እንጉርጉሮ 2

አዬ ስጋ ክፉ፣ አይ ሰውነት ብላሽ፣
ቆሻሻም ነፈገሽ፣ ዛሬስ አፈር በላሽ።
* * *
እዚያ ስርመሰመስ፣ የነበርኩት ጌጡ
ነፍስ የምዘራበት፥ ፈልፍዬ ከውስጡ
አድቦልቡዬ ቅርሻ፣
ትርጉም አወጣለት፣ አበጅቼ ጉርሻ
ከተረፈ ኗሪው፣ ለአኗኗሪው ድርሻ
 
በእኔ ገጽ፣ በእኔ አምሳል፥
ሙሰኛ ጅብ ሆዳም የኖረበት ዋሻ
ላዬ ላይ ተደፋ፣
ይኸው እንደሰዉ፥ ሰለቸኝ ቆሻሻ።
 
ገባሁለት ካፈር፥
ይቀኙ ይጻፉለት፣ ስሄድለት ይክበር።
* * *
ከቆሻሻው ክምር
ከሰው ተራራ ሥር
ነበረኝ ቀጠሮ፣
ለቅሜ ምፈታው የረሀብ ቋጠሮ፤
ከተማ ብመንን ቀን ቢነሳኝ ኑሮ
ሞት ሰው አገናኘኝ አዙሮ ዟዙሮ።
* * *
“እኔን እኔን እኔን፥ እኔን አፈር ይብላኝ”
ብሎ ያበላ ነበር
በቀን ጣ’ይ ተበልቶ፣ ሕዝቤ ባይቸገር
በረሀብ ጥም ተቀጥቶ፣ እጁ ባይጠፈር
ባይቆስል፣ ባይገደል፣ ባይሰደድ ኖሮ፥
ከሰው ጅብ ለመሸሽ፣ ባህር ባይሻገር፤
 
ይጽፈው ነበረ የልቤን እሮሮ
ሽንቁራም አንጀቴን ሚጥፍበት ቢያጣ፥
ተነቅፎ ባይጣል፣ እግር ተወርች ታስሮ
ስለተነፈሰ በአዋጅ ባይቀጣ።
* * *
ከወንዝ ወዲህ ማዶ፣ ከጠነባው ትቦ፣
ማማ ከሰራበት፣ ሰው ቆሻሻ ክቦ
መልክ፣ ሕይወት ነበረኝ
ኑሬ የማላውቀው፣ ኑሮ ሰድቦኝ በአግቦ
በሞት ተጠቁሜ፣ ጎበኘኝ ሰው ከብቦ፤
 
እብለት በደም ረቅቆ
ከተሰደርኩበት፣ ከቆሻሻ መስኩ፣
የጣለው ላይ ደምቆ
በሚጥለው መዓት ከሚታየው መልኩ
የሰውነት ሚዛን፣ የኗሪነት ልኩ
የግፈኛው ሽፎን፣ በዕድገት ማላከኩ
ዐይን ጆሮዬ ሞላ፥
 
ቆሻሻ ጭንቅላት ተለቅሞ ተለቅሞ፣
በየወንበሩ ላይ፣ በየህንጻው ከትሞ
ለስሙ መጠሪያ፣ ለልጆቹ መኩሪያ
ድንጋይ ሲደረድር፣ ሲያንገዋልል ትቢያ
ብርጭቆ ሲያገጫጭ፣ በውስኪ ሲረጫጭ፥
ድሀን ቸግሮት ሳቢያ
ቁንጫ ማስረሻ፣ ሆዱን መመቅነቻ
ሲድህ ሲንከላወስ፣ ልቡ ኑሮ ዛቢያ
ሲተክዝ ለብቻ፤
 
ከዳኝ ሆድ ማከኩ፣
በቃኝ መብሰክሰኩ
ምች አጠናገረኝ፣ አጣሁ ድንገተኛ
ከህንጻው ግም የመጣ ጠለዘኝ መጋኛ
ስሞት ወግ ደረሰኝ፥ እንደሰው ልተኛ።
 
/ዮሐንስ ሞላ/
 
የሞቱትን ነፍስ ይማር! ያዘኑትንም ያጽናና! ለአገራችን እና ለሕዝቡ የተሻለ ቀን ያምጣልን!

ተኖረና – ተሞተ

“ሳለ – ለሌለ”
እየታለ . . . እየተሌለ
በመሸ – ነጋ – መሸ
እንደነበረ . . . እንዳለ
እንዳደረ . . . እንደ – ዋለ
እንዲሁ . . . እንደ – ዋተተ
“መኖር”ን እንደ – ሞገተ
“ኗሪ” ሳይኖር . . .
ኖረ . . . ኖረና – ሞተ።
 
ተኖረ …… ተኖረና……. ተሞተ
ተሞተና – ተለቀሰ
ዕንባ እንደ ጅረት ፈሰሰ
ደረት – እንዳፈር ፈረሰ፤
 
ምድረ ቡትቷም . . . ርንቁስ – ደሀ!
ተቃቀፈና አነባ!
ለማንም . . . ምንም . . . ላይረባ!
 
ግና! . . . ያረፈ
እንዳላረፈ . . . አረፈ
አየ . . . አየና – አለፈ ፡፡
“ትቢያ” ነበር “ትቢያ!” ለበሰ
ለሟች – ኗሪ . . .
ለኗሪ ሟች . . . ወግ ደረሰ!
 
/ሻምበል ክፍሌ አቦቸር/

እንጉርጉሮ

ከአገሩ ቆሻሻ ሕይወቱን ፈልቅቆ ነፍስ የሚዘራበት
ብርቱው ሰው ተረቷል፣
በመሬቱ ንደት ባውሬዎች ተነጥቆ፣ ሸሽቶ ከኖረበት
ዛሬ በሞት ታይቷል።
* * *
ወይ ኑሮ አልሰመረ
ወይ ሞቱ አላማረ
ለቆሻሻ ዓለም፣ ቆሻሻ ሲለቅም፣
ቆሻሻ ሥር ቀረ፥
በታጠፈ አንጀቱ እንዳቀረቀረ።
* * *
ሲተፋ በሚያድር ሰገብጋባ በላ
ቆዳው ሊቀረፈፍ፣ አጥንቱ ሊበላ
ከጀርባው፣ ከፊቱ፣ ቢላዋ ሲሰላ
የጣዩን ግፍ ሸሽቶ፣ በቆሻሻ ጥላ፣
የአባዩን ነውር ንቆ፣ በደከመ ገላ
 
ሞቶ ሞቶ በላ፣
ኖሮ ኖሮ ሞተ
ሰውነት ቃተተ
ስጋ ተራኮተ።
* * *
ተረፈ ሙስና፣ የወንበር ጥቀርሻ፣
የጥርሳት ናሙና፣ የአሳሞች ንክሻ
ጎልቶ ሚታይበት፥
ከሞት ያመለጠ፣ የተረሳ ሕይወት፣
መንኖ ነበረ፣ ከቆሻሻ ዋሻ።
* * *
ወንበር ወንበር ስቦ፣
ስድ ሁል ተሰብስቦ
“ቀልቀሎ ስልቻ፣ ስልቻ ቀልቀሎ”
መናገር ቃል ቀልሎ…
“አትሰደድ” ይላል
(መሰደድ መች ቀላል?
ግብአት ገንዘብ ይሻል)
 
የመስሪያውን ገንዘብ፥ በቀን ተቀራምቶ
ቀን በቀን ሲገደል፣ ሰው በአገሩ ዋትቶ።
* * *
ንግስቲቱ እሌኒ፣ ትፈለግ ትጠራ
ቆስጠንጢኖስ ይድረስ፣
ይፈለግ መስቀሉ፣ ይደመር ደመራ፤
ዕጣን ከርቤው ይጨስ፣
ተራራው ይደርመስ፤
 
በተሰቀለው ሰው አምሳል የተሠራ፥
ፋሲካውን ሳያይ ከነቀራኒዮው፣
ሰው ከነትግሉ፣ ሰው ከነመስቀሉ፣
ሰው ከነሕማማቱ፣ ሰው ከነቁስሉ፣
ሰው ከነትዝብቱ፣ ሰው ከነዕንባ ቅሉ
ተደባልቆ ሞቷል ከቆሻሻው ክምር፣
ተትቶ በሴራ፣ ከቆሼው ተራራ፣
በደም የተገዛ ሕይወት እንደተራ፤
 
“ኤሎሄ…. ኤሎሄ…”
 
ትንፋሽ ሲፈለፍል፣ እስትንፋስ ሊሰራ
የልጆቹ እግዜር፣ የቤቱ አባወራ፤
ኖሮ ተጠቆመ፣ ስሙ በሞት ተጠራ
የማኖር ጥበቡም ታለፈ እንደተራ፤
ሕይወት ሊያመላክት
ለአጉል ኑረት ትርክት
ዝቋላ ተቃጥሎ፣ ጢሱ ቆሼ አረፈ፣
ሕይወት ያጋፋውን፣ ሞት አስተቃቀፈ፤
 
በደሉ ይነገር፣ መገፋቱ ይወራ፣
የፈጠረው ሰው ላይ፣ ፍጡር ሲፈርድበት
እግዜሩ ይጠራ፣
 
“ኤሎሄ… ኤሎሄ…”
 
ይደመር ደመራው፣ ሰማይ ጢሱን ይልበስ
የግፍ የመከራው፣ የኀዘን ተራራ ይፍረስ፤
 
የእናት ዕንባ ይትነን፣ ጽርሀ አርያም ድረስ፥
ታይቶ፣ ተመዝኖ፣ ወደ ምድር ይፍሰስ
ይውረድ ዳምኖ ዳምኖ፣ ዕንባ ዝናብ ሆኖ
ጎርፎ ይጠራርገው፣ አይኑር ባምባው ገንኖ።
 
/ዮሐንስ ሞላ/
 
የሞቱትን ነፍስ ይማር! ያዘኑትንም ያጽናና! ለአገራችን እና ለሕዝቡ የተሻለ ቀን ያምጣልን!