ገድለ ከርዳዳ ጸጉር

a00fde8d73d49f12969eafa7d59851efበአገሬ፥ ጸጉር እንዲህ ዝም ብሎ በአምስት ጣት በጠር በጠር ተደርጎ የሚተው ነገር አይደለም። የጥቁር ሰው ከርዳዳ ፀጉር ደንብ ይኽ አይደለም። ወግ አለው። ስርዓት እና አያያዝ አለው። ከጉፍርናው እስከ ጉንጉንናው ድረስ (ከጉርምስናው እስከ ሽምግልናው እንዲሉ) ተዘፍኖ፣ ተገጥሞለት ነው። በስሌት እና በምክንያት ነው እንጂ እንዲሁ አማራጭ ስላጡ የሚተዉት አይደለም።
 
“ጫካ ነው ጸጉሯ ሽጉጥ ያስደብቃል” ተብሎ ይፎከርለታል።
 
“ራሷን ሹሩባ ተሰርታ ስትመጣ” ይዘፈንለታል። እንደእኔ እና እንደ ሽመልስ የደረሰበት ያውቀዋል ሹሩባ አይቶ ሳይታመሙ የመሞትን ነገር። (ሽመልስዬ አራርሶዬ ❤ ሲናፍቀኝ እኮ!)
 
“ሀር ነው” ይባልለታል። ሀር አይቶ የማያውቅ ሁሉ ያማረ የተዘናፈለ ጸጉር ሲያይ ሀር ነው ይላል።
 
በሻሽ ቢጠፈነግም “ሀር አይደለም ወይ፣ ሻሹ በላይሽ” ተዘፍኖለት ነው።
 
“ፀጉሯ ወርዶ ወርዶ ይጠቀለላል እንደዘንዶ” ተብሎ ከበሮ ይደበደብለታል፣ እጅ ይጣፋለታል።
 
ዝናው ብዙ ነው።
 
እንጂ እንዲሁ በብላሽ ሳብ ሳብ ተደርጎ የሚተው አይደለም። ያ ሉሃጫ ፀጉር ወግ ነው። አማራጭ የሌለው ሰው በአንድ ዓይነት ስታይል በመኖር ብቻ ሌላውን የማጣጣል አቅም ያገኛል።
 
ሲደላ ቅቤ በሀደስ ተለውሶ፣ ወይ ደግሞ እንዲሁ ራቁቱን ይቀባል። (ቅዳሜ ቅዳሜ ሴቶቹ ተሰጥተው ቅቤ ሲቀቡ ደስ ሲል። “እንዲያቀልጠው ነው፣ እንዲሰርግ” ብለው የጋለ ጸሐይ ላይ ስቲም ይገባሉ። ወይባ ጢስ በነጻ፥ right from the source መሆኑ ነው። ቡናው ውጪ ይፈላል። ግልፈል በቆሎ ይፈነዳል። ፍርፍሩም ምኑም አይቀርም። ዘለን ዘለን ሲደክመን አብሮ ማሻመድ ነው። ተቀብጠውት ካደሩም ሽታው ደስ አይልም። ግን ከጠቀማቸው ምን ቤት ነን?
 
እግር ጥሎ “ለጸጉሬ ውሃ አፍስልኝ” ካሉ ነው ጉድ የሚፈላው። ዶሮ እንኳን እንደ ቅቤ ጸጉር ያን ያህል ተደጋግሞ አይታጠብም። ጆግ የተሸከሙበት ክንድ ይገነጠላል። ተጣጥበው፣ ደርቆ ሲታዩ ግን እምጷዬ ነው። ፊታቸው ቅዳሜን ይመስላል። ልምልም ይላል። ጥያሜያቸው ያንጸባርቃል። እዩኝ እዩኝ ይላል።
 
ቅቤውም እንዲሁ ተሞሽልቆ አይደለም የሚቀባው። ለጸጉር የሚሆነው ለጋው ተፈልጎ ነው። “ኧከሊት ቤት ሂዱ” ይባላል። አጓት አጓት የሚለውን፣ በቆረሲማ የታጠነውን ቅቤ ነው የሚቀቡት። ከተማ በቫኒላ ይለውሱት ነበር። ሲገኝ በሀደስ ነው። ብቻ ሲቀቡት በመነጋው ደስ ይላል። በታክሲ ሲጓዙ እንኳን ያልተለቃለቁት ቅቤ ከላቡ እና የጫማ ሽታው ጋር ተቀይጦ የድርሻውን ያዋጣል።
 
እግሩ ጫማው ውስጥ የሞተበት፣ እንደ ሰው አካል የረሳው ጎረምሳ፣ ልጇን ስታበላ ረፍዶባት ለጉሊት የምትሯሯጠውን ሴት ጸጉርሽ ሸተተ ሊልም ይችላል። ቂጡን የጣለ ፎከቲያም፣ ታጥቦ የሚያውቅ የማይመስል የታክሲ ረዳት ሳይቀር ልጅ አዝላ ልትገባ ያለችን ምስኪን “እናቱ ቅቤ ከተቀባሽ ውረጂ” ሲል ተጣልቼ አውቃለሁ። (በርግጥ አልተቀባችም ነበር። ግን ቢሆንስ ከዚያ ሁሉ ጥንባት ብሶ ነው?)
 
የሴቶች የጸጉር ወሬም እንደ ትልቅ አጀንዳ ይናፍቃል። በተለይ አርብ አርብ ይደራል። ድሮ፣ ለእነ ኦሊቬራ “ፓፓ” ሳይባልላቸው፣ በሞተር ስትሄድ ሳይከተሏት በፊት፣ ዜኒት ቅባት ሲገዙ ማበጠሪያ ይመረቅ በነበረበት ዘበን፥ የቢሮ ሴቶች ፀጉራቸውን በቪጎዲን ተጠቅልለው ጸሐይ ላይ ቅዳሜ ወይ/እና እሁድ ቁጭ ብለው ኑሮውንም፣ ገጠመኙንም ሀሜቱንም ሲከኩ ጸጉራቸው ይተኮስላቸውና ለሰኞ ቢሮ ይደርስ ነበር። የሜሪ አርምዴ የሹኪያ ተኩስስ የስንቱን ኮረዳ ዐይነ ጥላ ገፎልናል። እናቶችማ ተማረው ሹካ መግዛት አቆሙ።
 
ከርዳዳ ጸጉር፥ ቁጥርጥር (ይቅጠን ይወፍር ተብሎ) ልስራህ ይባላል። ሹሩባም የራሱ ነው። ሹሪባው ደግሞ ዐይነቱ ብዛቱ፥ ከአንድ እስከ አስር እዮሽ እንደ ችኮላ እና እንደ ፊት ቅርጽ ሁኔታ፣ የዶሮ ቂጥ፣ ዶሮ ሥራ፣ ተማሪ ሥራ፣ የማታ ተማሪ ሥራ፣ አምፖሎ፣ ቅቤ ቀቡኝ፣ ዚግዛግ፣ መረብ ሥራ ተብሎ በያይነቱ ነው። ሹሩቤ የሚባል መጠጫ ሁሉ ነበር። የልብ አድርስ ሳይሆን አይቀርም።
 
ፍሪዝ፥ ጂጂ ስታይል (ምቹን ካልፈሩ በተልባም ቢሆን። ወይ ደግሞ ቫዝሊን ተቀብቶ በሳሙና ሲታጠቡት ፍርፍር ይላል።)፣ ፍሽን፣ አልባሶ፣ ጅራፍ ሥራ፣ ጎፈሬ፣ ኧረ ምኑ ቅጡ። እሱም እየተሞከረ፣ በመስታወት እየታየ… ቆይ ሌላ ተብሎ ስታይል እየተቀየረ ነው። የየባህሉ፣ የየገጠሩም ለጉድ ነው። እንጂ ከርዳዳ ፀጉር እንዲሁ ዝም ብሎ ተዘናፍሎ የሚተው ብቻ አይደለም። መልክና ስርዓት፣ ወግና ጠባይ አለው። ሲፈልግ ደግሞ በካውያ ይለሰልሳል። ለስላሳን ጸጉር ግን እንዴት ያከረድዱታል?
 
ሲበጠር ራሱ የሆነ ኦርጋዝሚክ ስሜት ሳይኖረው አይቀርም። “እስስ…” ይላሉ። ሃሃሃ… ማበጠሪያው ይኾናል። እሱን እያሳመሩ ደግሞ ፍተላ ነው።
 
“ኧረ ፀጉሬ ተሰባበረ”
“የለም እኮ አልቋል። ታያለሽ የሚረግፈውን?”
“መንታ ሆነብኝና ቆረጥኩት” (ስለመንታ ጸጉር ተማርኩ)
“እማዬን ፈርቻት ነው እንጂ በደንብ ብቆረጠው ደስ ይለኛል።”
“በዊግ ብትሰሪው ይበዛልሻል።”
“እስኪ ሙች በይ? ወይኔ፥ እኔ እኮ ሂዩማን ሄር ነው ነበር የምለው።”
“ጥቁረቱ ራሱ ሀር አይደል እንዴ የእሷ ጸጉር?”
“ምንድን ነው የምትቀቢው በናትሽ?”
“ቅቤ… ቅባት አልስማማ ሲለኝ ቅቤ ነው የመለሰልኝ።”
“እኔም ብቀባ ደስ ይለኝ ነበር። ባለቤቴ አይወድም እንጂ አምሮኛል እንደውም።“
 
በስንት ልፋት ተሰርታ ያዘኝ ብላ የምትፈታዋም ትሰማለች። ደግሞ ይዟት ጊዜ አጥታ፣ ወይም ማጌጡ አምሯት ችላ ትታው ደምስሯ ተወጣጥሮ ፊቷ የዞረባትም ትታያለች።
 
“ኮኮስ ተስማምቶኛል”
“ወይኔ ጸጉርሽ ፏፏ” ይባላል። የደላው ልጅ በሚቀነጭርበት አገር ስለጸጉር መፋፋት ለማውራት ጊዜ አያጣም። ድንቡሽቡሽ ጸጉር ታየኝ።
 
እንቁላል፣ አቮካዶና ሙዝ ሲቀቡ አይቶ ምራቅ እየዋጠ “ምነው ጸጉሯን ባረገኝ” ያለ ጥበብ የጠራችው ፈላም አይጠፋም። ሃሃሃ…
 
ከርዳዳ ጸጉር ቢቆረጥም ያምርበታል።
 
“ሁልጊዜ ጎፈሬ ተከርክሞ ኑሮ፥
መቀሱን ላኩልኝ ቁርጥ ነው ዘንድሮ።” ብሎም የለ ዘፋኙ?
 
ይኼ ከከርዳዳ ጸጉር ወግ ማዕረግ በጥቂቱ ነው። ቁንድድ ቢሉት፣ ሽቦ ቢሉት፥ ለስታይል አንደኛ ነው። ሽቦ ነው እንጂ በፒንሳ ተወጥሮ የሚጠቀለለው፣ የትኛው ቃጫ ነው? 🙂
 
ማነው ለሉሃጫ ጸጉር ከ“እጆቼን ጸጉርሽ ላይ ሳንሸረሽር” ከማለት ያለፈ ነገር የተቀኘ? 😉
 
ሰላም!

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s