና ድንገተኛ አደጋዎች መከላከል እና መቆጣጠር መስሪያ ቤትም ሶስት የአደጋ ጊዜ ሰራተኞቹ ላይ ጉዳት መድረሱን ከመናገር ውጭ በእሰረኞች ላይ ስለደረሰው አደጋ ከመናገር ተቆጥቧል፡፡

በእስር ቤቶች ላይ የሚደርስ የእሳት ቃጠሎ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተደጋጋሚ ሲከሰት የሚስተዋል ጉዳይ ሆኗል፡፡ በዚህ ዓመት ብቻ በርካታ ሰዎች የተጎዱባቸው ተመሳሳይ አደጋዎች በጎንደር እና በደብረ ታቦር እስር ቤቶች ተከስቶ ነበር፡፡

ዋዜማ ሬድዮን የፌስቡክ ገጽ ይከተሉ። 

NEW VOCABULARY TO YOUR DICTIONARY

HMD (n.)
1. an obsequious or overly deferential person; a toady.
2. unintelligible or meaningless speech or writing; nonsense; gibberish.
3. foolish or vacuous; puppet.
 
Example:
a) “HMDs are telling the oppressed majority of Ethiopia is at the good hands of the government that is known for its bloodiness”
b) “He was HMD enough to be a yes man whatsoever”.
c) “You are HMD to make any sense even to your girl friend.”
 
HMD (v.)
1. to serve somebody in a servile, degraded way; to act in a disgraceful toady way.
2. to speak unintelligibly, typically through fear or shock.
3. to held meeting at which people attempt to make contact with the dead.
 
Example:
a) “The prime minister HMDed to homicide innocents protesting against the barbaric government.”
b) The officers have been HMDing with the ghost of the late prime minister so as to continue his legacy of consistent and shameless tyranny.
 
HMD (adj.) 1. producing no result; useless.
2. ridiculously impractical or ill-advised.
3. not existing, or not actually present.
 
Example:
a) “An HMD attempt to calm down the protests with bullet.”
b) “He pretended to give an HMD solution.”
 
#Ethiopia

Governance and bullying steps – the Ethiopian (TPLF/EPRDF) way!

(Comment on Alula Solomon’s post)
 
1. Sing ‘developmental democracy’, and dance ‘federalism’ to cover the fascist and the racist in it.
 
2. Censor private medias, and force them to close if they won’t be submissive to the government. Persecution and imprisonment follow.
 
3. Spread consistently fabricated lies and propaganda, labeling every good initiative ‘terrorist and anti-development’ if it is not harmonious with the government’s mischievous and corrupt plans and deeds, terrify the people as if it is an angel and devil will takeover when it fall, using the state owned TV and Radios. Doing every possible thing, whatever it may cost: from the tax payer’s money to the lives of journalists, bloggers, activists and opposition party members, to close and/or slander other information doors.
 
4. Organize immoral thugs in the name of ministers, advisers, officers, and cadres; and gangs in the name of federal police.
 
5. Work evilly to brainwash education, culture, pride, and every good thing the people has accumulated out of penury; and scorn the oppressed majority.
 
6. Corrupt systems and resources, terrify steadily, call up the hard times they had as rebel group against the Derg regime, to implicitly induce that they deserve to oppress the people (bragging like the country is their colony), benefit selectively based on ethnic and political opinion in almost every other spot, and creating disparity between different nations of the country.
 
7. Gather, as their cadres, many optionless bootlickers that strive to support their daily subsistence with the money they get as an allowance for attendance of Kebele meetings. And use them for any public demonstrations called by the government, such as the late PM’s mass mourning ceremony.
 
8. Create feelings of second citizens and strangers in the people through their ruthless practice of nepotism, and merciless actions against the concerned citizens.
 
9. Violate the constitution. Ban peaceful demonstrations, and assemblies. Imprison and persecute concerned citizens. Murder the people for their peaceful protests.
 
10. Vandalize and destroy the people itself, not limited to it’s properties.
 
11. Spread hatred among the people that itself has worked hard to segregate in the name of federalism, to let them fight each one another to seek more ages of tyranny.
 
12. Disseminate fabricated stories about the protests, hijack the realities of the causalities in order to confuse as if there is attack against an ethnic group. Fabricate lies about damaged properties of one, while there are mass killings of the other by it’s own police officers.
 
13. Making low quality documentaries; while the people keep on suffering, and try to sign petitions in vain to international community, US government, EU, etc.
 
14. So much more.
 
#Ethiopia #StopKillingCivilians #OromoProtests #AmharaProtests

ስለ ሁሉም!

“የማርያም መንገድ ስጠኝ። ዝቅ ብዬ ቁልቁለቱ ላይ ልቁምና ተራራዬን ላብዛው።” ብሎ ጨዋታ ምንም አይጠቅምም። ብሔር ተለይቶ ብቻ የተፈጸመ/የሚፈጸም ነገር ካለ፣ ወይም እንደዚያ የሚወሰውሱ ሰዎች ካሉ እነሱን አወግዛለሁ። አመንነውም ካድነው፣ አገሪቱ ላይ እንደ ሁለተኛ ዜጋ ሲሰማው የኖረ ብዙ ሰው አለ። ሀተታ እና ማስረጃ ሳያስፈልገው፥ ኢህአዴግ ይህን ማድረጉ ይታወቃል። ሀላፊነቱንም ራሱ ይወስዳል።
 
“የትግራይ ህዝብ ከመተማ ተለይቶ ተሰደደ፣ ቤቱ ተቃጠለ፣ ጥቃት ተፈጸመበት።” የተባለው ወሬ እውነት ከሆነ፥ በዋናነት ሀላፊነቱን የሚወስደው ኢህአዴግ ነው። “እውነት ከሆነ” ያልኩት፥ ተቃውሞዎች መሰማት ከጀመሩበት ጊዜ አንስቶ፣ ያለውን ጫና እና የጥቃት ልክ ስንሰማ የኖርንባቸው ሚዲያዎች፥ በዚህ ዙሪያ የዘገቡት ነገር ስለሌለ ነው። አገር ውስጥ ያለ ነጻ ሚዲያም የለምና እንዲህ ያለውን ወሬ የሚዘግብ አናገኝም። ሌላው ቀርቶ፥ “አመጽ ቀስቃሽ መጽሐፍ ይዘህ ዞረሃል” ብሎ መጽሐፍ አዟሪዎችን የማሰር ዜና ከሰማንም ሳምንት አልሆነውም።
 
የመንግስት ሚዲያ እንደው እንደከብት ዓይን አረንጓዴ እንጂ ራሱ የሚቀምመውን ቀይ ቀለም እንኳን አያሳይም። የሌለ ልማት እና ሰላም፣ እንጂ ሌላ ሌላ ነገር ሲወራ እንዳንሰማ ተፈርዶብናል። የተወራ ቀንም ለመግለጫ፣ ለዛቻ፣ ሕዝቡን በአንዳንድ የከተማ ነዋሪዎች ለማስመከር፣ እንዲሁም “ታድለው ምንም አይሰማቸውም” ለማስባል፣ እና ለስም መስጠት ነው። ስለዚህ ኢህአዴግ ሀላፊነቱን የሚወስደው፥ ሚዲያዎችን በማፈን፣ አገር ውስጥ የሚከናወኑ ጉዳዮች በእኩል መጠን የዜና ሽፋን እንዲያገኙ ስለማይፈቅድም ጭምር ነው። በፌስቡክ እንኳን ሰዉ በመረጃ ክፍተቱን ቢሞላ፥ እንዴት ጥርስ እንደነከሱባት በዶክመንተሪ እና በየስብሰባው እያነሱት አሳይተውናል።
 
የፈሰሰውን ደም እና ያለውን ተቃውሞ ከመዘገብ ይልቅ ያልዘራውን ማሳ፥ “አሸተ ጎመራ” ብሎ ማሳየት ነው የሚቀለው። ባለፈው ፈይሳ ሌሊሳ እጁን ቢያጣምር እና ተቃውሞውን ሲያሳይ ቀጥታ ቢታይ፥ መብራቱን ደረገሙት። እንግዲህ የኢህአዴግ ሚዲያ ከዚህ ከፍም ዝቅም የለውም። ስለዚህ ዜናዎች በአግባቡ እንዳይደርሱ እና እኩል ዘገባ እንዳያገኙ ከማድረግ ጀምሮ ለተጫወታቸው መሰሪ ሚናዎች ሁሉ ሀላፊነቱን ይወስዳል።
 
ስለዚህ፥ የትግራይ ሕዝብ ላይ ተለይቶ በሕዝብ ጥቃት ተፈጽሟል ብለው ያመኑ ሰዎች፥ ከሰፊው ሕዝብ ጋር ወግነው፣ መንግስትን የሚያወግዙበት እና “በቃህ” የሚሉበት ትክክለኛ ጊዜ ነው። ቢያንስ እሱን ሲያወግዙ ከስር ከስሩ ግድያውን እና ጅምላ ጨራሽ አዋጁን ማውገዝ ቀላል ነገር ሆኖ ተሰሚነትን ያስተርፋል። በዚያም ላይ፥ የዘረኝነትን ሴራ በመሸረብ ሲወጣ ሲወርድ የነበረውም ኢህአዴግ ስለሆነ እሱን በጋራ ማውገዝ እና አንድ ላይ በመሆን አምባገነንነት እንደማያሸንፍ ማሳወቅ ነው።
 
ተቃውሞ ስለማይረፍድ (መንግስትን መቃወም ማለት ሰፊው ሕዝብን መደገፍ ማለት መሆኑም እየታወቀ)፣ ከተጠቁት ወገን ሆኖ ኢህአዴግን በአደባባይ ስላወጀው ግድያ ማውገዝ ፈጣን መፍትሄ ይሆናል። አንዱ ቢጀምረው ሺ ምንተ ሺው ይከተላል። ሀበሻ ደግሞ በአንድ መፈክር ዞሮ ይገናኛል። Trust me, if it is heartfelt, unity is a slogan away!, and it will only terrify the bloody government.
 
የዘረኝነት ድርጊት ካለ ቋቱ ኢህአዴግ ጉያ ስር ነው። ዋናው ጠላታችን ለራሳችን ያለን ስሜት (ego) ነው። ሌላው ጠላታችን ደግሞ ነገሩን ቆመን የምንመለከትበት ቦታ ነው። ዳገት ላይ ቢቆሙ ቁልቁለት ነው የሚታየው። ቁልቁለት ላይ ቢቆሙ ደግሞ ዳገት ነው የሚታየው። እና አቋቋምን ለማስተካከል በመጣር ቢያንስ ጥፋትን መቀነስ ይቻላል። ጨካኞች ቀጥለው ነው የሚያጠቁን።
 
የትግራይ ሆነ የአማራ፥ የሰው ልጆችን መጎሳቆል ማየት የማይፈልግ ሰው፣ በውስጡ ሰብዓዊነት ይኖራልና፥ “ትግራይ ተለይቶ ጉዳት ደረሰበት” ካለ፥ የሌላውንም ጉዳት እኩል ዘግቦ ማውገዝ አለበት። መሞት እጣ ፈንታ በሆነበት አገር ላይ፥ ወደ ሱዳን መሰደድ እንደ እድል ሲቆጠር ቢታይም ብዙ አያስፈርድም።
 
አምባገነኑን መንግስት በመቃወምና፣ በጠቅላይ ሚኒስትር ሀማደ የታወጀውን ጅምላ ግድያ ለመቋቋም መከራውን እየበላ ያለ ሁሉም፥ ትግሉ ከስርዓቱ ጋር መሆኑን በማወቅ ጥቃት ያልፈጸመበት ሕዝብ ላይ ምንም እንዳያደርግ ሊጠነቀቅ ይገባል። የአምባገነኑ መንግስት አካላትም ቢሆኑ፥ የድርጅታቸውን እድሜ ለማራዘም ጥቃቱን ከሕዝብ ለሕዝብ የተፈጸመ በማስመሰል አድርገው ሊያደርጉ ይችላሉና እነሱንም ነቅቶ ማየት ያሻል።
 
ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!