ለቁም ነገር ስንጠራ

ማፈን መፍትሄ ኾኖ ቢያውቅ ኖሮ እንዲህ ባልደነበሩ ነበር። “ፀጉራም ውሻ አለ ሲሉት ይሞታል”ን በልባቸውም ቢሆን ለራሳቸው ባልተረቱ ነበር። ይኸው አዲስ አበባም ላይ የስልክ እና የሞባይል ኢንተርኔት አገልግሎቾን እንዳቋረጡ ነው።
 
ይኼ ማለት፥ ምንም እንኳን በየልሳናቶቻቸው እየቀረቡ፣ የማኅበራዊ ሚዲያዎችን እና ተጠቃሚዎቻቸውን በማውገዝ እና፣ በማንቋሸሽ ቢጠመዱም፥ የሚዲያዎቹን ሚና የሚያጣጥሉት እንዳልሆነ እየመሰከሩ ነው። የሚሸበሩት በመግባባታችን መሆኑን እየተናገሩ ነው። ቆዩ! ፍቅረኛቸው ብንሆን ኖሮማ “ብቻዬን ላገኝሽ ብጓጓ፣ ኢንተርኔት እስካቋርጥ… ስልኬን እስካዳፍን ድረስ ራድኩልሽ” ብለው ግጥም ሳይጽፉልንም አይቀሩ ነበር።
 
“ሥራ ያጣ ቄስ ቆብ ቀዶ ይሰፋል” ሲባል ዝም ብሎ ነገር ማሳመሪያ ተረት እንደኾነ አድርገው ቆጥረውት ይሆናል። የረባ ነገር አስበው አያውቁምና አልፈርድባቸውም!
 
የሕዝብን ገንዘብና የአገርን ሀብት እየበዘበዙ በሙስና ሲጨማለቁ፥ ‘ኢኮኖሚውን ምን ቀይሰን እናሳድገው? ምን የሥራ መስክ እንፍጠርለት? እንዴት እናሳትፈው፣ በገዛ አገሩ እንዲሰማው ያደረግነውን የእንግዳነት ስሜቱን በምን እንቅረፍለት?’ ብለው ተጨንቀው የማያውቁለት ስንትና ስንት ተመርቆ ቁጭ ያለ ለጋ ወጣት፣ ሥራ ፈልጎ ቢያመለክት ያሸበረቀ የባለሞያ ሲቪው እንዲታይለት ዘመድ ወይም የፖለቲካ ተሳትፎ እያስፈለገው፥ ተስፋ ይኾናል ሲባል ከኅሊናው ጋር እየተሟገተ ተስፋ ቆርጦ ቁጭ ያለ ወጣት፣ ከቤተሰብ በሚያገኘው ድጎማም ቢሆን ኢንተርኔት ላይ ቢጣድ፥ በሥራ ተጠምዷልና ስጋት ይቀንሳል።
 
ሌላም፥ ተጠቃሚውም ሰው በሚጽፋቸው ስታተስ አፕዴቶች እና በሚሰጣቸው አስተያየቶች የተነሳ “እየታገልኩ ነው” ብሎ ማሰቡና ራሱን ማጽናናቱ አይቀርም። ኢንተርኔቱ ሲቋረጥ ግን፥ በየፌስቡኩ መገናኘት የለመደ ሰው፣ መንደር የመቀየር ያኽል face to face መገናኘትን ማሰቡ አይቀርም። ይኼ ትንበያ አያሻውም። የኖርንበት ነው።
 
ቤት ውስጥ ሆነን፣ ኢንተርኔት ሲቋረጥ ከፌስቡክ ወጥተን ቤተሰቦቻችን ጨዋታ መሀል ገብተን እናውቃለን። ለጨዋታም ቢሆን ቤተሰቦቻችን ለቁም ነገር ሊያገኙን ሲፈልጉ የኢንተርኔት አፓራተሶቻችንን ደብቀውብን ያውቃሉ። ኔትዎርክ ሲቋረጥ ለሻይ ተሰብስበን ስልኮቻችንን መነካካቱን ትተን እርስበርስ ማውራት ጀምረናል። ያለንበትን የኑሮ ዓይነት እና አካባቢውን ቃኝተን “ምን እናበርክት?” ብለናል። ደጃፍ ላይ እንኳን “ችግኝ እንትከል” ተባብሎ የሚስተባበረው ከኢንተርኔት ላይ ወጥተው ሰፈር ውስጥ ሲገኙ ነው።
 
አንክድም፥ ዕውቀት ገብይተንበታልና የኢንተርኔት ሱሰኞች ኾነናል! ብድግ ብለው፣ ያላስታመሙት ሱሰኛ ሱስ ላይ በር መዝጋት ምን ዓይነት ተጽህኖ እንደሚፈጥር፥ የጭቆና እና የገዳይነት ሱሰኞች ናችሁና አይጠፋችሁም። አሁን ምን ጎድሎበትና ምን አግኝቶ ፌስቡክ ውስጥ ሲሸሸግ ሱሰኛ እንደሆነ ያውቃል። ሳይወድ በግዱም የጎደለበትን ይፈልጋል። ምስጋና ግንኙነት ያቋረጠ መስሎት፣ በአካል የመራራቅ ምሽጉን እየሰበረ ላለው አምባገነኑ መንግስት!
 
አሁን መንግስት ወጣቱን ለቁም ነገር ሳይፈልገው አልቀረም ኢንተርኔቶችን ዘግቷል። እንጂማ ሰላሙን ቢፈልግ፣ እንኳን ኢንተርኔት ሊያጠፋ፣ ዜንጦ ስልኮች (smart phones) የሌላቸውን ኹሉ ከሲም ካርድ እና ነጻ የአየር ሰዓት ጋር እያስታጠቀ በየማኅበራዊ ድረ ገጾች እንዲመሽግ ያደርገው ነበር። 🙂

ግድቡማ

እንገንባ ሲሉን ግድቡን ነው ብዬ
ቦንድ ግዙ ሲሉን ለልማት ነው ብዬ፣
ለካስ ለምሽግ ነው፥ ለሚሸጎጡበት…
ሲያጥለቀልቃቸው ጎርፍ ሆኖ ዕንባዬ!
 
ይኸው ደግሞ ወደንም ኾነ ተገደን፣ ላባችንን ጠብ አድርገን እያስገነባን ባለው “የአባይ ግድብ” ማስፈራራት ጀምረዋል። እንደምናየው እያስፈራሩን ያሉትም በራሳችን ንብረት ነው። የሕዝብ ብሶት ጦር ኾኖ ሲንቀለቀልባቸው፣ አባይን ተጋሸን (ጋሻ ሁነን) እያሉት ነው።
 
አሁን ነው “ወንድምና ወጥ ማስፈራሪያ ነው።” ብለው ሚሸልሉት። ግን እንጀራው ሲሻግት ወጡ በስትራው አይመጠጥ! እንጀራው ሲደርቅ ወጥ ትሪ አያስፈራራ! ደግሞ ተገንብቶ ኃይል ሲያመነጭስ ለእኛ ይትረፍ አይትረፍስ በምን እናውቃለን? እኛን በጨለማ “የሽንብራው ጠርጥር”ን እያስዘፈኑ ለሌሎች አፍሪካ አገራት መብራት እየቸበቸቡትም አይደል?
 
እኛ ቁርበት ላይ ስንቆራፈድ በስንትና ስንት ሚሊዮን ብር ቪላ አንጣለውም አይደል? ለቀድሞው ፕሬዝዳንት አቶ ግርማ ወልደ ጊዮርጊስ ሳይቀር በወር 450 ሺህ ብር ቤት ኪራይ እየከፈሉ፣ ሰውዬውን ገዳም ገብተው ንስሀ እንዳይቀበሉ (እሳቸውን እንጥቀም ብለው ይሁን አከራዩን፥ እነሱ ያውቃሉ።) የከለከሏቸው በሕዝብ ገንዘብ አይደል?
 
ከዘፍጥረት አንስቶ፣ ገነትን ያጠጣ የነበረ፣ ከኤደን የፈለቀው የጊዮን ወንዝ እንደው ከአምባገነኖች ጋር ሕብረት አይኖረውም። ጩኸታችንንም ይዞት ይሄዳል። የምናምነው ያየናል። እንኳን ባሮቹን ሊፈጅ የመጣ መሰሪ ስርዓት፥ ይኹን ሲባል የኢያሪኮ ቅጥርም ከመውደቅ አልዳነም። ፈርኦን ከነጭፍሮቹም አልተረፉም። መልከ ጼዴቃዊ ሹመት ለግፈኞች ቃል አልተገባም።
 
የጊዜ ጉዳይ ነው እንጂ ሁሉም ሂሳቡን ያወራርድ ዘንድ ግድ ነው!