እንዴት እንዴት ነው የተጨካከንነው ግን?!

የሰማኒያ ዓመት እናት በሁለት ልጆቻቸው የበደልም በደል ተፈጽሞባቸው ከሞቀ ቤታቸው ቤት አልባ ሆነው የትም ተጥለው፥ በአዋቂ ሰው እርጋታ እና ብስለት ውስጥ ሆነው “የእርቅ ማዕድ” ላይ የሰጡትን ቃለ መጠይቅ አድምጬ የምገባበት ጠፋኝ። በርግጥ ከጸሐይ በታች አዲስ ነገር የለምና እንዲህ ያለ ጉድ ተከስቶ ያውቃል። አባቱ ሞቶ እስኪወርስ ድረስ መጠበቅ አቅቶት በመጥረቢያ የገደለ ትቢያ ታሪክም ተሰምቶ ያውቃል።

ትንቢትም ተነግሯል። “…ዳሩ ግን፦ መካኖችና ያልወለዱ ማኅፀኖች ያላጠቡ ጡቶችም ብፁዓን ናቸው የሚሉበት ጊዜ እነሆ ይመጣልና ለራሳችሁና ለልጆቻችሁ አልቅሱ።” ~ የሉቃስ ወንጌል 23፥ 29

ሰው ከየትም የማያውቃቸውን አረጋውያን ለመርዳት በሚጥርበት አገር/ዓለም ውስጥ፥ እንዲህ ደግሞ የገዛ ወላጅ እናቱን ለመበደል የማይራራ ልብ ያለው ሰውም አለ። ስንት ዓመት ሊኖር? ነገ እንዴት አይፈራም? እንዴት ሰው ምን ይለኛል አይባልም? ገንዘብ እንዲህ ተወዶ ምን ቋሚ ነገር ሊገዛበት ነው? እናት ተካደች፣ ብሩ ተገኘ፣ ያሰቡት ተሳካ፣…እሺ ከዚያስ??

ይሁዳ ኢየሱስ ክርቶስን በሰላሳ ብር እንደሸጠው እንዲሁ፣ ወላጅ እናቱን ስለገንዘብ የመካድ እና የመለወጥ አቅም ያለው ሰው ከመኖሩ እኩል፣ የሰማው እንኳን የሚርድበትን እና መፈጠሩን እስኪጠላና ነገውን እስኪፈራ ድረስ የሚያማርርበትን ጉዳይ ፈጽመው፣ እንደ ሰው ቆሞ መሄድ እንዴት እንደማይከብዳቸው፣ እንቅልፍ እንዴት እንደሚወስዳቸው ሲታሰብ ይደንቃል።

ነገሩ በአጭሩ እንዲህ ነው፤ ባስታወስኩት መልኩ በራሴው መንገድ ገልጬ እንጂ ንግግሮቹ ቃል በቃል አይደሉም። (ሙሉውን ለመስማት ግን እነሆ ማስፈንጠሪያው: https://www.youtube.com/watch?v=8TJxKbUFYw0)

ከእርሳቸው ጋር ተጠግታ የምትኖር ልጃቸው “እማዬ፥ ከእንግዲህ ደክመሻልና በስተርጅና ከምትንከራተቺ፣ ውክልና ስጪኝ እና እድሩንም፣ ውሀውንም፣ መብራቱንም እኔ እከፍልልሻለሁ።” ትላቸዋለች። እሺ ብለው ይፈርማሉ።

ሆኖም እሷ ያስፈረመቻቸው ወረቀት “የተበደርኳትን 300 ሺህ ብር በሁለት ወር ውስጥ እከፍላለሁ። ካልሆነ፥ ከዚህን ያህል ወለድ እና፣ ከዚህን ያህል መቀጫ ጋ ንብረቴን ሸጬ እከፍላለሁ።” ነበር የሚለው።

ከሁለት ወር በኋላ መጥሪያ መጥቶላቸው ፍርድ ቤት ይቆማሉ።

“አላውቃትም። አረብ አገር ሰርቼ ያመጣሁትን ብር ነው የወሰደችብኝ።” ትላለች።

ጠበቃውም ጉቦ የበላ መሆኑ ነው መሰለኝ ያዋክበኛል አሉ። ሴትዮዋ በድንጋጤ ልሞት አሉ። ሁኔታቸውን ዳኛው ተመልክቶ፣ እንዲረጋጉም ጭምር ሳይሆን አይቀርም ለሌላ ቀን ቀጠረን አሉ። ‘ደግሞ መልካችን አንድ ነው፣ አላውቃትም ማለቷ ዳኛውንም አስደንግጦታል’ ይላሉ።

“እናቴ አይደለችም ብለሽ ማዪ” ተብሎ ወንጌል ቀርቦላት፣ ክዳኝ ማለች። እንግዲህስ ምን ቀረኝ አልኩ። በቁሜ ሽንቴ አመለጠኝ፣ አንዴ ልናገር ክቡር ፍርድ ቤት ብዬ እጄን አነሳሁ፥ እንግዲህ የዘጠኝ ወር ቤቷን፣ የሶስት ዓመት ጥገቷን ከካደች፣ ብሩ ይከፈላት” አልኩ። ዳኛው “ከየት አምጥተው ይከፍላሉ?” ሲል፥ “ቤቱ ተሽጦ ይከፈል። እኔ ለእነሱው ነው እንጂ መሽቶብኛል። ከእንግዲህ ወይ ስንዝር ወይ ክንድ ነው ቢያስፈልገኝ። ፀሐይ ጠልቃብኛለች መሽቶብኛል።” ይላሉ። እንዲህ እንደማወራው አይደለም።

ቤቱ ተሽጦ ወደ ስድስት መቶ ሺህ ብር ይሰጣታል። አራጅ እንዳይወጣበት በማለት፣ የገዛችው ሴትዮዋ ናት ቀድማ ብሩን የምትሰጥላቸው። እግዜር መጽናኛውንም እሷን አመጣላቸው። እንደእሷም ዓይነት ደግነት እዚያው ሲሰማ ደግሞ በመካከሉ ያጽናናል።

እኔ ቤት ይቆዩ ብትል፣ “በህጉ ሻጭ እዚያው መሆን አይችሉም ተብሎ በሁለት ሺህ ብር ተከራየችልኝና ሌላ ቦታ አስቀመጠችኝ። እሷም ትሰለቻለች። እስከመቼ በምን እዳዋ ትከፍላለች?” አሉና ያው ጊዜው ሲደርስ ከዚያም ወጡ።

ብሩን የወሰደችው ሴት ድጋሚ መጥታ የጠበቃ አበል ብላ ሌላ ሀምሳ ሺህ ብር ወሰደች። እንደገና መጥታ ”እዚህ ቤት ውስጥ የሰራኋቸው ክፍሎች አሉ” ነገር ብላ መጣች አሉ። ገንዘብ አፍቅሮ ማፈር የለ። “ገንዘብን መውደድ የክፋት ሁሉ ሥር ነውና…” ~ 1ኛ ወደ ጢሞቴዎስ 6፥10

በመጣች ጊዜ “ሞት እምቢ ብላ ነው የምትጠራኝ አሉ።” የዚህ ግርግር ሲያባራ፣ ለእርሷ ያለችው ብር ሁሉ ተሰጥቷት አንድ ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ብር ይቀራል። ታላቋ ደህና ሰው ሆና ቀርባ (እንዲያም ሆኖ ሳትሻል አትቀርም መሰለኝ) ኮንዶሚነም ቤት ገዝታ፣ ተከራይቶ እንዲህ ሆኖ ትጦሪበታለሽ አለችኝ አሉ።

(ቤቱን የገዙት ሴት “ድጋሚ ስህተት እንዳይሰሩ ብሩ አሁን በእርስዎ ስም ይቀመጥ። የሚፈልጉት ብር በሚኖር ጊዜ በመኪና ራሴው አድርሼ እመልስዎታለሁ። ግድ የሎትም።” ብላቸው ነበር። ግን ያው የእናት አንጀት አሸንፏቸው ልጃቸውን አመኗትና ነው።)

“ከህዳር 24 በኋላ ሄደሽ ኪራዩን ትቀበያለሽ አለችኝ። መልሳ ደግሞ ምንም ነገር የለሽም ብላኝ ቃሏን ታጥፋለች። እኔ መቁረቢያ ጨርቅ ጣዪብኝ። የቁም ተስካሬን ላውጣ ጸበል ጸዲቅ ላድርግ ብቻ ነው ያልኳት። ጭራሽ መቄዶንያ ግቢ አለችኝ። ይኽን ስናገር ያሳፍረኛል። በጣም ያሳፍረኛል። ግን ምን ላድርግ አሁን ከአቅሜ በላይ ሆኖብኝ ነው።” ያለቅሳሉ።

የእኔ እናት 😥

እኔ አፍ አፏን ያልኩበት እና፣ ከእናቴ ጋ ተጯጩኼ የማወራበት ጊዜ ሁሉ ፍም ላይ እንደቆመ ሰው ይለበልበኛል፣ እንዲህም ዓይነት አቅም ያለው ሰው አለ።

ስንቱ ሰው እናቱን ልንከባከብ ብሎ ፈልጎ በሕይወት አጥቷት በጸጸት እና ቁጭት ዝንታለም ያነባል፣ ለእናቱ “ሞት እምቢ” የሚል ስም ማውጣት የሚችል ሰው አለ። የሚገርመው ነገር ደግሞ እሷም ልጆች አሏት። እንዴት ነገን አላሰበችውም? እንዴት እንዴት ከፍተናል አቦ!? እሺ ከዚያስ??

መቼም ዕድሜ ይኑር እንጂ እግዚአብሔር ፍርዱ በምድር ነው። በገዛ ልጆቻቸው ክህደት ቢፈጸምባቸውም፣ የሚናፍቁትንና ቀሪ ጊዜያቸውን ማሳለፍ የሚፈልጉትን የንስሀ ሕይወት አግኝተው በእግዚአብሔር ዘንድ ተቀባይነት እንዳገኙ ሳይሰማቸው አልቀረም።

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s