የዛሬ 8 ዓመት ገደማ፥ በወርሀ ሰኔ፣ “ገሳ ልልበስ፣ መሬት ልረስ” በማይባልበት የሀዋሳ ከተማ፣ ከሞኝ አበስብስ ዝናብ ጋር ተሯሩጬ፥ አልፎ አልፎ፣ ከመደበኛ የቢሮ ሰዓት በኋላ፣ ከጥቂት ወዳጆች ጋር ተሰብስበን የበጎ ፈቃድ ሥራ የምናግዝበት፥ በቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን ሥር በተቋቋመ የምግባረ ሠናይ ኮሚቴ ቢሮ ውስጥ ገባሁ።
በወጨፎ የቆሸሸ ሱሪዬን ማራገፍ፣ በዝናብ የራሰ ፀጉሬን መጠራረግ እንደጀመርኩ አንዲት ህጻን እያለቀሰች ገባች። ሹራቡ የተተለተለ ዩኒፎርም ለብሳለች። በዝናብ የረጠቡ ደብተሮች በቀኝ እጇ ከደረቷ ጋር አጣብቃ ይዛ፣ ከእንባዋ ጋር ተቀላቅሎ ሊወርድ የሚለውን ንፍጧን ሳብ እያደረገች ታለቅሳለች። ከተማው ውስጥ ካሉ ቤቶች የነጻ ትምህርት ፈቃድ አግኝተን፣ ቁርስ (አምባሻ በሻይ) እዚያው ግቢ ውስጥ ተመግበው፣ ለምሳ ሽሮ ተቋጥሮላቸው ትምህርት ቤት እንዲሄዱ ከምናግዛቸው 45 የተማሪዎች መሀል አንዷ ነበረች።
[…ተማሪዎቹ ጎዳና ላይ ያለፈ ያገደመውን ለምነው (ሲችሉም አምታተው) የሚኖሩ ወላጅ አልባዎች፣ ወይም ከወላጆቻቸው ጋር ተጋግዘው በልመና የሚተዳደሩ ናቸው። በወቅቱ የኮሚቴው አቅም ቁርስና ምሳ ማብላት ብቻ ስለነበር፥ ከትምህርት ቤት ሲመለሱ አማራጭ በማጣት ወደልመናው ያቀናሉ። ከዚህም ባሻገር፥ ወላጆቻቸው ት/ቤት ሲሄዱባቸው የገቢ እጥረት ስለሚያጋጥማቸው፣ ልጆቹ ትምህርት እንዲያቋርጡ እንቅፋት ይሆኑባቸዋል።
የእኛ ዋና ሥራ፥ የማይጠቀሟቸውን አልባሳት እና ወርሃዊ መዋጮ የሚያደርጉ አባላትን ማስተባበር፣ ለዕለት ዕለት ምግብ ማብሰያ የሚወጣውን ወጪ መጠየቅ፣ እንደ ዩኒፎርም እና ደብተር የመሳሰሉ ዓመታዊ ቁሶችን ጊዜያቸው ሲደርስ ማሟላት፣ እና ህጻናቱ ወገንተኝነት እንዲሰማቸው፣ በትምህርትም እንዳይዘናጉ ‘አለሁ’ የማለት ያህል ነበር። ለምግብ ሥራው የተቀጠረ ሰራተኛ ነበር። ከበጎ አድራጊ በተገኘ የቆርቆሮ እና የሰራተኛ ክፍያ ድጋፍም ኩሽና እና ለመመገቢያ መጠለያ እንዲሆን እንደነገሩ ተመቷል። ሥራው መንፈስን ቢያጽናናም፣ በውስጡ መፈጠርን የሚያስመኙ ብዙ ፈተናዎች ነበሩት…]
በትምህርቷም ምስጉን ሆና፥ ለሽልማት የወላጆች ቀን ጥሪ ሁላ መጥቶልን ያውቃል።
“ምን ሆነሽ ነው?” አልኳት፥ ‘ይህኔ አንዱ ጥጋበኛ ሰካራም መቷት ይሆናል’ ብዬ ግምቴን አስቀድሜ።
የሹራቧን እጅጌ ሰብስባ በመዳፏ ይዛ፣ በአይበሉባዋ ዐይኗን እየጠረገች “ደብተሬን ዝናብ አጠበው” ብላኝ እሪታዋን እንዳዲስ አቀለጠችው።
“አይዞሽ በቃ፣ ሌላ ደብተር እሰጥሽና ትገለብጪያለሽ” አልኳት።
“ፈተና ደርሷል። ገልብጬ አልደርስም።” ብላ እዬዬዋን ቀጠለች። ምን ይደረጋል?
በሌላ ጊዜ እንዲሁ አንድ ልጅ እያለቀሰ መጣ። እናት የሞተችበት ያህል ነው የሚያለቅሰው። “ምን ሆነህ ነው?” ሲባል፥
“አባቴ ዩኒፎርሜን ሸጦ ጠጅ ጠጣበት” አለን።
እንዲህ ያሉ ብዙ ዓይነት ፈተናዎች ነበሩ።
ዩኒፎርሙን ደብቃ፥ “ጠፋብኝ ብለህ ተቀበል” ብላ የላከችም እናት ገጥማን ታውቃለች። ተስፋ ማየታቸው ሲታይ ግን ለራስም ትልቅ ተስፋ ይሰጥ ነበር።

ዕቅዱን ለማሳካት የቀረው እንዲሟላ፣ የምትችሉ ከ$5 ጀምሮ በማዋጣት ልጆቹን “አይዟችሁ፣ በርቱ” እንበላቸው። ያልቻላችሁ፣ በማትችሉበት ሁኔታ ያላችሁ ደግሞ፥ መልእክቱን SHARE ብታደርጉት፣ ሌላ አቅምና ሁኔታ የሚፈቅድለት ሰው አይቶት እንዲያግዝ ምክንያት ትሆኑታላችሁና፥ አደራ!
Thanks for caring Yohannes