መንግስት ቢኖር…

የምር መንግስት ቢኖረን ኖሮ፥ ይህኔ በሬድዮና በቴሌቪዥን የሚታጀብ፣ ሰንደቅ ዓላማ ዝቅ የሚደረግበት ብሔራዊ ኀዘን ላይ ነበርን። ግን ያው፣ ሕዝቡ ራሱ ብሔራዊ ሐዘን ተጠራርቶ ቁጭ ብሏል።
 
“የገደለው ባልሽ
የሞተው ወንድምሽ፣
ሐዘንሽ ቅጥ አጣ
ከቤትሽ አልወጣ” ሆኖ አላመች አላቸው እንጂ፥ ለራሳቸው ፍጆታ ሲሉ እንደከዚህ በፊቱ ሁሉ እኛ የጠራነውን ብሔራዊ ሐዘን ያዳምቁ ነበር።
 
አሁን እንደው የመለስ ሞት በምን ሚዛን ተሰፍሮ ነበር፣ “በመንግስት ጥበቃ ስር ናቸው።” ተብሎ ሲታሰብ፣ በጥይት እና በእሳት ተጠባብሰው ከሞቱ ወገኖች ልቆ በዋሽንት ስንደነቁር የነበረው? ሲሆንስ አዲስ ዓመትን ጠብቆ እስረኞችን መፍታት የሚጠበቅ ነበር።
 
እሺ እሱም ቅንጦት ሆኖ ይቅር። የቤተሰብን ልብ ሰቅሎ ማሰቃየት ምን ይባላል? ባገራችን ደንብ እንደው የሰው ክቡርነት በሞት ደምቆ ይገለጻል። እርም ሳይወጣ ምግብ አይበላም። የከፋ ቅያሜ ቢኖር እንኳን አስከሬን ቆመው ያሳልፏል።
 
የሟች ወገኖች እናቶች እንዴት ሆነው ይኾን? የእናት እና የልጅ ተፈጥሯዊ ትስስር ጥልቅ ስለሆነ፥ የሞቱት እስረኞች እናቶች ይኽኔ ቁርጡን ሆዳቸው ይነግራቸዋል። (እናቴ በሌለሁበት ጠንከር ያለ እንቅፋት ቢመታኝ ታውቃለች።)
 
ታዲያ ግን ምን ብለው “ልጄ ሞቷል” ብለው ለቅሶ ይቀመጡ? ስሜቱን የማያውቅ ሰው እንደአሟራች ቢቆጥራቸውስ ይፈረድበታል። ምን ብለውስ “ልጄ ደህና ነው” ብለው ይረጋጉ። ስሜቱን የማያውቅ ሰው እንደግብዝ ቢቆጥራቸውስ ይፈረድበታል? ልጆቻቸው ሞቱ/ኖሩ ቁርጡን ሳያውቁ እንዴት ያንቀላፋሉ? ወዳጅ ዘመድ ጓደኛስ እንዴት እህል ይወርድለታል?
 
ሕዝብ በመንግስት በዚህ ልክ ይጠላል? “የድሃ ድሃዎች” አሉ ቃል ሲያሳምሩ እና ወሬ ለመቀሸር ሲሯሯጡ።
 
የክፉ ክፉዎች!!
 
ሕዝብ
——-
የእምቧይ ድርድር ካብ፥ እሾህ የማያጣ፣
ንጉሥ ሲደብረው፣
¬ ጭቃ ሹም ሲከፋ፣ ባለሟል ሲቆጣ፣
እንኳን ወሬው ቀርቶ፥ ዝምታው ‘ሚያስቀጣ፤
 
ኩራቱ ‘ሚያስጨንቅ — እንደ እመቤት ኩርፊያ፣
መቻሉ ‘ሚያስገፋ፣ ‘ሚያስደምር ከትቢያ፤
 
ወንበር ‘ሚያነቃንቅ፥ — የሰላሙ ዜና፣
መንግሥት የሚያሸብር፥ — የነፍሱ ጽሞና፤
 
ሳቁ ‘ሚያጠራጥር፤ ትንፋሹ ‘ሚያስገምት፣
እርምጃው ‘ሚለካ፤ ሩጫው ‘ሚያስፎትት፤
 
ሕዝብነት—
— ከንቱነት!
 
/ዮሐንስ ሞላ (2005) የብርሃን ልክፍት/

የንፍገት ጥግ

ከእለታት ባንዱ ቀን አምባገነን ገፍተው፣ ከጫካ ብቅ አሉ… ለመላ ለዘዴ፥ በሽለላ ብዛት፣ በዲስኩር ጋጋታ፣ ባዋጅ አጥር ብዛት፥ የሚሻል መሰሉ… ‘ዴሞክራሲ ሰፍኗል፣ ተናገሩ… ጻፉ፣ ተከራከሩ’ አሉ…
 
ገና በማለዳው፥ እንኳን የጻፈውን፣ ሊጽፍ ያሰበውን በፀረ ሽብር ህግ በቁም አሸበሩ… ‘በሽብርተኝነት ጠረጠርኩኝ’ ብለው ማለፊያውን ለቅመው፣ ሰብስበው አሰሩ፣…. ለተጠርጣሪው ሰው ማስረጃ ፍለጋ፣ ማስረጃ ቅመራ ላይ ታች ተባረሩ… በሰማይ በምድሩ ቧጠጡ፣ ዳከሩ… ወለሉን ቆፈሩ፣ ግድግዳውን ጫሩ… አልበቃ ብሏቸው ጊዜ ለፈጠራ፣ ለክስ ቅሸራ፥ በቀጠሮ መዓት፣ ገነቡ ተራራ… በእግረ ሙቅ እጅ አስረው፣ ከሰሩት አቀበት እያመላለሱ፣ አሳዩ መከራ…
 
ሲኖሩ ሲኖሩ…
ከእለታት ባንዱ ቀን፥ ‘እሳት ተነሳ’ አሉ ከእስር ቤት ምግብ ቤት… ‘ሊያመልጡ ሲሉ ነው’ ብለው በመተኮስ፣ የቻሉትን ጣሉ… አማራጭ በማጣት፣ የቀረውም ሸሸ ወደ ላንቃሙ እሳት… ‘ይህን ያህል ሞተ’ ተብሎ ተወራ፣ ከተጠቂውና ካጥቂው መንግስት ጎራ፣ ተዛብቶ ቆጠራ… ‘ከሞቱ ተረፉ’ የተባሉትንም ጭነው አጋዟቸው እስር ቤት ቀየሩ… በቤተሰብ ለቅሶ፣ በወዳጆች ዋይታ ታፈነ አየሩ… ቆዘመ መንደሩ…
 
ሳይነገር መርዶ… አስከሬን ሳይሰጥ… ከጥቃቱ የዳነም እንደተጨነቀ ሰላሙን ለማውራት… ተቆጠሩ ቀናት… ‘ቄሱም ዝም፣ መጻፉም’….. እርም ሳይወጣ፣ ያለው ሳይታወቅ ልብ እንደሰቀሉ… ‘አገሩ ሰላም ነው… በእውቀት ተቃወሙን’ ብለው አላገጡ፣ የቀለም ቀንዶችን፥ የቻሉትን አስረው፣ የቻሉትን ገፍተው እንዳላቀለጡ።
 
#Ethiopia
 
ምንም እንኳን የማውቃቸው ታሳሪዎች ባይኔ እየዞሩ እረፍት ቢነሱኝም፥ በሀቅ ሲመዘን ተጎጂው ሁሉ እኩል ነው። እግዚአብሔር ለተጨነቁትና ላዘኑት ሁሉ ብርታት ይስጥ። መርዶአቸው ባይሰማም፥ የሞቱትም በሰላም ይረፉ! የሰማዕትነትን አክሊል ያቀዳጅልን!