ስለመውደቅ…

ሰፈሬ ልጅ ገና ሊወድቅ ሲያስብ፥
 
“አንተ ልጅ ዋ… ቀስ ብለህ ተጫወት…”
“ዋ ብያለሁ…”
“እሺ ኋላ እሪ ብትል ምናለች እንዳትል…”
“ትደፋና ኋላ…ዋ”
(“ውይ ተዪው አንቺ ደግሞ። ይጫወቱ እስኪ። ሸክላ ነው ልጅ ሁሉ ሲጫወት ተለይቶ ምን እንዳይሆን ነው? እሺ ከዚያስ…” የሚል ወሬ የተጠማ ድምጽ ፊቸሪን ሊገባም ይችላል።) ብዙ የማስጠንቀቂያ መዓት ይጎርፍበታል።
 
ልጁ ልጅ ከሆነና፥ አስጠንቃቂዋ እናቲቱ ከሆነች በዐይኗ እየተከታተለቸው ሲወላገድ ትወላገዳለች፣ ሲወድቅ ትወድቃለች። አይሞቀውም እንጂ፣ አያውቀውም እንጂ፣ አንቀልባ አልጣለችበትም እንጂ፣ እየሄደ መስሎታል እንጂ፥ በዐይኗ አቅፋው ነው የሚራመደው።
 
ከዚያ ተፍ ተፍ ብሎ ባፍጢሙ ይደፋላቸውና፥ አቀባብሎ እንደሚጠብቅ ሁሉ ሰፈሩ ባንድ እግሩ ይቆማል።
 
“ኡኡ…” ድብልቅልቁ ይወጣል።
የወደቀበትን አፈር መቃም ግዴታው ነው። አጉል አፈር አይንካኝ የሚል አፈሩን የተጠየፈ ካልገጠመው በቀር አፈሩን አቅምሶ ነው ብድግ ማለቱ የሚቀጥለው።
ከሩቅ ያዩና ያልደረሱበት “አፈሩን አቀመስሽው?” ይላሉ።
“እናትህ ትደፋ” (እንደእኔ ዓይነት ልጅ ሲሆን “የእርሶ እናት ትደፋ” ብሎ የሚሮጥበት አጋጣሚም ይኖራል። 🙂 )
“እኔን እናትህ/እህትህ/ወንድምህ…”
“ድፍት ያርገኝ…”
እህቱ ካለች ደግሞ ታየው ታየውና አንጀቷ ሰፍሰፍ እያለባት “ውይይ እኔን…” እያለች ሽጉጥ ታደርገዋለች። ምክርና ቁጣ የቀላቀለ ፍቅር ታዘንብለታለች። ጉልቤ ወንድም አያጣም መቼስ። “ማነው የፈነከተው?” ይላል። “ልቀቁኝ፣ አትናገሩኝ” ነው። “ኧረ ወድቆ ነው” ተብሎ በስንት ዝክርና ዝርዝር ነው እጁ የሚመለሰው። ሃሃሃ…
 
ካበጠ እዳው ገብስ ነው። ወደውስጥ እንዳይደማ እየተጸለየ በበረዶ ሲታሽ ማደር ነው።
 
እንደምንም ብሎ ደምቶለት ከሆነ ደግሞ፥
 
“ደሜ ይፍሰስ…”
“እኔ ልተርተር…”
(ኡኡ አልተረፈም። ታዪዋለሽ። እኔን እናትህ።)
“ግን እንኳን ደማ…”
“ኧረ ልክ ነሽ እንኳን ደማ። ወደ ውስጥ ፈሶ ቢሆን ኖሮስ?”
“ኧረ የሰይጣን ጆሮ ይደፈን።”
(በየመሃሉ “ባለፈው ታች ሰፈር፣ ላይ ሰፈር….” እየተባለ መሰል የመውደቅ አደጋ ታሪኮች ይወራሉ። ለመውደቅ አደጋዎች የአንበሳውን ድርሻ የሚወስደው መንግስት የሚቆፍራቸው ጉድጓዶች ውስጥ የወደቁ ሰዎችም አብረው መነሳታቸውም አይቀርምና መንግስትም ይታማል።)
“እሰይ…መድማቱ ጥሩ ነው።”
“በማን ወጥቶ ነው ቂመኛ? ደሙን ታዪዋለሽ አጠቋቆሩ”
(በከፊል ይሳቃል። በከፊል ደግሞ ነገር አሳማሪዋ ትወረፋለች።)
 
ሀኪሙም ብዙ ነው።
 
“ቀስ አትልም ነበር”
“ስለው ስለው” የሚሉ ድምጾች ምርኩዝ ሆነው ማንሳት ጀምረው፣ ጥግ አስይዘው ደም ያጣርጉታል።
“እስኪ ሚሪንዳ ግዙ ደም ይተካል።” ይላል አንዱ የደላው።
“ጭራሽ ሚሪንዳ? እየወደቅክ ና ለማለት ነው? በሉ ሰፈር አታበላሹ።” ይላል ሌላው።
“አታንጋዪው…”
“ኧረ ቀና አድርጊው…”
(አያዎ የኑሮው ዘይቤ ነው። ልጅ ተጠይቆ ሲናገር “ጭራሽ መልስ ልትመልስልኝ ነው? ከአዋቂ ጋ እኩል ይቅር አላልኩም? ነብር አየኝ በል” … በጄ ብሎ አዋቂ ሲያናግረው ዝም ሲል “ጎሽ! ተጎርምሶልኛላ። ምን ይዘጋሃል አንተ? ንቀት መሆኑ ነው?” ይባላል። 🙂 )
 
የሸረሪት ድር ይታሰሳል…
የማሰሻ ጨርቅ ይንጋጋል (ከሰል ላይ እየተሞቀ ሊተኮስ)
ቡና ይደምደምበት ይባላል።
አልኮል ከጠፋ ውድ ሽቶ ይነሰነስበታል… (ሰርገኞች “ኧረ ሚዜው ድሀ ነው ሽቶው ውሃ ነው።“ ከሚሉ ሙሽራውን ፈንክተው ባዩት። ሃሃሃ)
(“ቡና ለእሳት ነው” “ለፍንክት ነው” የሚሉ ኤክስፐርቶች ጭቅጭቅ ሳይበርድ እናቲቱ አክሽን ትወስዳለች።)
ቡናው ተደምድሞ ትንሽ ሳይቆይ፥ “ሊጥ ጥሩ ነው” ይባላል። “ዘይት ጥሩ ነው” ይባላል። “ኧረ ተዉ እሳት አይደለም ይሄ። የሸረሪት ድር በቂ ነው።” ይባላል። መውደቅ ወደ ተንቀሳቃሽ ኩሽናነት ከመቀየር ጋር የሚቀራረብ ብቸኛው ነገር ሳይሆን አይቀርም።
 
መቼም “የወለደ አልጸደቀ” ትላለች እናቴ። ወላድ ሁሉንም ይሰማል። እናቲቱ ቡናውን ሙሽልቅ አድርጋ ጠርጋ ሊጥ ትመርግበታለች። ሌላው ሀኪም ይመጣና “ኮልጌት ጥሩ ነው። ከነጠባሳው ነው ብን የሚያደርገው።” ይላል። መከረኛዪቱ ኮልጌት ፈልጋ ትቀባዋለች። እንዲህ እንዲህ እየተባለ፥ እንደምንም ተብሎ የሸረሪት ድር ፈልጉ የተባሉት ብቅ ይላሉ። ማን እንደ ሸረሪት ድር? እሱ ይለብስና ጠባሳ ይቀመማል።
 
“እስኪ ተጎዳ? ትላለች” ተባለንዴይቱ
“ኧረ ተመስገን የባሰስ ቢሆን” ይላል ሌላው
በግርግር አላየሁም፣ ለወሬ ዴንታ የለኝም ባይ፣ የጤፍ ቆሎ ሚዋጣላቷ ደግሞ ታየውና “ውይ ውይ… ዐይኑን እግዜር ነው ያወጣው። እኔማ ምኑም አያምረኝ ነበር። ሲሮጥ አይተሽዋል። ኧረ እንደውም ለልቡ ነበር የምፈራው። እንኳን በዚህ ተመለሰ።”
 
እናቱ በወቅቱ የሌለች እንደው “በሉ እናቱ ሳታየው እጥብጥብ አድርጉት” አለች ደግሞ ትዕዛዝ ሰጪ….
አባቱ በወቅቱ ካልነበረ፥ ተደብቆ ላይደበቅ “በል አባትህ እንዲህ ሆነ እንዳያይህ። ግባና ተኛ።” ተብሎ በጊዜ እንቅልፍ ይታዘዝለታል።
(ዕድሉ ከሆነ ደግሞ ሳሎን እስኪነጠፍ ድረስ የአባቱ መኝታ ላይ ተኝቶ ስለሚጠብቅ፣ አባቱ ተሸክሞ ሊያመጣው ሲል የታሸገውን ያየውና በድንጋጤ ባናቱ ሊለቀውም ይችላል። ሃሃሃ…)
 
ከዚያ ተስያትና በማግስቱ የሰፈሩ ወሬ ማድመቂያ መሆን ነው።
 
ሰፈሩ ሁሉ ይሰማል።
 
መምከሪያ ይደረጋል።
 
“ይኸው እሱም አልሰማ ብሎ ነው ተው እየተባለ። ቀስ…”
“የአበራሽን ጠባሳ ያየ” የሰፈሩ ያልተጻፈ መፈክር ሆኖ ይቆያል።
 
ሰፈሩ ያድባል። የሚሮጥ ይቀንሳል። “ዕብድ ቢጨምት እስከ 7 ሰዓት” እንዲሉ ለሁለት ቀን ኮሽታም የለ። ከተቻለ ከቦ ማስታመም ነው። የልጅነት ወረት እንደጠዋት እንቅልፍ ጣፋጭ ናት። (አትሌቶቻችን በየቀኑ ቢያሸንፉ ኖሮ ሰፈራችን ብዙ ሯጭ ታፈራ ነበር እላለሁ። እኛው ቀጥቅጠን በሲጋራ ወረቀት ለለበጥነው የቆርኪ ሜዳሊያ ቀላል ደም ተፋን? ልባችንን ባፋችን ለመልቀቅ ምን ይቀረን ነበር። ለበረኪና ዋንጫ መጋደሉም እንደዚያው ነው። አሁን ሳስበው ያስቀኛል።)
 
እንደምንም ብሎ ቁስሉ ጠፈፍ ሲል ደግሞ መረቀዘ አልመረቀዘ ጆካ ይያዛል። እናትየው ሳት ብሏት “ኧረ ምግብ ቀነሰ” ወይ “ቃዠ” ካለች ሁለት ሰባት ሁሉ የሚያዝ አይጠፋም።
ትልቅ ጠባሳ ፊቱ ላይ ያለበት ሰው ሳይቀር “የድሮ ጠባሳ ሁሉ ያጠፋል ተብሏል። ድንች እኩሉን ሰንጥቀሽ ውሃውን ክደኚው” ብሎ ምክር ይሰጣል። በሰበቡ አንድ ኪሎ ድንች ይገዛና ቅቅሉን እየላጡ በሚጥሚጣ በሽበሽ ነው።
 
በዚህ ሁሉ ግርግር መሀል ግን የጩጬው ልብ የመጬ ይፈነጥዛል። ነገ ትምህርት የለም! ሰሞኑንም ትምህርት ለመቅረት ሰበቡ ብዙ ነው። 🙂
 
እንዲህ ነው ወጉ!
 
መርካቶዬ፥ የሰው ሰፈር። የሰው አገር። ሕይወት የሞላበት።
 
ሰው መሀል እንቅፋት ቢጤ ከዚህ እዚያ አሽቀንጥሮኝ ከመጤፍም ሳልቆጠር ስቀር እና፣ አይዞህ እንደ ረቂቅ የሙዚቃ ቀመር ትዝ ቢለኝና ምትሀታዊነቱ ቢያሳስበኝ ነው። 🙂

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s