ጠዪ በከፋ ቁጥር…

581855_10151320355817546_1236470796_nምንድን ነው እሱ ስራ ፈትቶ ‘ጠላሁት’ ስላሉት ሰው መመላለስ? ከሀይማኖት እና ከአማኞች ጀርባ ላይ ወርዶ አረፍተ ነገር መስራት የማይችሉ ኢአማንያንን መምሰል? “ቴዲ ይሄን መዝፈን ነበረበት። ለኧከሌ ውዳሴ መዝፈን ነበረበት። ኧከሌን ባያወድሰው። ይሄን መዝፈን አልነበረበትም።” ብሎ እኝኝ ማለትና ገና ቴፑ ሳይከፈት ምላስና ጆሮ አሹሎ ለማብጠልጠል መደራጀት? ‘የጠላሁትን ጥላ፣ የወደድኩትን ውደድ’ ብሎ ነገር ነውር አይሆንም? ‘እከክህን ትተህ የእኔን እከክልኝ’ ማለት አያስገምትም?
 
ማን ቃላት ቆጥሮ፣ ታሪክ ሰድሮ በአደራ አስረክቦታል? ማን ዜማ ሰፍሮ ሰጥቶታል? የት ከሰጠነው የሀሳብ ውሃ ልክ ነው ፈቀቅ አድርጎ መሰረት የጣለው? የትኛው የማዕዘን ድንጋይ ተናጋብን? በራሱ ፈቃድ፣ በራሱ ድምጽ፣ በራሱ ጊዜ፣ በራሱ ስም፣ በራሱ ገንዘብ ያሳተመው ሆኖ ሳለ፥ “ልጋታችሁ” ያለ ሳይኖር፣ ለምንድን ነው ለኪነ ጥበብ ወይም ለራሳቸው ጆሮ ተቆርቋሪ በመሆን ሳይሆን፣ በመንገብገብ ስሜት ውስጥ ሆነው ጥላቻን የሚያቁላሉ እና ክፋት የሚፈተፍቱ ሰዎች ከመካከላችን ሊፈጠሩ የቻሉት?
 
“ከዚህ በላይ ማድረግ ይችል ነበር። እንዲህ ቢሆን፣ እንዲያ ቢሆን… እዚህ ጋር ልክ አይደለም፣ በተሳሳተ መልኩ ነው የተገለጸው።” እያሉ በቀናውና ሰሪውንም፣ የሰሚንም ጆሮ በሚያንጽ መንገድ አስተያየት መስጠት፥ ሰሪውን ያሳድጋል፣ ለአድማጮችም የተሻሉና ዘመን ተሻጋሪ ሥራዎች እንዲሰሩ ያበረታልና መልካም ነው። በተለይ ከባለሞያ ሰዎች ይህንን እንጠብቃለን። (የጭፍን አድናቂ ስድብ ዶፍ ከባድ ቢሆንም በትንሽ ትንሹ መጋፈጥ ቢቻል እመኛለሁ። ባለፈው Abraham T. Woldemichael ቪኦኤ ላይ የሰጠውን አስተያየት ተከትሎ ዘለፋና ሙገሳ ያዘነበው ሰው አብዛኛው ቃለ ምልልሱን ያልሰማ እንደነበረ ስታቲስቲክሱን አይተናል።) ገንቢ የትችት ባህል ቢዳብርልን፣ ለሰራውም ሰው እውቅና መስጠት፣ ለሚመጣውም ትምህርት ይሆናል።
 
በሌላ ጎኑ፥ ከእነሱ የተለየ አስተያየት የሚሰጥን ሰው በስድብ እና በዛቻ የሚሞልጩ ሰዎችንም አወግዛለሁ። የምንወደውን ሰው በስድብ ካልሆነ ማስከበር የማንችል የሚመስለን ለምንድን ነው? ነፍሱስ ሰላም አታጣም? ማንስ ሰው ቢሆን፥ በርሱ የመጣ ሰዎች ሲሰደቡ እና፣ “አንተን ላወድስህ ኧከሌን ሰደብኩልህ” ተብሎ ይሸማቀቃል እንጂ ይደሰታል? ለምን የምናደንቀውን ሰው ለማሸማቀቅ እንደክማለን? ምን ይጎልብናል ሰው ያመነበትን ነገር እና የመሰለውን አስተያየት ቢጽፍ/ቢናገር? ደግሞ ምን አንገበገበን፥ የወደድነው ሰው ከዚህ በላይ የላቀ አቅም ላይ ቢደርስ?
 
ይህ በእንዲህ እንዳለ፥ ለሁሉም ነገር ጊዜና ሁኔታ አለው። እሱን መጠበቅ ተሰሚነትን ከፍ ያደርጋል። ሲቻልና ሰሪው ፈቅዶ ሲያሳትፍ፥ ቀደም ብሎ አስተያየት መስጠት ነው። ካልሆነ ደግሞ ለቀጣይ ሥራ መማሪያ እንዲሆን ከስሜት ውዥንብር አርፎ መሬት እስኪያዝ ድረስ መጠበቅ ነው። ሙሽራን የሰርጓ ቀን አዳራሽ ውስጥ ሆና “ቬሎሽ ተንዘላዘለ፣ ሜካፕሽ በዛ” ብትባል ፎቶዋ እንዲበላሽ ከመጣር ያለፈ ሆኖ የሚፈይድ ነገር አለ?
 
በቃ የተመቻቹን መርጣችሁ ስሙ። ካልሆነም ላሽ በሉ። “አድናቂ ነን” ያላችሁም፥ ውዳሴ በመጻፍ ፋንታ፣ ሌላን ሰው በመስደብ የምትወዱትን ሰው ክብር ለማስጠበቅ አትሞክሩ። ትገመታላችሁ። ሁሉንም ሰው ካለምንም ተቆርቋሪ ስራው ያወጣዋል። ማንም ማንንም አያቆምም፣ አያራምድምም! ማንም በሰው ማጥላላት እንቅስቃሴውን አላቆመም። ማንም በወዳጆቹ ተሳዳቢነት ጸንቶ አልበረታም።
 
ጠዪ በከፋ ቁጥር ፍቅር በአምባው ላይ ይገናል! ልክ እንደዚሁ፥ ፍቅር አጨማልቆ እና ጨፋፍኖ፣ ልዩ የሆኑትን ማሳደብ ሲጀምር ተደናቂው ሰው ላይ ጭምር ጥላ ያጠላል። በፍቅር አምባገነንነት ውስጥ ግዞት ያለን ሰው ከስሜቱ እኩል እልህ ይዘውረዋል። ጥላቻም እንዲሁ ነው።
 
ስለዚህ እንተሳሰብ ጓዶች! ተቃቅረን ከምንኖር የተወሰኑ እርምጃዎችን ተቀራርበን የጋራ የሀሳብ ነጻነት ቤታችንን እንገንባ። ቢያንስ ፌስቡክ ያለውን ዘርፈ ብዙ ተጽህኖ እያየን ነውና፥ ፌስቡክ ላይ እንበርታ። ልክ እንደበፊቱ እንማማርበት።
 
ኢትዮጵያ ውስጥ ተቀብሮ ባለው እና ተከብሮ በዋለው ዓለማቀፍ የፕሬስ ነጻነት ቀን፥ ይህንን ስናገር ደስታ ይሰማኛል! 😉
 

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s