
ከአፄ ምኒልክ የአዋጅ ቃል የምረዳው እውነት፥ ማንም ለመጠንከርና ለመሰልጠን ቢፈልግ፥ በቅድሚያ መድከም እንዳለበት ነው። ‘መድከም’ን የተረዳሁት ደግሞ በሁለት መልኩ ነው፤ – የመጀመሪያው፥ ‘መልፋት፣ መጣር፣ መጋር…’ ሲሆን፥ ሌላኛው ደግሞ ‘ድክመትን ማስተናገድና በደካማነት መስመር መጓዝ’ ብዬ ነው። …ብዙ ጊዜ ቁጭ ብሎ ሲሳይና አዱኛ የለም። ድንገት ቢኖር እንኳን፥ እጅና እግርን አጣጥፎ መማርና መሰልጠን፣ ማደግና መሻሻል ሊመጡ አይችሉም።
ደግሞም እንደ ጊዜና ሁኔታው ለመማርና ለመሰልጠን በደካማነት መስመር መጓዝ ግድ የሚል ቅድመ ሁኔታ (input) ባይሆንም፥ ሰው በጉዞው መሀል ቢደክም ያ ጤነኛና ማንንም ሊያጋጥም የሚችል ነገር መሆኑን እናውቃለን። ዋናው ነገር ግን የቀደሙት የፈፀሙትን ድክመት/ስህተት እኛ እንዳንደክም ማሰብ ነው። …እነርሱ ከተጓዙበት ጎዳና በተሻለ እኛ መረማመድ የምንችል ስለመሆን መጨነቅ ነው። …የቀደሙት በእሾህ እና በቆንጥር ያጠሩት ጎዳና ቢኖር፥ ደግሞ በመልካም የጠረጉትም ጎዳና አለና፥ በርሱ ገብተን ቆንጥርና ሾህ ያለበትን መንገድ በማፃዳት ለመጪው ትውልድ የተሻለ መንገድ ማበጀት ነው። …እንጂ ታሪክ ለመማሪያና ዛሬን ለማሻሻያ ሳይሆን፥ ዝም ብሎ ለመራቀቅና ጨዋታን ለማሳመር ፍጆታ የሚውል የሚጠቅም አይመስለኝም።
የእኛ ሰው፥ ሲወድና ሲያደንቅ የቅዱሳንን ደረጃ ሰጥቶ… የወደደው ሰው ፍፁም የማይሳሳት፣ የሰውነት ግብሮች የሌሉት አድርጎ የመሳል አባዜ ስላለበት፥ አፄ ምኒልክን በሚወዷቸው ሰዎች ልብ ዘንድ እንዳለው የቅዱሳን ደረጃ ሊኖራቸው አይችልም። …ደግሞም እንዲሁ፥ የእኛ ሰው፥ ሲጠላና ሲጠምድ የሰይጣንን ደረጃ ሰጥቶ… የጠላው ሰው ፍፁም የማይረባ፣ ጭራሽ የሰው ልብ የሌለው ተልካሻ አድርጎ የመክሰስና የመውቀስ ዝንባሌም አለና፥ አፄ ምኒልክን በሚወነጅሏቸው ሰዎች ልብ ዘንድ እንዳለው ዓይነት በመጥፎ ሥራ ብቻ የሚታወሱ አይደሉም። ጭራሽ ስማቸውን ለምን ሰማሁ ማለትም ከነውርም አልፎ አደገኛ አላዋቂነት ነው።
ዛሬ አንገታችንን ቀና አድርገን ከነድህነታችን በኩራት ቀጥ ብለን የምንራመድበት የአድዋ ድል፥ የአፄ ምኒልክ የመሪነት ውጤት ነው። አዳዲስ ነገሮችን ወደ ሀገር ለማስገባትና ስልጣኔዎችን ለማስተዋወቅ መጣራቸውና በብዙ ማሳካታቸውም አይዘነጋም። ታዲያ እንዲሁም፥ ግዛትን በማስፋትና የሳሉትን የኢትዮጵያ አንድነት ወደመሬት አውርዶ በማስፈፀም ስሜት በርሳቸው የተበደሉ ዜጎችም አሉ። ያ ያለፈ ታሪክ ነውና ዛሬ ላይ መልሰን ማኖር (undo ማድረግ) የምንችለው አይደለም። ‘ይቅርታ እንጠያየቅ አካኪ ዘራፍ’ የሚያስብልም አይመስለኝም። ዛሬ ያ እንዳይደገም መታገል ግን እንችላለን። …የቀደሙት የፈፀሙትን ስህተት በማረም ሽፋን እኛ ደግሞ የከፋውን ስህተት እንዳንፈፅም መጠንቀቅ አለብን።
የዛሬ 103 ዓመት በሰላም ያንቀላፉትንና የነበሩበት ስርወ-መንግስት (regime) ያከተመውን መሪ ትተን፥ ዛሬም በሕይወት ያሉ ብዙ በደለኞችና ጨካኞችን የሚያስተዳድሩ ስርዓቶች (systems) ~ መሪውም ተቃዋሚውም ጎራ ~ አሉና፥… ከትናንት ጋር ውኀ ወቀጣ ስንታገል፥ ዘነዘናና ሙቀጫችን ዛሬን እንዳናይ ለራሳችን ደንቃራ እንዳይሆን መጠንቀቅ አለብን። ….ዛሬ የትናንትን ጥፋት በማውገዝና በመቆርቆር ሰበብ ታሪክ እያነሳን እየጣልን ስንወሸክት፥ የከበደውን ጥፋት እንዳንፈፅም ማሰብ ይገባናል። …በጊዜ ወደኋላ ሩቅ ሳንሄድም፥ ዛሬ እየተሰራ ያለውን ታሪክ ነገ ሲፃፍ እንዴት ሊያምርና የሚያስቆጣቸውን ሰዎች ሊቀንስ እንደሚችል በማጤን የራሳችንን ኃላፊነት ስለመወጣት ብናስብ ትርፉ ይበዛል።
«እናንተ አንድ ልብ ከሆናችሁ በምቀኝነት እርስ በርሳችሁ ተዋግታችሁ ካላለቃችሁ በቀር ኢትዮጵያን አገራችንን ለሌላ ለባእድ አትሰጧትም፤ ክፉም ነገር አገራችንን አያገኛትም። ነፋስ እንዳይገባባችሁ አገራችሁን በያላችሁበት በርትታችሁ ጠብቁ፤ ወንድሜ ወንድሜ እየተባባላችሁ ተደጋገፉ፤ የኢትዮጵያን ጠላት ተጋግዛችሁ ተደንበር መልሱ። የኢትዮጵያ ጠላት ባንዱ ወገን ትቶ ባንድ ወገን ቢሄድና ደንበር ቢገፋ፤ በኔ ወገን ታልመጣ ምን ቸገረኝ ብላችሁ ዝም አትበሉ፤ ያ ጠላት በመጣበት በኩል ኁላችሁም ሄዳችሁ አንድነት ተጋግዛችሁ ጠላታችሁን መልሱ እስከ እየቤታችሁ እስኪመጣ ዝም ብላችሁ አትቆዩ» ~ ዳግማዊ ዓፄ ምኒልክ፤ ግንቦት ፲ ቀን ፲፱፻፩ ዓ.ም. (አፈወርቅ ገብረኢየሱስ፣ (፲፱፻፩ ዓ/ም) ውክፔዲያ ላይ እንደተጠቀሰው።)
ዝክረ እረፍቱ ለምኒልክ ❤ !
ነፍስህን በገነት ያኑራት!