ኢሬቻ

ed0665b9a76b426480aa73c26a057bc8_18አበባ ቀጥፌ፣ ምስጋና ሸክፌ፣
“ዋቃ ገለቶሚ” ልልህ አሰፍስፌ
መጥቼ ነበረ፥ ሰንበትን ቆጥሬ፣
ለከርሞው ልማጸን፥ ውዳሴ ሰፍሬ
ግጥሜን ደርድሬ፣ እልልታ ቀምሬ
ሀሴትን ቋጥሬ፥ የከንፈሬን ፍሬ፤
እኔን የቆሉበት ጢስ ሰማይ ላይ ወጥቶ፥
አጨናብሶህ መሰል፥ እንዳታይ አጥርቶ፣
ዘንድሮስ አልሞላ ቀጠሮ ታጎለ፣
ሳንተያይ ቀረ
ስጋ ዳገት ሰራ፣ ካፈር ተከመረ፤
ዋቃዮ የታለህ?
ብጣራም አልመጣህ ጭራሽ አትሰማ
በደም ተነከረ ያቀፍኩት ቀጤማ፤
ጽልመት ተነባብሮ ድቅድቅ ባለ ቁጥር፥
“ጽጌ ሊጠባ ነው፣ ሊነጋ ነው” ብዬ መጓጓቴም ከሳ፤
በነጎድጓድ ብዛት ሰማይ ሲተራመስ፥
ረግቶ ማያውቀው ሀይቅ፥ ክፉኛ ሲታመስ፥
“ምህረት ሊዘንብ ነው፣ ጥሩ ልጠጣ ነው”
ብዬ መጠበቄም፥ ጫነብኝ አበሳ፤
ኤሳ ጂራ ዋቃ?
ጋረደኝ ጨለማ፣ ደድሮ ተነሳ
የልቤ ክረምቱ በጣ’ይ ተከመረ፥
ብሶት እንባ መስሎ ካይኔ ተከተረ፤
ደሙን ተራምጄ ደም አደናቀፈኝ
እንባውን አልፌ እንባ ጠላለፈኝ፣
ዋይታውን ብዘለው ዋይታ ተቀበለኝ፥
ብሄድ ወደ ግራ፥ ብታጠፍ ወደቀኝ
ለቅሶና መከራ፣ ታጅቦ ጠበቀኝ፣
እስረኛው ጉያዬም በእሳት ተቃጠለ፥
በግፈኛው ሚዛን ሰውነት ቀለለ፤
ንገረኝ ጌታ ሆይ…
ስንት ተስፋ ይንጠፍ?
ስንት ጀምበር ይለፍ?
ስንት አበባ ይርገፍ?
ስንት ሰው ይሰዋ፣
እንዴት ይሙላ ጽዋ?
አይጥ በጠገበ፥ ስንት ይገረፍ ዳዋ?
ስንት ዳስ ይደርደር፣
ስንት ገጽ ይቧጨር?
ስንት ደረት ይፍረስ?
ስንት አጥንት ይከስከስ?
ከገጠር ከተማ፣ ስንሞት፣ ስንደማ፥
እንድታየን አንተ፣ ስንጮኽ እንድትሰማ?!
/ዮሐንስ ሞላ/

 

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s