መስከረም ሳይጠባ!

እግዜር ኀዘን ስፈር፣
እግዜር አልቃሽ ቁጠር
አስለቃሹን መዝግብ፣
በግርማ መንግስትህ
እግዜር ዋይታ ዘግብ፣
መከራውን አስብ፤
 
እግዜር ለቅሶ ለካ
ያልቃሹን ዐይን ንካ፣
ዳብሰው በመዳፍህ
አፍርስ ንቀል ሳንካ፣
ተቆጣው በቃልህ
አስለቃሹን ስበር፣
ደህነኛውን ተካ፤
 
አደይ አበባ እንካ፥
ውሰድ ጽጌያቱን
ተወው ያንን ዋርካ፣
በደግ ቀን ላንተ
ከዛፉ ጥላ ሥር
ውዳሴ እንድንሰፍር
ቃል እንድንቆጣጥር፣
አበባ እንድንለቅም፣
ጨዋታ እንድንገጥም
‘እኔክሽ እኔካ’
ጎንጉነን እንግጫ፥
የምናርፍ ጊዜ፥
ከጌቶች እርግጫ፤
 
ሲከፋን ተደፍተን፣
እንድናለቅስበት
ተሰብስበን በእምነት
ተጣምረን በእውነት፣
ደርድረን ምስክር
ከሰማይ ከምድር፣
እሮሮ እንድንቀምር፥
ተውልን ሰማዩን
ንቀለው ፀሐዩን
አዲስ ትከልልን፤
ሳናርፍ ከመከራ፥
እንባ ጋብ ሳይል
አንዴም ሳያባራ፣
ስንዘም፥ በምሽቱ
ስንወድቅ በጠራራ፣
“ማራናታ” ስንል
ሰርክ ስንጣራ…
 
ጊዜ ተፈትልኮ፣
ክረምት አልፎ በጋ፥
ሺህ መአልት ጨልሞ፥
አንዴም ሌት ሳይነጋ፣
ጳጉሜን ሆነ እኮ
ዘንድሮም ቀደመህ፣
አዲስ ዓመት መጣ፤
ሰለቸን ሺህ ዘመን
በ“እህህ” ማቃሰት
ጎዳን እምቧይነት፣
መኖር እሾህ ታክኮ
መቀለብ በጎመን…
 
አሮጌው ድስት ይውጣ፣
እግዜር ብረድስት ላክ፥
ብርቱ አብሳይ አምጣ፣
‘ሕዝብህን አድነው
ርስትህንም ባርክ’
ሰቆቃውን ክላ፣
ቤቱን ዘይት ሙላ
እግዜር ቀማሽ ስደድ፣
አልጫው ይጣፍጥ፣
ይነስነስበት ጨው፥
በሰላም ይላቆጥ፣
ይመለስበት ሰው፣
 
እንቁጣጣሽ እንበል
ዕንቁው ለዓለሙ፣
ጣጣው ያማረበት
የሰው ልጅ ሰላሙ!
 
ጅብ ከደጅ ሲያደባ
የሰው ደም ተጠምቶ
ይቀበር ከጉድባ፤
 
እግዜር ገድብ እንባ
እግዜር ሀሴት አስባ፣
መስከረም ሳይጠባ!
 
/ዮሐንስ ሞላ/

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s