“ኧረ ውሃ ውሃ…” እያለ ውሃን በማሰብ የኖረ፣ አፉ የደረቀበት እና ቧንቧው የዛገበት ሰው፥ የዓለም የውሃ ቀንን በምን አስቦት ይውላል? – በግጥም? ቀናቱ የተጎራበቱትስ ለደሀው ሰቀቀን ማስታመሚያ አማልክቱ ፈርደው ይኾን?
“እንጀራ ሚሰራው በውሃ ነው ብዬ
ውሃን አስቀደምኩት እንጀራዬን ጥዬ” ማለቱም እንደ ቅንጦት ኾኗል።
በእንጀራ ሳያሳብቡም… ድህነትን ለመርሳት ሆነ “ሺህ ዓመት አይኖር” ተብሎ፥ ለብ ያለውን ያንዶቆዱቁታል!
“እንጀራ ሚሰራው ከጀሶ ነው ብዬ
ቤት ማደሱን ተውኩት እንጀራ ከጅዬ” ይባል እንጂ።
ወይ ደግሞ፥
ቢራ መጠጣት
አንድ ለመርካት
አንድ ለመርሳት
(እዚሁ የተሰነኘ አጭሬ :p)
ክፋት ተጭኖን አለን። ከስንቱ ጉድ የተረፈው በጄሶ እንጀራ እና በተቀሸበ ዘይት ቤቱ ድረስ ሞት በወስከምቢያ ይቀርብለታል። ህመምና ኀዘንን ወጥቶ በገንዘብ እንደመግዛት ያለ ክፉ እድል ከወዴት ይገኛል?
አይገርምም ግን? የአገሬ ሰው፥ ክፍቱን በሰው ልጅ ክፋት ተከቦ የሚኖር ከለገዳዲ እና ሌላ ሌላ ጣቢያ፣ በዛገ ቧንቧው በኩል የሚፈስለትን ውሃ አምኖ ሲጠጣ? ውሃ በቧንቧ ከሚደርሰው ቀን ይልቅ፥ ከአይኑ የሚፈሰው እንባ ቀን መብዛቱ? ‘መቼስ በበረከት ነው የሚለቀሰው እንጂ ይኽ ሁሉ ውሃ ከየትኛው የሰውነት ውሃ ይጨመቃል?’ ያሰኛል።
እስኪ ግጥማችንን አንብበን ላሽ እንበል…
ጥም ወለድ ጸሎት
———
ይኸው ከባለፈው፥ ከቤትህ ስወጣ ካየኸኝ ጀምሮ
ጠብ ላይል ነገር፥ “ኧረ ውሃ” እያልኹኝ በደረቅ ጉሮሮ፥
(ሙዚቃ ስቀምር፣ ዜማ ስሰፋፍር፥ ቅኔ ስቆጣጥር፥
ጊታር ስገታትር፣ ክራር ስከረክር፣ ስደልቅ ከበሮ፥. . .)
ሰፈር እያሰስኹኝ፣ አገር እያመስኹኝ፥ በጩኸት በእሮሮ፥
ጀሪካን ሸክፎ፥ መንደር መንደር መዞር ሆኗል የእኔ ኑሮ፤
ላዩም ታቹም ግዑዝ፥ ድንጋይ ሳንቃ መውቀር፣ ባዶ ቤት መቆርቆር፣
ሰውን ከ’ነኅሊናው ወደማያዩበት ሰፊ ኦና ቅፅር፥ በሽንቁር ማጨንቆር፤
ያለቅሱበት ሳይኖር፥ ይደገፉት ክናድ፣
ይጠጉት ምንጭ ሳይኖር – ያበርዱበት ንዳድ፥
ሠርክ መገማሸር፣ ዘወትር “አቤት” ማለት፤
በብላሽ ማባበል፥ ካለቅንጣት ደስታ፣
ካላ’ንዳች እፎይታ፥ ካለቁራጭ ፋታ. . .
ታከተኝ አባቴ!
አቅም አጣሁ ከቶ፥ እጅ እግሬ ታሰረ፥ ገፈተረኝ ቤቴ፣
ፍርሀት አሰለለው፣ ቃተተ አንደበቴ፣
¬ በመውጣት በመግባት ዛለብኝ ጉልበቴ፤
እናም ‘ካህንዬ’. . .
ፍቀድልኝና፥ በልጅ የደም ዋጋ ካቆምኻት ቧንቧ ስር፥ ከደጅህ ልሰለፍ፤
ለነፍሴ ማጠቢያ፥ ባቀናኻት ቀዬ፣ ባጸናኻት መስመር፥ በበራፍህ ልለፍ፤
በጠረግኻት መንገድ፥ በዕውቀት ልመላለስ
¬ ሞገስህን ልልበስ፤ በክብር ልተላለፍ፤
በውኆች መካከል “ትሁን” ካልኻት ሰማይ
¬ በሚነፍሰው ነፋስ በእርካታ ልንሳፈፍ፤
ድርቀት ዐይኑ ይጥፋ፥ ከነሥሩ ይጥፋ፤
¬ ከነነፍሱ ይርገፍ፤ ከነስሙ ይንጠፍ፣ ከምንጩ ይንጣፈፍ!
ለጭንጫው ሕይወቴ፥ ከጭንጫ ውሃ አውጣ፤
በቸርነት እርጨኝ፣ ከበረዶ ልንጣ፤ (እንደ አፈጣጠሬ)
ጥሜን ቁረጥልኝ፥ ካለጭንቅ ልጠጣ፥
ጥም በጥም ይጎዳ! (እንደ ተስፋ ቃልህ)
ነፍሴን ላለቃልቅ፥ ቆሻሻ ይሽሸኝ፣ ለዓለም ዓለም ልጥራ፤
ለይኩን ለይኩን!
ልምጣ ውሃ ልቅዳ።
__________________________
/ዮሐንስ ሞላ “የብርሃን ሰበዞች” ገጽ 67/