መርጠውና ለይተው፣ በእውቀትና በጥናት ላይ ተመርኩዘው ያደረጉት ነገር አይደለም። ልክ አፈጣጠራችንና በስጋ አዘማመዳችን እንደ እድል እንደሆነ፥ ሞታችንንም እንደ ዕድል ነው ያደረጉት። ካልደገፍናቸው፥ ኑሯችን እንደነፍሰጡር ሴት፥ ደርሶ እስኪታይ ድረስ መጪው የማይታወቅ ነው።
ስላልገደሉን ነው እንጂ ሁላችንም ላይ ተኩሰዋል። ስላልታሰርንላቸው ነው እንጂ ሁላችንም ላይ ሰንሰለታቸውን እያንሿሹ ሸልለውብናል። ስላልጣሉን ነው እንጂ ሁላችንንም ገፍትረዋል። ቅሬታን መግለጽና ይሻላል ያሉትን ሀሳብ መናገር ነውር እስኪመስል ድረስ በፍርሀት እና በሽብር ጠፍንገውናል። መፈጠራችንን እስክንጠላ ድረስ እርቃናችንን ለማስቀረት ደክመዋል።
እኛም አለን እስካሁን ከለቅሶ ለቅሶ እየዘለልን። ጨረስናቸው ሲሉን እንደ ምድር አሸዋ በዝተን እንኖራለን ገና!
እኔ ብሆን ኖሮስ?? እናቴ ብትሆን ኖሮስ?? ልጄ ቢሆን ኖሮስ?? ወንድሜ ቢሆን ኖሮስ?? እህቴ ብትሆን ኖሮስ?? ፍቅረኛዬ ብትሆን ኖሮስ?? የልብ ወዳጄ ቢሆን ኖሮስ?
“ማነሽ ባለተራ”
ጥርስ ውስጥ የገባሽ?
አናውቅም! ማንም አያውቅም!
እነሱም መግደልና ኡከት መፍጠር ሞያቸው ስላደረጉት እንጂ፥ ነገም ተቃዋሚውን መግደላቸውን እንጂ ማንን መግደላቸውን አያውቁም። ከገደሉ በኋላ ደግሞ ቁጥር መሸቀብና መቀርቀቡን ያውቃሉ። መዋሸቱን ያውቃሉ። እንጂ አገዳደሉ እንደገበያው ነው። ቤቱ ክፍት እንደተገኘበት ነው የጅብ አገባቡ። ጎረቤቱ እንደናቀው ነው የአጥር አነቃነቁ።
ሁላችንም በጋራ መነጋገር ካልጀመርን፣ ማውራት እና መደማመጥን ካላበረታን፣ እርስበርስ ካልተጠባበቅን ይጨርሱናል። በአንድነት ካልቆምን ለቅሷችን አያባራም፣ ድንኳናችንም አይፈርስም።
እግዚአብሔር ከተጎዱት ጋር ይቁም! በቃችሁ ይበለን!