ምስጋና እና ብርታት

የሰው ልጅ ብቻውን እንደሆነ እንዳይሰማው፣ እንዳይሰለቸውና እንዳይፈራ በነገሩ ሁሉ በዓላማ መኖሩን እንዲያውቅና እንዲረዳ፣ ፈጣሪ ዓይኖቹንና ጥርሶቹን አጎራበታቸው። ዙሪያውን በሰው ልጆች አጠረው። ስሜቶቹን አሰለፈለት። ጊዜንም በወቅት ከፋፈለ: ክረምት፣ ፀደይ፣ በጋ፣ በልግ…ጨለማ እና ብርሀን… ጠዋት እና ማታ… እርሻ እና አዝመራ… ኀዘን እና ደስታ። ትዝታን እና ተስፋንም በልቡ አኖረለት። አጢሀት እና ይቅርታንም በመንገዱ ላይ አቆመ። ከአፈርና ከአጥንት እፍ ብሎ የምድርን ጾታ አሰባጠረ። ለዘወትር ድካሙ እንዲሆን፥ ካለአጀንዳም አላስቀረውም።
 
“ፀሐይ ይሁን” ቢል፥ ፀሐይ ሆነ። ጨረቃና ከዋክብትን፣ ነፋስና ውሀንም እንዲህ አፀና። ሥነፍጥረት ሁሉ በቃሉ ተከናወኑ። የሰው ልጅን ከነአስገራሚ መላመዱ እና ከነጥበቡም በእለተ አርብ ፈጥሮ ፍጥረታትን አስገዛለት። መንገድንም አመላከተው። በተሰጠው ላይ የሰው ልጅ እየጨመረበት ነገር ሁሉ ይበልጥ ውብ ሆነ። ፍቅርን ምድር ላይ ዘራ። ስለመኖሩ ምልክት እንዲሆኑት፣ እንዲጽናና እና እንዲበረታበት ለሁሉም አንጻርና ወዳጅ አላሳጣውም። ሲለቀስ ለሲቃ ጥርስ ይነከሳል፣ አፍንጫም ከጥርስ የሚሰበስበው አቅም አለ። ሲሳቅም አይን አብሮ ይስቃል እንጂ የጥርስ ድርድር መታየት ብቻ ሳቅ አይባልም።
 
አዋራና ጎርፍ ይፈራረቃሉ። ህጻናት ያድጋሉ። ወጣትነት ሲሰሰት ያልፋል። ጉልምስና በክፋት፣ በ“ካለ’ኔ”፣ እና በራስ ወዳድነት ይጠቀረሻል። ያልለገሙበት ጊዜ ወራዙት ግን ከራስ አልፎ ዙሪያንም ያበለጽጋል። ልብ የሰበሩለት ጉልምስናም ጌጥ ለሚሆን ሽምግልና ይገነባል። ውብ አበባ፣ ጣፋጭ ፍሬ እና እሾህ ካንድ ዛፍ ላይ ይበቅላሉ። ሁሉም እንደመድረሱ ልክ እና እንደመሻቱ ይለቅማል። ዕድሉ ሆኖ፥ ካማረ መስክ ላይ መጣል የሚቀናው አይጠፋም። ለፍሬ ብሎ ተንጠልጥሎ እሾህ መያዝና መፈተንም አለ። ፀንተው ቢቆዩ ፅናት ወደፍሬው ያሻግራል። ደግሞ ‘እሾህ ነው ዕጣፈንታዬ’ ብለው ቀድመው ሲያማርሩ፥ ፍሬ ታድሎ በረከት መቁጠርም የሰው ልጅ እጣ ፈንታ ውስጥ ይገኛል። እግዚአብሔር “ይሁን” ሲል ግን፥ አንዲት ጀምበር ይበቃል!
 
“ነገር ሁሉ ያደክማል፤ ሰው ይናገረው ዘንድ አይችልም፤ ዓይን ከማየት አይጠግብም፥ ጆሮም ከመስማት አይሞላም።”ና ቆመን መሄዳችን እስኪደንቀን ድረስ በዓይን እና በጆሯችን አሳልጦ የገባ መአት ጉድ እንታጨቃለን። ግን እንኖራለን። ከብዶን የወደቅን እንደው፥ ጉዱም ጉድ አይሆን። …ከእናታችን ማህጸን ጀምሮ ታውቀን እስከራስ ፀጉራችን ድረስ ተቆጥረናል። ይተናነቀናል እንጂ፥ “በእምነት ሆናችሁ ተራራውን ሂድ በሉትና በመደነቅ ኑሩ” ተብለናል።
 
ስሜት ቦታና ጊዜው ሲገጥምለት ጽንስ ይሆናል። እናት ልጇ ቢራብ ጡቷ ላይ ህመም ይሰማታልና በዚያ ታውቃለች። አድጎ፥ እንኳን ህመም፣ ከረር ያለ ግጭት ውስጥ ቢገባ እንኳን ሳይነገራት እንድታውቅ የፈጣሪ ድንቅ ሥራ ነው። ደግሞ ሽል ሳይቀር ድምጽና ወሬ ይለያል። ተክሎችም በሙዚቃ ይፈነጥዛሉ። ጠፉ ሁሉ በልባዊ ፈገግታ ይለመልማል። የተፈጥሮ ዑደት፣ የእጽዋት እና እንስሳት እድገትና መዝናናት፣ የዘመናት መፈራረቅ፣ የወቅቶች ማለፍ፣ የእጁ ሥራ ሁሉ አይጓደልም። ሰው ሲሞት፥“ዋርካው ወደቀ” ተብሎ በሀዘን ቢረገድ፥ ሺህ ዋርካዎች ከሥር ይወለዳሉና በዚያ መጽናናት ይሆናል። “ቆሜያለሁ” ቢሉም መውደቅ አይቀርምና ልብ ብለን ብናይ ማስታወሻው ብዙ ነው። ድንቅ ነው!
 
ተመስገን! ፀሐይና ጨረቃን ሰው አይፈቅድም። ብርድና ሙቀትንም ሰው አይከለክልም። ፍቅርን ሰው “ይሁን… አይሁን” አይልም። ስለዚህ ካለን፥ ምን ሌሊቱ ቢረዝም፣ ሲነጋ ጠዋት መሆኑ አይቀርም። ከቆየን፥ ደመናው አልፎ ፀሐይ ይሆናል። ይኽ እውነት ነው የሚያበረታን!
 
ፍቅርና ማየት ምርኩዝ ሆነውኝ እኖራለሁ። ጭጋጋም ቀናትን ተሻግሬ ብርሃናቱን አቅፍ ዘንድ፣ ዳፍንታም ቀናትም እንዲሸማቀቁ የፈጣሪ ቃል ነውና አይታጠፍም። ደግሞም የቀደመ ልምድ ያበረታል እንጂ፥ ተመልሰው በቦታ እና ጊዜ ለውጥ እንደሚመጡም አውቃለሁና እግዚአብሔር መርሳትን አያድርግብኝ።
 
አሁን ደምና ጦር አስደንግጠው እንደሚያደነድኑት ዓይነት፥ የጠላትም የወዳጅም ቅይጥ መንፈሶች ስንቅ ሆነውኛልና በፍጹም አልፈራም! ለዚህ በሰማይና በምድር፣ ከተጻፈው እና ካልተጻፈው ብዙ ምስክር አለኝ!
 
ሃሌ ሉያ!

ዝክረ እረፍቱ ለምኒልክ

emperor-menelik-ii«….ማንም ሰው ለመማርና ለመሠልጠን መድከም አለበት።» ~ አፄ ምኒልክ በ፲፰፻፺፰ ዓ.ም ስለትምሕርት ያስነገሩት አዋጅ [ዘውዴ ረታ “ተፈሪ መኮንን – ረዥሙ የሥልጣን ጉዞ” (ውክፔዲያ ላይ እንደተጠቀሰው)]
 
ከአፄ ምኒልክ የአዋጅ ቃል የምረዳው እውነት፥ ማንም ለመጠንከርና ለመሰልጠን ቢፈልግ፥ በቅድሚያ መድከም እንዳለበት ነው። ‘መድከም’ን የተረዳሁት ደግሞ በሁለት መልኩ ነው፤ – የመጀመሪያው፥ ‘መልፋት፣ መጣር፣ መጋር…’ ሲሆን፥ ሌላኛው ደግሞ ‘ድክመትን ማስተናገድና በደካማነት መስመር መጓዝ’ ብዬ ነው። …ብዙ ጊዜ ቁጭ ብሎ ሲሳይና አዱኛ የለም። ድንገት ቢኖር እንኳን፥ እጅና እግርን አጣጥፎ መማርና መሰልጠን፣ ማደግና መሻሻል ሊመጡ አይችሉም።
 
ደግሞም እንደ ጊዜና ሁኔታው ለመማርና ለመሰልጠን በደካማነት መስመር መጓዝ ግድ የሚል ቅድመ ሁኔታ (input) ባይሆንም፥ ሰው በጉዞው መሀል ቢደክም ያ ጤነኛና ማንንም ሊያጋጥም የሚችል ነገር መሆኑን እናውቃለን። ዋናው ነገር ግን የቀደሙት የፈፀሙትን ድክመት/ስህተት እኛ እንዳንደክም ማሰብ ነው። …እነርሱ ከተጓዙበት ጎዳና በተሻለ እኛ መረማመድ የምንችል ስለመሆን መጨነቅ ነው። …የቀደሙት በእሾህ እና በቆንጥር ያጠሩት ጎዳና ቢኖር፥ ደግሞ በመልካም የጠረጉትም ጎዳና አለና፥ በርሱ ገብተን ቆንጥርና ሾህ ያለበትን መንገድ በማፃዳት ለመጪው ትውልድ የተሻለ መንገድ ማበጀት ነው። …እንጂ ታሪክ ለመማሪያና ዛሬን ለማሻሻያ ሳይሆን፥ ዝም ብሎ ለመራቀቅና ጨዋታን ለማሳመር ፍጆታ የሚውል የሚጠቅም አይመስለኝም።
 
የእኛ ሰው፥ ሲወድና ሲያደንቅ የቅዱሳንን ደረጃ ሰጥቶ… የወደደው ሰው ፍፁም የማይሳሳት፣ የሰውነት ግብሮች የሌሉት አድርጎ የመሳል አባዜ ስላለበት፥ አፄ ምኒልክን በሚወዷቸው ሰዎች ልብ ዘንድ እንዳለው የቅዱሳን ደረጃ ሊኖራቸው አይችልም። …ደግሞም እንዲሁ፥ የእኛ ሰው፥ ሲጠላና ሲጠምድ የሰይጣንን ደረጃ ሰጥቶ… የጠላው ሰው ፍፁም የማይረባ፣ ጭራሽ የሰው ልብ የሌለው ተልካሻ አድርጎ የመክሰስና የመውቀስ ዝንባሌም አለና፥ አፄ ምኒልክን በሚወነጅሏቸው ሰዎች ልብ ዘንድ እንዳለው ዓይነት በመጥፎ ሥራ ብቻ የሚታወሱ አይደሉም። ጭራሽ ስማቸውን ለምን ሰማሁ ማለትም ከነውርም አልፎ አደገኛ አላዋቂነት ነው።
 
ዛሬ አንገታችንን ቀና አድርገን ከነድህነታችን በኩራት ቀጥ ብለን የምንራመድበት የአድዋ ድል፥ የአፄ ምኒልክ የመሪነት ውጤት ነው። አዳዲስ ነገሮችን ወደ ሀገር ለማስገባትና ስልጣኔዎችን ለማስተዋወቅ መጣራቸውና በብዙ ማሳካታቸውም አይዘነጋም። ታዲያ እንዲሁም፥ ግዛትን በማስፋትና የሳሉትን የኢትዮጵያ አንድነት ወደመሬት አውርዶ በማስፈፀም ስሜት በርሳቸው የተበደሉ ዜጎችም አሉ። ያ ያለፈ ታሪክ ነውና ዛሬ ላይ መልሰን ማኖር (undo ማድረግ) የምንችለው አይደለም። ‘ይቅርታ እንጠያየቅ አካኪ ዘራፍ’ የሚያስብልም አይመስለኝም። ዛሬ ያ እንዳይደገም መታገል ግን እንችላለን። …የቀደሙት የፈፀሙትን ስህተት በማረም ሽፋን እኛ ደግሞ የከፋውን ስህተት እንዳንፈፅም መጠንቀቅ አለብን።
 
የዛሬ 103 ዓመት በሰላም ያንቀላፉትንና የነበሩበት ስርወ-መንግስት (regime) ያከተመውን መሪ ትተን፥ ዛሬም በሕይወት ያሉ ብዙ በደለኞችና ጨካኞችን የሚያስተዳድሩ ስርዓቶች (systems) ~ መሪውም ተቃዋሚውም ጎራ ~ አሉና፥… ከትናንት ጋር ውኀ ወቀጣ ስንታገል፥ ዘነዘናና ሙቀጫችን ዛሬን እንዳናይ ለራሳችን ደንቃራ እንዳይሆን መጠንቀቅ አለብን። ….ዛሬ የትናንትን ጥፋት በማውገዝና በመቆርቆር ሰበብ ታሪክ እያነሳን እየጣልን ስንወሸክት፥ የከበደውን ጥፋት እንዳንፈፅም ማሰብ ይገባናል። …በጊዜ ወደኋላ ሩቅ ሳንሄድም፥ ዛሬ እየተሰራ ያለውን ታሪክ ነገ ሲፃፍ እንዴት ሊያምርና የሚያስቆጣቸውን ሰዎች ሊቀንስ እንደሚችል በማጤን የራሳችንን ኃላፊነት ስለመወጣት ብናስብ ትርፉ ይበዛል።
«እናንተ አንድ ልብ ከሆናችሁ በምቀኝነት እርስ በርሳችሁ ተዋግታችሁ ካላለቃችሁ በቀር ኢትዮጵያን አገራችንን ለሌላ ለባእድ አትሰጧትም፤ ክፉም ነገር አገራችንን አያገኛትም። ነፋስ እንዳይገባባችሁ አገራችሁን በያላችሁበት በርትታችሁ ጠብቁ፤ ወንድሜ ወንድሜ እየተባባላችሁ ተደጋገፉ፤ የኢትዮጵያን ጠላት ተጋግዛችሁ ተደንበር መልሱ። የኢትዮጵያ ጠላት ባንዱ ወገን ትቶ ባንድ ወገን ቢሄድና ደንበር ቢገፋ፤ በኔ ወገን ታልመጣ ምን ቸገረኝ ብላችሁ ዝም አትበሉ፤ ያ ጠላት በመጣበት በኩል ኁላችሁም ሄዳችሁ አንድነት ተጋግዛችሁ ጠላታችሁን መልሱ እስከ እየቤታችሁ እስኪመጣ ዝም ብላችሁ አትቆዩ» ~ ዳግማዊ ዓፄ ምኒልክ፤ ግንቦት ፲ ቀን ፲፱፻፩ ዓ.ም. (አፈወርቅ ገብረኢየሱስ፣ (፲፱፻፩ ዓ/ም) ውክፔዲያ ላይ እንደተጠቀሰው።)
 
ዝክረ እረፍቱ ለምኒልክ ❤ !
ነፍስህን በገነት ያኑራት!
ሴትን አንኳስሶ የሚናገር ከራሱ ነው ክህደት የሚፈፅመው። ያ ባይሆን ደግሞ፥ አለማወቁን ነው የሚገልጠው። ይገልጠው አለማወቅ ባይኖረው፥ አውቆ ቸል ማለቱን ያሳያል። ወይም፥ ከእውቀቶቹ ሁሉ “ሴት”ን በአግባቡ ማወቅ ጎድሎት ሳይሆን አይቀርም። ወይ ደግሞ፥ ያልተጣራ የውስጥ ችግር ይኖራል። – እንጂማ፥ “ካላበደ በቀር ዱባ ቅል አይጥልም” እንዲሉ፥ ማንም ስለፆታው ያደረገው አስተዋፅኦ በሌለበት ሁኔታ፥ ፆታው ከርሱ የተለየውን ዝም ብሎ አይፈርጅም።
 
ሴት የሚለው ቃል እንደ ቅፅል፥ ፆተኝነትን አቀንቃኝ ያልተገባ ልማዳዊ አጠቃቀም እንዳለው ቢታወቅም፥ እንደ ስም፥ የወል መጠሪያ ነው። …እንደ ወል ስም፥ ሴት: ከሊቅ እስከ ደቂቅ፣ ከመሀይም እስከ ምዑር፣ ከቤት እመቤት እስከ ድርጅት እመቤት፣ ከምንዝር እስከ አለቃ፣ ከወላድ እስከ መሀን፣ ከወታደር እስከ ጦር መሪ፣ ከአገልጋይ እስከ እመ ምኔት፣ ከፀሐፊ እስከ አንባቢ… ሌላም ከ—እስከ ተብሎ ተዘርዝሮ የማያልቅ የተለያዩ የኑሮ እርከኖች ላይ የሚገኙ፣ በተፈጥሮአዊ ባህርያቸው እንስት የሆኑ ሰዎች ተለይተው ይታወቁበታል።
 
“ሴት” ብሎ በጅምላ የሚዘልፍ፣ የሚሰድብና ደምሳሳ ድምዳሜ (hasty generalization) የሚያደርግ ፆተኛ፥ የስኬት መሰረት የሆኑ የታፈሩና የተከበሩ ሴቶችን ታሪክ አያውቅም። ወይም እያወቀ እንዳላወቀ ሆኗል። …እያወቁ እንዳላወቁ መሆን ደግሞ ካለማወቆች ሁሉ የከፋና በራስ ጥመት የሚመጣ በመሆኑ፥ ይበልጥ የማህበረሰብ እና የጋራ ግንዛቤዎች ጠንቅ ይመስለኛል።