“ሄዋን እንደዋዛ ፍሬዋን በልተሽ
በእኔና በምድር፣ ሞት እንዳመጣሽ”
የሚላት የመጀመሪያዋን ቀዳማዊት ሄዋን ነው
“ለባከነው ልቤ ራርቶ ልብሽ
መጽናናያ ሆኖኛል፣ ክሶኛል ፍቅርሽ”
ሲል ደግሞ ይኽቺ ዳግማዊት ሄዋን እመቤታችን ማርያም ሆና፣ በልጇ በክርስቶስ እንደካሰችን ነው የሚያሳየው።
~ ቴዲ አፍሮ ❤
“ልቤም ተደላደለ ጎኔም ደላው መሰለኝ
አንቺን ስለመውደዴ፣ አገር ሰምቶ ጉድ ቢለኝ
ከወደድኩሽ ወዲያ ምንድን ነው?
ቢጠፋም ስሜ ነው።
በዚህች ዓለም ስኖር ሰው ነበር ረሀቤ
ምኞቴ ተሳካ ባንቺ አረፈ ልቤ…”
እያለ ነው እንግዲህ ዘፈኑ ጀምሮ……….
“ሄዋን እንደዋዛ ፍሬዋን በልተሽ
በእኔና በምድር፣ ሞት እንዳመጣሽ
ለባከነው ልቤ ራርቶ ልብሽ
መጽናናያ ሆኖኛል፣ ክሶኛል ፍቅርሽ”
የሚለው ጋ የሚደርሰው። እንዲህ ቅልጥ ባለ እና ቅልጥ በሚያደርግ የፍቅር ዘፈን ላይ፥ ይኼ ማርያምን ነው የሚገልጸው ማለት ለምን እንደሚጠቅም አላውቅም። አንዳንዱ ነገር ባይብራራ ሳይሻል አይቀርም።
* * *
ጎሳዬ ተስፋዬ ❤ “እናትዬ የሚለውን ለማን ነው የዘፈንከው?” ሲባል
“ለእናቴ” አለ ብለው ሲያነፍሩን ነበር። (ቃለ መጠይቁን አልሰማሁትም) እንግዲህ “ሁለት እናት አለኝ…” ሁሉ የሚል ሀረግ አለው። 🙂
እንግዲህ “አቤት ብቻ ነው ሲጣሩ እቴጌ!” ተብሏልና፥ የምንወዳቸው ከያንያን ሲሉን፣ አሉን ነው። 😉
* * *
የስዕል አውደ ርዕይ ልንመለከት ሄደን ሙንጭርጭር ያለ ስዕል እናይና፥ ቀለሙን ብቻ ወደነው እንኳን እንዳናልፍ ለነገር ሰዓሊው እዚያው ቆሞ እናገኘዋለን። …ዐይን ዐይኑን እያየን ትርጉሙን ከፊቱ ላይ ልንፈልግ ስናፈጥ፥ ማስረዳት ይቀጥላል።
“…እዚህ ላይ ቀዩ መስመር ህልማችንን ነው የሚወክለው። ወደዚያ የሄደው ሰማያዊ ደግሞ… ጥቁሩ መደራረቡ የሰዉን የኑሮ ውጣ ውረድ… እዚህ ጋ ደግሞ አይታይም እንጂ፣ ጽጌረዳ አበባው መድረቁ ህልም የመሰለችኝ ፍቅሬ ትታኝ መሄዷ…”
“አሃ” እያልን፣ ራሳችንን በአዎንታ እየነቀነቅን፣ በልባችን “ወንድሜ እኔ የማየው ነገር የለም” እንላለን።
የባሰም አለ፥ “ወንድም ይኽ ስዕል ምን ለማሳየት ነው?” ሲባል
“አይ ለራሴ ነው የሳልኩት”
ምንሼ አደባባይ ማውጣቱ?
.
.
እመው “ተከድኖ ይብሰል” ይሉትን ፈሊጣዊ አነጋገር ካለነገር አላሉትምና! አንዳንዱ ነገር ባይብራራ እና ከተሰራ በኋላ በመጣ እውቀት ለመቃኘት ባይሞከር እንዴት ሸጋ ነበር?!
ሰላም!