ስለ ሁሉም!

“የማርያም መንገድ ስጠኝ። ዝቅ ብዬ ቁልቁለቱ ላይ ልቁምና ተራራዬን ላብዛው።” ብሎ ጨዋታ ምንም አይጠቅምም። ብሔር ተለይቶ ብቻ የተፈጸመ/የሚፈጸም ነገር ካለ፣ ወይም እንደዚያ የሚወሰውሱ ሰዎች ካሉ እነሱን አወግዛለሁ። አመንነውም ካድነው፣ አገሪቱ ላይ እንደ ሁለተኛ ዜጋ ሲሰማው የኖረ ብዙ ሰው አለ። ሀተታ እና ማስረጃ ሳያስፈልገው፥ ኢህአዴግ ይህን ማድረጉ ይታወቃል። ሀላፊነቱንም ራሱ ይወስዳል።
 
“የትግራይ ህዝብ ከመተማ ተለይቶ ተሰደደ፣ ቤቱ ተቃጠለ፣ ጥቃት ተፈጸመበት።” የተባለው ወሬ እውነት ከሆነ፥ በዋናነት ሀላፊነቱን የሚወስደው ኢህአዴግ ነው። “እውነት ከሆነ” ያልኩት፥ ተቃውሞዎች መሰማት ከጀመሩበት ጊዜ አንስቶ፣ ያለውን ጫና እና የጥቃት ልክ ስንሰማ የኖርንባቸው ሚዲያዎች፥ በዚህ ዙሪያ የዘገቡት ነገር ስለሌለ ነው። አገር ውስጥ ያለ ነጻ ሚዲያም የለምና እንዲህ ያለውን ወሬ የሚዘግብ አናገኝም። ሌላው ቀርቶ፥ “አመጽ ቀስቃሽ መጽሐፍ ይዘህ ዞረሃል” ብሎ መጽሐፍ አዟሪዎችን የማሰር ዜና ከሰማንም ሳምንት አልሆነውም።
 
የመንግስት ሚዲያ እንደው እንደከብት ዓይን አረንጓዴ እንጂ ራሱ የሚቀምመውን ቀይ ቀለም እንኳን አያሳይም። የሌለ ልማት እና ሰላም፣ እንጂ ሌላ ሌላ ነገር ሲወራ እንዳንሰማ ተፈርዶብናል። የተወራ ቀንም ለመግለጫ፣ ለዛቻ፣ ሕዝቡን በአንዳንድ የከተማ ነዋሪዎች ለማስመከር፣ እንዲሁም “ታድለው ምንም አይሰማቸውም” ለማስባል፣ እና ለስም መስጠት ነው። ስለዚህ ኢህአዴግ ሀላፊነቱን የሚወስደው፥ ሚዲያዎችን በማፈን፣ አገር ውስጥ የሚከናወኑ ጉዳዮች በእኩል መጠን የዜና ሽፋን እንዲያገኙ ስለማይፈቅድም ጭምር ነው። በፌስቡክ እንኳን ሰዉ በመረጃ ክፍተቱን ቢሞላ፥ እንዴት ጥርስ እንደነከሱባት በዶክመንተሪ እና በየስብሰባው እያነሱት አሳይተውናል።
 
የፈሰሰውን ደም እና ያለውን ተቃውሞ ከመዘገብ ይልቅ ያልዘራውን ማሳ፥ “አሸተ ጎመራ” ብሎ ማሳየት ነው የሚቀለው። ባለፈው ፈይሳ ሌሊሳ እጁን ቢያጣምር እና ተቃውሞውን ሲያሳይ ቀጥታ ቢታይ፥ መብራቱን ደረገሙት። እንግዲህ የኢህአዴግ ሚዲያ ከዚህ ከፍም ዝቅም የለውም። ስለዚህ ዜናዎች በአግባቡ እንዳይደርሱ እና እኩል ዘገባ እንዳያገኙ ከማድረግ ጀምሮ ለተጫወታቸው መሰሪ ሚናዎች ሁሉ ሀላፊነቱን ይወስዳል።
 
ስለዚህ፥ የትግራይ ሕዝብ ላይ ተለይቶ በሕዝብ ጥቃት ተፈጽሟል ብለው ያመኑ ሰዎች፥ ከሰፊው ሕዝብ ጋር ወግነው፣ መንግስትን የሚያወግዙበት እና “በቃህ” የሚሉበት ትክክለኛ ጊዜ ነው። ቢያንስ እሱን ሲያወግዙ ከስር ከስሩ ግድያውን እና ጅምላ ጨራሽ አዋጁን ማውገዝ ቀላል ነገር ሆኖ ተሰሚነትን ያስተርፋል። በዚያም ላይ፥ የዘረኝነትን ሴራ በመሸረብ ሲወጣ ሲወርድ የነበረውም ኢህአዴግ ስለሆነ እሱን በጋራ ማውገዝ እና አንድ ላይ በመሆን አምባገነንነት እንደማያሸንፍ ማሳወቅ ነው።
 
ተቃውሞ ስለማይረፍድ (መንግስትን መቃወም ማለት ሰፊው ሕዝብን መደገፍ ማለት መሆኑም እየታወቀ)፣ ከተጠቁት ወገን ሆኖ ኢህአዴግን በአደባባይ ስላወጀው ግድያ ማውገዝ ፈጣን መፍትሄ ይሆናል። አንዱ ቢጀምረው ሺ ምንተ ሺው ይከተላል። ሀበሻ ደግሞ በአንድ መፈክር ዞሮ ይገናኛል። Trust me, if it is heartfelt, unity is a slogan away!, and it will only terrify the bloody government.
 
የዘረኝነት ድርጊት ካለ ቋቱ ኢህአዴግ ጉያ ስር ነው። ዋናው ጠላታችን ለራሳችን ያለን ስሜት (ego) ነው። ሌላው ጠላታችን ደግሞ ነገሩን ቆመን የምንመለከትበት ቦታ ነው። ዳገት ላይ ቢቆሙ ቁልቁለት ነው የሚታየው። ቁልቁለት ላይ ቢቆሙ ደግሞ ዳገት ነው የሚታየው። እና አቋቋምን ለማስተካከል በመጣር ቢያንስ ጥፋትን መቀነስ ይቻላል። ጨካኞች ቀጥለው ነው የሚያጠቁን።
 
የትግራይ ሆነ የአማራ፥ የሰው ልጆችን መጎሳቆል ማየት የማይፈልግ ሰው፣ በውስጡ ሰብዓዊነት ይኖራልና፥ “ትግራይ ተለይቶ ጉዳት ደረሰበት” ካለ፥ የሌላውንም ጉዳት እኩል ዘግቦ ማውገዝ አለበት። መሞት እጣ ፈንታ በሆነበት አገር ላይ፥ ወደ ሱዳን መሰደድ እንደ እድል ሲቆጠር ቢታይም ብዙ አያስፈርድም።
 
አምባገነኑን መንግስት በመቃወምና፣ በጠቅላይ ሚኒስትር ሀማደ የታወጀውን ጅምላ ግድያ ለመቋቋም መከራውን እየበላ ያለ ሁሉም፥ ትግሉ ከስርዓቱ ጋር መሆኑን በማወቅ ጥቃት ያልፈጸመበት ሕዝብ ላይ ምንም እንዳያደርግ ሊጠነቀቅ ይገባል። የአምባገነኑ መንግስት አካላትም ቢሆኑ፥ የድርጅታቸውን እድሜ ለማራዘም ጥቃቱን ከሕዝብ ለሕዝብ የተፈጸመ በማስመሰል አድርገው ሊያደርጉ ይችላሉና እነሱንም ነቅቶ ማየት ያሻል።
 
ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s