እደጃፌ ወድቆ
ሳየው ኑሬ ኑሬ
ወዳጄ ሲያነሳው፣ ውድነቱን አውቆ
በንፍገት ደንብሬ፥
ልቤ ሊያብድ ተጨንቆ፣
ነፍሴ ሊበር ወልቆ፣ ስጋዬን አሳቅቆ።
እደጃፌ ወድቆ
“ለእግዜር” እንኳ ባልል፣
ለዐይኔ ተቆርቁሬ
ሳላነሳ ትቼው፣
ሲንደፋደፍ ከእግሬ
የቀረን ምስኪን ሰው
ስለነፍስ ያደረ ሳምራዊ ሲያነሳው፥
መጽደቁን ቆጥሬ፣
የደጉን ተጋድሎ፣ ባገር መወደሱን
በሀሳቤ ዘርዝሬ፣
በቁጭት ተቀጣሁ፣
ዋልኩኝ ተንጨርጭሬ
በክፋት ደንብሬ፣ በቅናት ታጥሬ።
* * *
ነገር ግን ይገርማል!
ወዳጅ ባየው ቅጽበት
ባነሳበት አፍታ፥
በተመኘው ጠዋት፣
ባጌጠበጥ ማታ፥
የጣሉት ይከብራል
ዋጋው ይጨምራል።
* * *
ጥፍጥናዬን ምጎ፣ መረቄን ጨርሶ
ከአውላላ ሜዳ ላይ የተፋኝ አንኳሶ፥
ስደክም የዘረረኝ፣ ስወድቅ የረገጠኝ
ስንከራተት ደጁ፣ ያልጣለልኝ ከእጁ
ያልነበርኩ ወዳጁ፥ ቆለለኝ ስነሳ
ካበኝ በየፈርጁ፣ ሰፈረልኝ ካሳ።
* * *
ለካስ ለመላ ነው የሚለው አገሩ፥
“የወደቀን አንሱ፣ የሞተን ቅበሩ”
ካለፈ እንዲማሩ፣ በወግ እንዲኖሩ
እጃት እንዲጥሩ፣ ዐይናት እንዲበሩ።
/ዮሐንስ ሞላ/