ትግሉ መስመር እስኪይዝ ድረስ፥ እንኳን በኢትዮጵያ አንድነት ከሚያምኑ ኦሮሞዎች ጋር መስማማት ቀርቶ፥ የአማራ እና የኦሮሞ ዛፍነትና የስሮቻቸው ተጨባባጭነትም ይቀነቀናል። እስከዚያ፥ ተመልካች (audience) እየለዩ፥ ዓላማን ለመሸፋፈን እና ወቅታዊ ተቀባይነትን ለማግኘት፥ በየቋንቋው የተለያየ ነገር ያስተላልፋሉ። ስጋቱን ለመግለጽ የሚሞክር ቢኖር፥ በ“ትግል አታዳክም” ታፔላ ሊሸማቀቅ ይዳከራል። ትግሉ መስመሩ ተጠናክሮ ዳር ሊይዝ አጥቢያው ሲመስል ደግሞ፥ “አገር ይፍረስ! እንክትክቱ ይውጣ!” ይባላል።
ይገርመኛል! ፊደል መቁጠር ለዚህ ለዚህ ካልጠቀመ ለምን ሊጠቅም ነው? በተለይ በባዕድ አገር ላይ፥ “ከየት ነህ? ማን ነህ? ምን ቋንቋ ትናገራለህ? ለምን መጣህ?” ሳይባል፣ ተመቻችቶለት እንደልቡ እየኖረ እና እንደ ኅብረተሰቡ አካል ተመሳስሎ እየተማረ፣ በሞያው እያገለገለ፣ መብቱን አስከብሮ ሸጦ ለውጦ እየተዳደረ፣ ቢሻው ሀብት ንብረት እያፈራ እና ቋሚ እሴት እያጠራቀመ፥ እንዴት ለገዛ ወገኑ እልቂት መፈራረስን ይመኛል? በእንግድነት በተድላ ከሚኖርበት ቦታ እንኳን እንዴት ይህንን ትምህርት አልቀሰመም? እንዴት በመከራ ውስጥ ሆኖ ነጻነቱን ሲፈልግ፥ ባልጠገበ አንጀቱ በአምባገነን ስርዓት ወድቆ የቀረ ወገኑ ደም ላይ ይሳለቃል?
ይኽስ ማንን ይጠቅማል? ሰድቦ ለሰዳቢ አሳልፎ ለመስጠት ካልሆነ፥ ማንን ወደፊት ያራምዳል? እስከመቼስ በአንድነት እና በትብብር አብሮ የሚኖረው ሕዝብ፣ በሆዳም ‘አዋቂ’ ነን ባይ ፖለቲከኞች “አይ አብረህ መኖር አትችልም” ይባልለታል? ለእነሱ አገር በማፍረስ ዋጋም ቢሆን የሚገኝ የስልጣን ጥማት ማርኪያነት ለምን ይናፈቃል? ትናንት የመጡትስ ከዚህ መች ተለይተው ጀመሩት? ደግሞ፥ “ይሁን” ቢባልና ቢሳካስ በሰላም መኖር ይቻል ይመስላቸዋል? ወይስ በቃ አገሪቱን ተቃርጠው በየክልሉ ተመሳፍነው ሊያስገብሩ ነው?
እንዲህ ዓይነቱ ጨዋታ፥ የሴረኞችን ህልም ከማሳካት ይልቅ፥ ሙሉ አገሩ ስለአንድነቱ በጋራ እንዲቆም እንደተላለፈ ጥሪ የሚቆጠር ነው። አገራችን በጨካኝ ስርዓት እጅ ባለችበት በዚህ ሰዓት፥ ‘አገር አፍራሽ ሆነን፣ ልንበትንህ መጥተናል። እኛ መሲህ ነን’ ዓይነት ነጋሪት ብትጎስሙበትና ከያዘው ትግል ልታጓትቱት ብትጥሩ፥ አይምራችሁ! የነጭ ስልጣኔ፣ ገንዘብና የተሻለ ኑሮ ሳያጓጓቸው በባዶ እግር እና በጨበጣ ውጊያ ጣሊያንን እንኳን ገርፎ የመለሰ ሕዝብ አገር ሰዎች ነንና መቼም አይሳካላችሁም!
መተዋወቅ ያስፈልጋል። ስለማታውቁት፣ ወይም ድሮ አውቃችሁት ስለረሳችሁት ሕዝብ ነው የምትደሰኩሩት። “ዶሮ ብታልም ጥሬዋን” እንዲሉ፥ መከራ የፈነቀለውን እና በጋራ የቆመውን ሕዝብ “የኔ ጦር ነው…የኔ” ትባባሉበታላችሁ። ቢቆስል፥ ‘የውሻ ቁስል ያድርግልህ’ ያላላችሁትን፣ ቢሞትበት፥ የቤተሰቡን ትኩስ አስከሬን ፎቶ በየገጹ ከመቀባበል ያላላፈ፥ ጠንከር ያለ “ነፍስ ይማር” እንኳን ያላላችሁለትን፥ ደሙን ገብሮ ነጻነቱን ለመቀዳጀት ደፋ ቀና ሲል… ‘እኛ ነበርን እግዚአብሔሮችህ፣ ከኋላህ ቆመን በለው በለው ስንልህ የነበርን። አሁን ድል አገናኝቶን የባንዲራህን ጨርቅ አስቀድደን፣ ልንሰቅልልህና ልናሸጋግርህ መጥተናል’ ብትሉት አይሰማችሁም። ኢህአዴግም በብዙ ነገር ከፋፍሎ፣ በትንሽ ትንሹ ጠርንፎ፣ በሀውልትና በፕሮፖጋንዳ፣ ‘በታትኜ ያዝኩት’ ያለው ሕዝብ፥ አንድ ሆኖ እያስደነበረው ነው።
አሰቃቂው የኢሬቻ እልቂት ሳይቀር እንኳን፥ እንደጥሩ ትግል ማቀጣጠያ ቤንዚንነት ያስደሰታችሁና፣ እንደ ጥብስ ወሬ ያነቃቃችሁ፥ “የአገር መፍረስ ህልመኞች” እንዳላችሁ ልባችሁ የሚያውቅ ታውቁታላችሁ። ቱኒዚያ ቦአዚዝ ራሱን ቢለኩስ፥ ቤንዚን ሆኖ የነጻነት መንገድ እንደጠረገላቸው፣ ለግብጽ አብዮትም የካሊድ ሰይድ ግፈኛ አገዳደል እርሾ ሆኖ እንዳሰባሰባቸው፥ ሰው በሞተ ቁጥር ህልማችሁን የማሳካት ሴራችሁ ከግብ እንደተቃረበ በመቁጠር ብቻ… በመሰባሰብ ፈንታ፣ ‘የድል ዋዜማ ላይ ነንና ብቻችንን እንቁም’ በሚል ብልጣብልጥነት ስንቱን ለማግለል እንደጣራችሁም፣ ስንቴ በጠላት እንዳሳለቃችሁብን የምታውቁ ታውቁታላችሁ። ኦሮሞ ያልሆነ ሰው የኦሮሞ ፖለቲካ ላይ ሀሳብ ቢሰጥ፥ በ’oromophobia’ ፈርጃችሁት፣ ፍርሀትን ለመትከል የለፋችሁም ታውቁታላችሁ።
“እንለይህ” የምትሉት ወገን፥ በጂኦግራፊያዊ አቀማመጥ እንኳን አንድ ቦታ የተከማቸ፣ ባህሉንም ያልተወራረሰ አይደለም። እንለይህ የምትሉት ወገን፥ እንጀራ ተበዳድሮ እና ሚጥሚጣ ተዋውሶ፣ ለቡና እየተጠራራ፣ ልጁን እርስ በርስ እየተቀጣጣ፣ ቤቱን ቁልፍ አልባ ትቶት “መጣሁ” ተባብሎ የኖረ ነው። ጡት ሳይቀር ተጋርቶ ያደገው ሕጻን ብዙ ነው። በከተሞች ብልጭ ድርግም ባይ መብራቶች የተጋረደ ብዙ ያልታየ ሕዝብ አለ። በአካባቢ መቀየር እንኳን የኑሮ ቀውስ የሚገጥመው ሕዝብ ነው።
“ጠላቶችህ ናቸው” ብላችሁ ስለወዳጆቹ ክፉ ለመንገር የምትደክሙለት ሕዝብ ያን ያህልም ክፉና ደግ የማይለይ እንዳልሆነ እንኳን አትገነዘቡም። ንቃችሁት ተነስታችሁ ነው እናስከብርህ የምትሉት። ከዚህ በላይ ‘እየታገልኩልህ ነው’ የሚሉትን አለማወቅ የለም!
የወገኖቻችን ደም በከንቱ ፈሶ አይቀርም!
ይጮሃል! ሁሌም ይጮኻል! ከጩኸቶቹ ሁሉም የጎላና የከበደ የሚሆነው፥ ‘ምሁራን’ ተሰብስበው ደሙን ሊያቃልሉበትና፣ ለጠላቶቹ መስዋዕት ሊገብሩበት እንደሆነ ያወቀ ጊዜ ሳይሆን አይቀርም።
የደፈረሰው ጠርቶ፣ የተከፈለው መስዋዕት እንደሚያጠባብቀንና ልቦቻችንን አክሞ በጋራ እንደሚያኖረን፣ አገሪቱንም ለሰው ልጆች ሁሉ የሚመች ስርዓት የሰፈነባት እንደሚያደርግ አልማለሁ!
ከዛሬ ነገ ይሻላል!
#Ethiopia