አሰፋ ጫቦ ተገደለ ወይስ ሞተ?

ቬሮኒካ መላኩ 18119501_10212516554410253_4349511308389670468_n

ባለፈው ወር አካባቢ የቦርከና ድረ ገፅ ባለቤት የእለት ስራውን እያከናወነ እያለ ከሌላኛው የአለም ጫፍ ከወደ አውስትራሊያ አንድ አጠር ያለች መልእክት ትደርሰዋለች ። ይች መልእክት ቦርከና የመልእክት ሳጥን ውስጥ በገባችበት ሰአት በሌላኛው የአለም ጫፍ አንድ በሙሉ ጤንነት ላይ የሚገኝ ሰው ዳላስ ውስጥ ምናልባት ራሱ ያፈላውን ቡና ከሲጃራው ጋር እያወራረደ ይሆናል ወይም ደሞ ብዙውን ጊዜውን የሚያዘወትርበት ቤተ መፅሃፍት ቤት ውስጥ ይሆናል ። ሁለቱንም ልማዶቹን በጣም ይወዳቸዋል ። ይህ ሰው በሙሉ ጤንነት ይገኝ የነበረው አሰፋ ጫቦ ነበር ።

መልእክቷ ምን ትላለች?

የቦርከናው ድረ ገፅ ባለቤት መልእክቷን ሲከፍታት እንደዚህ ትላለች

” ሰላም ጠና ይስጥልኝ ። ስሜ ግሪጎሪ ማኬንዚ ይባላል ። አቶ አሰፋ ጫቦ ጋር እንተዋወቃለን ። ሁለታችንም በዓለም በቃኝ እስር ቤት ጓደኛ ነበርን ። እባክህ የአቶ አሰፋ ጫቦን የኢሜይል አድራሻ ላክልኝ። ከምኖርበት አውስትራሊያ ወደ አሜሪካ ስለምጓዝ አሰፋን ማግኘት እፈልጋለሁኝ ። ሁለታችንም ስላረጀን የመጨረሻ እድሌ ሊሆን ይችላል ። ” ይላል

ይች አጭር መልእክት የደረሰችው የቦርከናው ድሜጥሮስ ብርቁ ወድያውኑ ለአቶ አሰፋ በፌስ ቡክ ሜሴጂ በኩል የሚከተለውን መልእክት ይልካል :

” ጋሼ አሰፋ ሰላም ነዎት ወይ? አንድ ግሪጎሪ ማኬንዚ የሚባል ሰው ከወደ አውስትሪሊያ ኢሜሎትን ጠየቀኝ ። ሰውየው በአለም በቃኝ እስር ቤት አብረን አሳልፈናል እያለ ነው ። ጓደኛየ ነበሩ ብሏል ። ግለሰቡን ያውቁታል ወይ ? ” በማለት ይፅፍላቸዋል ።

አሰፋ ጫቦም ስሙን በማስታወስ ” አዎን ! በማእከላዊ እስር ቤት ካገኘኋቸው አዋቂ የምላቸው ሰዎች አንዱ ነው ፤ ኢሜይሌን ስጠው ” ብለው መለሱ።

የአቶ አሰፋን መልስ ያገኘው የቦርከናው ድረ ገፅ ባለቤት አቶ አሰፋ የሰጡትን የኢሜይል አድራሻ ለግሪጎሪ ማኬንዚ ይልክለታል ።
ከቀናት በኋላም አቶ አሰፋ ወደ ቦርከና በላኩት መልእክት ” ግሪጎሪ ማኬንዚ በስልክ እንዳገኛቸው እና ወደ አሜሪካ ሲመጣ ዳላስ ቴክሳስ ለመገናኘት እንደተቀጣጠሩ ይነግሩትና ። ” ምስጋና ጨምረው ይፅፉለታል ።

ቀድሞ በተያዘው ቀጠሮ መሰረት አቶ አሰፋ ጫቦ እና “ሊጎበኛቸው” ዳላስ ድረስ የሄደው ግሪጎር ማኬንዚ ማርች 27 ቀን ዳላስ (ዳውን ታውን) ተገናኙ። በወቅቱ ሁለቱ ግለሰቦች ሲገናኙ አቶ አሰፋ ጫቦ ምንም አይነት የህመምም ሆነ የድካም ምልክት ያልነበራቸው እና እንዲያውም ለእድሜያቸው በጣም ጠንካራ የሚባል ሁኔታ ላይ እንደነበሩ ነበሩ ።
ይሄንም የሚያረጋግጥ ምናልባት ከራት ሰዓት በፊት በሚመስል ሁኔታ አብረው የተነሱትንም ፎቶ ግራፍ አለ።
ሶስት ሰዓት በዘለቀው ቆይታቸው ፤ በእራት ሰዓት በአንድ የጣሊያን ሬስቶራንት ራት በልተው ፤ እንደገና ለመገናኘት ቀጠሮ ይዘው ተለያዮ።

በማግስቱ አቶ አሰፋ ጨቦ ታመው ሆስፒታል ሄዱ። አቶ አሰፋ ጫቦ የመጨረሻዋን ኤሜይል ለግሪጎሪ ፃፉ “በምግብ መመረዝ” ። እንደታመሙ እና ስለህመማቸው ስሜት በዝርዝር ከፃፉለት በኋላ ዳግም ሊያገኙት ያልቻሉበትን ምክንያት ሆስፒታል መግባታቸው እንደሆነ ገለፁለት ። ”

ከአውስትሪሊያ ወደ አሜሪካ አቶ አሰፋን ጫቦን ለማግኘት ብዙ ሺህዎች ማይል አቋርጦ ዳላስ የደረሰውና አብሮአቸው ራት የበላው ግሪጎር ማኬንዚ ምንም የሆነው ነገር የለም።
ከዚያ በኋላ አቶ አሰፋ ከሆስፒታል አልተመለሱም። የግሪጎሪ ማኬንዚን እራት ተከትሎ ወደ ሆስፒታል የገቡት አቶ አሰፋ ከሆስፒታሉ ድነው ሳይሆን የወጡት ህይወታቸው አልፎ ነበር ።
እንቆቅልሹ የሚጀምረው እዚህ ላይ ነው ።

ለአለፉት 40 አመታት አቶ አሰፋ ጫቦ ከተለያዩ የፖለቲካ ሃይሎች ጋር ግልፅና ስውር ሽኩቻ ሲያደርግ ቆይቷል ። ዋጋም ከፍሎበታል ። ኢትዮጵያ ውስጥ እና በአካባቢው ያሉ የፖለቲካ ሃይሎች ወያኔ ፣ ኦነግ ፣ሸአቢያ ፣ ኢህአፓ እና መኢሶኖች አሰፋ ጫቦ ላይ ብዙ ክሶችን ፅፈውበታል ። እሱም የሚያውቀውን የድርጅቶችን ገበና ሳያቅማማ ሲፅፍ ነበር ። እነዚህ ፓርቲዎች በግለሰብ ደረጃ እንደ አሰፋ ጫቦ በእጅጉ የሚፈሩት አልነበረም፡፡ የሸአቢያን ፣ የወያኔንና የኦነግን ሴራ የሚያጋልጠው ፅሁፉ ፅፎ ካሰራጨና በመላው አለም መነጋገሪያ ከሆነ እንኳን ሁለት ወር አይሞላውም ነበር ።
አሰፋ ጫቦ በብሩህ አዕምሮውና በላቀ የእውቀት ደረጃው ብዙዎቹን ፖለቲከኞች በእጥፍ ድርቡ ያስከነዳቸው ነበር ፡፡ በዚህ የተነሳም አሰፋ ጫቦን ለአመታት ሲሰሩት የነበረውን ድብቅ ሴራ አውጥቶብናል ገና ወደፊትም ያወጣብናል እያሉ አጥብቀው ይፈሩትና አምርረው ይጠሉት ነበር ።

አሰፋ ጫቦ ጠንቃቃና የማስታወስ ችሎታ የነበረው አዛውንት ስለነበር በኢትዮጵያ ውስጥ እና በኢትዮጵያ ላይ የተሰሩ የድብቅ ሴራዎችን በጥንቃቄ ይዟቸው ኖሮ እያወጣ መጎልጎል ጀመረ ። በመለስ ዜናዊ የውሸት ክስ ሀገር የተባረረው አሰፋ ጫቦ በአሜሪካ አገር በስደት መኖር ጀመረ፡፡ የተለያዩ የፖለቲካ ሃይሎች ግን በብዙ ሺ ኪሎ ሜትሮች ርቆ በሰው ሀገር የሚኖር ቢሆንም የአሰፋ ጫቦ ነገር እንቅልፍ ሊሰጣቸው እንዳልቻለ ብዙ ጠቋሚ ምክንያቶች ነበሩ ።፡ አቶ አሰፋ ጫቦ በተለያዬ ጊዜ በሚፅፋቸውና በሚያጋልጣቸው ድብቅ ሴራዎች “የቀን ቅዠት ሆኖ እያባነነና እያስበረገጋቸው እንደነበር ይታወቃል። ሌሎቹንም የተደበቁ ሴራዎች እየፃፈ እንደነበር ተናግሯል ።

የአቶ አሰፋ ጫቦ የማስታወሻ ደብተር ብዙ ጉዳዮችን አጭቂ የያዘ እንደነበር መገመት አይከብድም ። የኢትዮጵያ ፖለቲካ
እንደ ቆሰለ ጅብ የመበላላት አባዜ የተጠናወተው ነው ። ሸፍጡን እና ሴራውን ለመደበቅ አንዱን ገድሎ ስልጣኑን ማደላደል የተለመደ ነው ። ይሄ ለአመታት የተለመደ መርዘኛ ሂደቱን ቀጥሏል ። ከአንድ ሰሞን ከንፈር መምጠጥ ባለፈ “ ይሄ ሰው እንደት ሞተ? “ለምን ተገደለ?” በማን ተገደለ? ገዳዩ ለፍርድ ይቅረብ ወዘተ” የሚል ባህል የለንም ።

የአሰፋ ጫቦ ጉዳይ ገዳይ ተገዳይ ድራማ ያለበት መስሎ ይሰማኛል ፡፡ በዚህ የገዳይ ተገዳይ ድራማ ውስጥ ብዙ ተሳታፊዎችን መጥቀስ ይቻላል ። አሰፋ ጫቦ በብእሩ ጫፍ ያቆሰላቸው ብዙ ናቸው ። “የትዝታ ፈለግ ” በሚለው መፅሃፉ CIA ኢትዮጵያን ለማፍረስ ሱዳን ካርቱም ላይ መሰርቶት የነበረውን ጣቢያ አጋልጧል ።

“የተሰነይ ጉባኤ ” በሚለው ፅሁፉ ወያኔ ፣ሸአቢያ እና ኦነግ በኢትዮጵያ ላይ የሰሩትን ሴራ ለህዝቡ አሳውቋል ። ለወደፊቱም የሚያጋልጣቸው ብዙ ሚስጥሮች እንዳሉት እና እያዘጋጃቸው እንደነበር ነግሮናል ።

ስታሊን ከአባት ሀገር ያባረረውን ሊዮን ትሮትስኪ በብዙ ሺ ኪሎ ሜትሮች ርቆ በሰው ሀገር ሜክሲኮ የሚኖር ቢሆንም የሊዮን ትሮትስኪ ነገር እንቅልፍ ሊሰጠው ስላልቻለ በመጥረቢያ አስፈልጦ አስገደለው ። ወያኔ በኬኒያ እና በሱዳን የሚኖሩ ተራ ስደተኞች እረፍት ሲነሷት ወደ አገሮቹ ጎራ በማለት እንደምትገድል ይታወቃል ። CIA ም ቢሆን ጠላቴ ትንሽ ነው ብሎ አይንቅም ። ኦነግም አቶ አሰፋ ጫቦ በሚፅፋቸው መራራ ሃቆች ሲቆስል ኖሯል ። ዛሬ አሰፋ ጫቦን አጥተነዋል ነገር ግን ስለአሟሟቱ እንድንጠይቅ የሚያስገድዱ ብዙ ጥርጣሬዎች አሉ ። አሰፋ ጫቦ ተገደለ ወይስ ” ሞተ? ” ። ይሄ እንቆቅልሽ ይፈታ ዘንድ ሁላችንም መጠየቅ እና ትክክለኛውን መልስ ማግኘት አለብን ።

“Donkey Meat Up for Export, Slaughterhouse Opens” – Fortune

ሲለፋ የኖረው በሸክም በዱላ
የአህዮቹ ገላ
ቀረበ ተልኮ፣ በጀማው ሊበላ
ታጨ ለስል ቢላ።
* * *
ተርፏቸው ሳይሰጧት
“ማር አይጥማት” ሲሉ
በስሟ ቀን ግፊያ
“አለች አሉ አህያ”
ብለው ሲደልሏት
ሲያነሱ ሲጥሏት በተራ በተራ
በኑረት ግፍተራ፣ ለተረት ሲሾሟት
ለሽሙጥ ሲድሯት…
 
በክፋት ታጭቀው በምሬት ሲያጉላሉ
ኖረው ኖረው መጡ
ስጋዋን ሊቆርጡ፣
ጌታዋን ሊረግጡ።
* * *
አህያማ ሞልቷል “አልጋ ሲሉት አመድ”
አቀማመጥ ጠፍቶት፣ ሰርክ የሚወላገድ፤
 
ወግ ደርሶት ገራፊ ወፌ ወፌ ላላ
ከፈሱ ተጣልቶ ሰው ገድሎ ሚበላ
ከባዶ አፍ ነጥቆ ቀፈቱን ሚሞላ፤
 
“ሰው መሳይ በሸንጎ”
በየወንበሩ ላይ፣ በየቢሮው ባልጎ
“በወል ስም” ተጠሪ፣ ኗሪ ተሸሽጎ።
 
/ዮሐንስ ሞላ/
 
donkey_export_ethiopia
Fortune: Ethiopia is to export donkey’s meat, following the start of operations at a slaughterhouse in Bishoftu (Debrezeit) town, 48Km east of Addis Abeba.

ትውስታ… (አብደላ ዕዝራ)

13394118_1346035022079626_8563230783627582053_n“ጥሬ ሁል መብቀያ፣ መብሰያ ጊዜ አጣ፤
‘ካፍ ካፍ የሚለቅም’፥ የሰው ዶሮ መጣ።”
ብዬ የዛሬ ሶስት ዓመት የለጠፍኩት ላይ ከዚህ ዓለም በሞት የተለየን ሀያሲ እና ፀሐፊ ጋሽ አብደላ ዕዝራ አስፍሮት ከነነበረው አስተያየት ፌስቡክ አስታወሰኝ። አስተያየቱን ከስር አስፍሬዋለሁ። ትንሹን ነገራችንን በቁምነገር መዝግበው እንደትልቅ እየቆጠሩልን የሚያበረቱንና የሚገስጹን ይብዙልን!
* * *
“ቀለማቱን ብቆጣጥር፥ ቤቱን ባስዉብ ባሰማምር፥
ቅኔ ዘረፋ ብማስን፥ ወርቁን ከሰሙ ብጋግር”… ያልከዉ ትዝ አለኝ።
“የብርሃን ልክፍት” እንደ ርዕስና ሽፋን የሚመጥነዉ የለም። ደበበ ቀድሞህ “የብርሃን ፍቅር”፥ አለማየሁ ገላጋይ ለጥቆ “የብርሃን ፈለጐች” ቢሉም፥ እንደ ርዕስ የልክፍትን [የብርሃን ልክፍት] ምትሃት ++ ያዉ እንደመጥምቁ በምናብ ወንዝ ተነክሮ ይሆናል። ጀርባዉም ይነባባል። ጨለማዉን ገምሶ የሚያንሰራራ የብርሃን ልክፍትአይለቅም።
የገዛሁት ሁለተኛዉን ዕትም ነበር። Oland በድሎሃል… ዉስጡን ለቄስ አስመሰለዉ፤ ግጥሞቹን ማለቴ አይደለም። scan ወይም ቀሺም ፎቶ ኮፒ መሰለ፤ በስንኝና በለጣቂዉ መካከል የተረሳዉ/የረገበዉ ክፍተት ገፀ ዉበቱን አደበዘዘዉ። የተፃፈበት ሆሄ ቢነበብም ቀለሙ [ካንተ ልዋስና] ወየበ። ሊትማንን “ገንዘቤን መልስ” አልለዉ-ጥቂት ግጥሞችህ እንቁ ሆነዉ ማን በፍራንክ የለዉጣቸዋል?
የመሰጠህን አንድ መንቶ ምረጥ በለኝ [] ሶስት ገፅ የወረረዉን የግጥሙን ድባብ የሚያባንንም፥ የሚያስተክዝ ነዉ። ተስፈንጥሮ የወጣ መንቶ አለ።
““እንኳን አደረሰህ” ከተንኳኳ በሬ
ያን ጊዜ እነቃለሁ፥ እሱ ነዉ ሀገሬ”
የተወሰኑ ግጥሞች ደግሜ የማነባቸዉ አሉ፤ ጥቂት የተንዛዙ እንደ መስለምለም ይከጅላቸዋል። ከመሰጠኝ አንዱ አሁን የሚታወሰኝ አጭር ግጥምህ ናት- “ፍርሃት” የምትለዉ። ለምን? እንዴት? ሰለመፅሐፍህ በሌላ ወቅት ሂስ መስል የተሰማኝን እገልጥለሃለሁ።
አሁን “ወርቁን ከሰሙ” የጋገርክበትን ከላይ የለገስከንን ዕምቅ መንቶ ልነካካዉ። አሻሚ ነዉ። ብርሃኑ ገበየሁ እንደሚለዉ “አሻሚነት ከአንድ ፍቺ በላይ ትርጓሜ መያዝ፥ ከግጥሙ ዐዉደንባብ በመነሳት ቁርጥ ያለ ትርጓሜ ለመስጥት አለመቻል” ነዉና እንደ አንባቢዉ ይነባበራል። ሁል ገድፈህ ሁሉ ቢሆን ዜማዉን አይጣረስም፤ ቀለም ሳይቆጠር እንዲሁ ሲደመጥ ያስታዉቃል። አለበለዝያ የ-ሁል- አደናጋሪነት የስንኙን ጠብታዎች ሊያመከን ነዉ።የተደራሲዉንም ትኩረት ይሻማል።
ገና እንደ አነበብኩት አዞ ትዝ አለኝ – አዞ እንባነቱ አይደለም – ሰፊ አፉን ከፍቶ ከጥርሶቹ መካከል አእዋፍ ጥሬ ስጋዉን ሲያስለቅሙ፤ ለአዞ እፎይታ ለነሱ መሰንበት። ይህ አንድምታ ነዉ።
“ካፍ ካፍ የሚለቅም የሰዉ ዶሮ መጣ” ግን ጉዳቱ ያሳስባል። አንድ የጥሬ ትርጉም “ያልተነካ ፥ አዲስ” ከሆነ አድገዉ ለወገን ምርኩዝ የሚሆኑትን ካከሰማቸዉ፥ በዘራፊ ማን ይመካል? ካፍ [ካፌ ባይሆንም] ከቀኝ ቢነበብ ፍካ ፍካ ሰለሚሆን ጮርቃዉን ብቻ አይደለም የፈካዉንም ሊለቃቀመ እንጂ። ይህ በደሉን አባባሰዉ። ከቀኝ ወደ ግራ ባይነበብም ሰሙ ወደ ወርቅ ሲመራም ነዉና ይነበብ።
ከጀርባዉ ከተስተዋለ ግን ብርቅ አንድምታ አለዉ። ዶሮ ጥሬ ለቅማ እኮ ነዉ [የአዳም ረታ ገፀባህሪይ – መዝገቡ- በልቶ የተደነቀበትን] የዕንቁላል ፍርፍር የምናገኘዉ። ጥሬ ተለቅሞ የሚጥም ከመቋደሻ እስከ ፈረሰኛ ለፋሲካ ወደ ብርሃነ ትንሳኤዉ የምንሻገርበት። “የሰዉ ዶሮ” የላመዉን፥ ያልሰለጠነዉን እየለቃቀመ እንደ ዕንቁላል እንደ ጫጩት ሊቀፈቅፋቸዉ ከቻለማ እሰየዉ ነዉ።
የግጥምህ አሻሚነት እየቆየ መዘርዘር፥ መነስነስ ይጀምራል። ይልቅ አሁን የመስፍን አሸብር ምጥን ግጥም ታሰሰኝ፤ በሱ ተመሰጥና ይብቃን።
“ጫጩቶቿን ብላ
ጭራ ልታበላ
“ቋቅ! ቁቅ!” እያለች፥
ይዛቸዉ ራቀች
ሄደች ኰበለለች፤
ያረባኋት ዶሮ
እንደወጣች ቀረች።”
—— // ——
ሀያሲ እና ፀሐፊ አብደላ ዕዝራ ግንቦት 28 ቀን 2008 ዓ/ም ነበር ከዚህ ዓለም በሞት የተለየን። ለኢትዮጵያ ስነጽሁፍ እድገት ትልቅ ሀብት ነበር።

ነፍሱ በሰላም ትረፍ!