ኧረ ገንዘቤን ለቀቅ!

አንዳንዱ ግንድ ተሸክሞ “አባይ ማደሪያ የለው”ን ሲተርት ዕድሜውን ይፈጃል።
 
ገንዘቤ ባንዲራው ኮከብ ስለሌለበት አስቀምጣው ሄደች ብሎ፣ እየተመላለሱ “አገር ይያዝ” ማለት ምንድን ነው? (“ወረወረችው” ማለት አጓጉል ግነት ነው።)
 
ባለፈው “በ25 ዓመቱ ጎንደር ላይ ታየ” ብለን አልነበር እንዴ ከዳር ዳር ስንፍነከነከ የነበረው? የፖለቲካ ፓርቲ ሰልፍ ቢጠራ ወይ ሕዝባዊ ስብሰባ ቢደረግ፣ ስታዲየም ውስጥ ጨዋታ ሲኖር፣ አገር ውስጥ ኾኖ ኮከብ የሌለበትን የሚጠቀም አለ? 
መንግስትን አጥብቆ እንደሚጠላ እየገለጸ ሰልፍ እና ስብሰባ ሲኖር የሚገኘው እና፣ ለተቃዋሚ እና ለሚዲያ አካላት የ“አይዟችሁ” (emotional support) ድጋፍ ለማድረግ የሚሞክረው ምን ያህሉ ነው?
 
“የሰንደቅ ዓላማ ቀን” ይከበር ብሎ መንግስት አስገድዶ በየሱቁ እና በየቅያሱ ባንዲራ ሲያሰቅል፣ “ይኼ ኮከብ ስላለው አልሰቅልም” ያለ አለ?
ምን ያህል ሰውስ ኮከብ የሌለው ባንዲራ ቤቱ አለ? ቢኖረውስ እንደ አያት ውርስ ጌጥ፣ ከስንት አንዴ እያወጣ፣ መልኩን እያየ ያስቀምጠዋል እንጂ አደባባይ ላይ በሚደረጉ ፌስቲቫሎች ይዞት ይወጣል?
 
ለምንድን ነው እኛ ለማድረግ የምንፈራውን፣ ቤተሰቦቻችን እንዳያደርጉ የምንከላከለውን፣ ወይም ጊዜና ሁኔታ እንዲሁም ቦታ አመቻችተን ያደረግነውን ነገር ሌሎች እንዲያደርጉ የምንጠብቀው? 
 
የ90 ሚሊዮን ሕዝብ ጭንቀት ጀርባቸው ላይ ተሸክመው ሮጠው፣ አንገታችንን ቀና ለማድረግ ደፋ ቀና የሚሉ አትሌቶችን የፕሮፖጋንዳ ቅመም ማድረጉን ትተን፣ የፖለቲካ ሲስተሙን ማብጠልጠል፣ እርስበርስ መባላቱ ተትቶ በጋራ ስለመቆም መምከር የተሻለ ይሆናል።
ካለዚያ ግን በየዘርፉ ጠላት ከማበርከት የተሻለ ሚና አይኖረንም።
China Athletics Worlds
ብዙ ኑሪልን አቦሸማኒት ❤
 
 

‘Crazy baldheads’

እነዚያን አሚኖችማ፣ …ቀልበ ሸፋፋ፣ ዳውላ፣
እነዚያን ልበ-ጠማማ፣ አንጎለ – መላጣ ሁላ፤
ጉድ እንስራቸው ዛሬማ፤
አሳድደን እያሯሯጥን፣ ቂጥ ቂጣቸውን እያልን፣
እናስወጣቸው ይሂዱ፤ …ይራቁ ከእኛ ከተማ፤
(እንኑርበት በአማን፣ ከፍ ብለን እንዋል ከማማ)
አያ ጓዴ፥ ስማኝማ…
እኒህን ልበ-ገመዶች፣ ልበ-ልጥ፣ ሀሳበ-ፍልጦች…
እኒህን ቀውሳን፣ ቀጣፎ’ች፤ አናባ’ራቸው ምጣማ፤
(እኛማ) እኔ እና እኔ፣ ቀለስን ደሳሳ ጎጆ፣
እኔ እና እኔ፣ ዘራን መርጠን በቆሎ፤
ታዲያ ምን ነካው ይህ አውሬ?!…
ቀድሞ እዚህ የነበሩት፥ የእኔ ወገን ታታሪዎች፣
(ጭሰኛ ቢሆን ባላባት፣ ነጋዴ ቢባል ገበሬ)
ጠብ እርግፍ ብለው ያቆሟት፣ ሎሌ አልነበሩ ላገሬ?
በክፉ የሚያንጓጥጠው፣ በክፉ የሚያየኝ ዛሬ?
እሸቴን ሊቅም ቀምቶ፣ ያበቀልኩትን ታትሬ፤
ይሄን ብላ! …ራስታ ቢስ፥ Baldhead!
አነሱ እቴ… ዓለም በቃኙን ቀለሱ፣
አስኳላውን ስናቀና፣ አሳር ፍዳውን አላሱ፤
ቀለሙን አቀጣጠኑት፣ ሞኝ ሊያደርጉን ተላላ፣
(ትምህርቱን አለቃለቁት፥ ሲነጋ እንዳንነቃ ከቶ፣
በድህነት እንድንማቅቅ፣ እንድንለብስ ድሪቶ።)
ሰፍረው ቆጥረው ሸላለሙን …በፍቅራችን ልክ ጥላቻ፤
‘ላይ ስላለው ፈጣሪ ቀባጥረው ባ’ፋቸው ብቻ።
Baldheads!
አያችሁት ይህን አታላይ? ያህን ቀጣፊ፣ ጨንቋራ፥
እኛን በዝርፊያው ሊያሰቃይ፥ (ማልዶ ተነስቶ በግራ)
የጥላቻ ሀዋርያ፥ የሸር የክፋት ቀረፎ፣
ሲገሰግስ ወደ ደጄ የሸፍጥ እቅዱን ሸክፎ፤
ይብላን ላእሱ!… እኛስ መወስለት አያውቀን፣
የብርሃን መንገደኞች፣ የመኖር ናፋቂዎች ነን።
/ነጻ ትርጉም: በዮሐንስ ሞላ/

10968371_719232758197760_1126497837224941388_n

 

P.S. Two years ago, on my Bob Marley’s birthday, I’ve attempted to translate one of my favorites ‘Crazy Baldheads’ to Amharic. Baldhead, ከራስተፈሪያን ውጭ የነበሩ ሰዎች ይጠሩ የነበረበት ስያሜ ነው። ራስታ ያልሆነ… እንደማለት ነው።
Long live Bob Marley‘s soul!