ንጉሠ ነገሥት ምኒልክ በ፲፱፻ ዓ/ም የዠመራቸው በሽታ እየጸና ሔዶ በመጨረሻ ሰውነታቸው ዝሎ፣ አንደበታቸው ተዘግቶ እንደቆየ በታኅሣሥ ፫ ቀን ፲፱፻፮ ዓ/ም ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ። የሸዋ ንጉሥ (፲፰፻፶፯-፲፰፻፹፩) በኋላም፣ የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት (፲፰፻፹፪-፲፱፻፮) በነበሩበት ዘመን ሁሉ ክፉውን በክፉ ሳይሆን፣ ክፉውን በደግነት እየመለሱ ጥፋትን ሁሉ በትዕግሥት እያሸነፉ፣ አገር የሚሰፋበትን ልማት የሚዳብርበትን፣ ሕዝብ ዕረፍትና ሰላም የሚያገኝበትን ከማሰብና ከመፈጸም አልተቆጠቡም። የአውሮፓን ኃያል መንግሥት በጦር ሜዳ በማሸነፍ ኢትዮጵያን በዓለም እንድትደነቅ አድርገዋል።
የዳግማዊ አፄ ምኒልክን ዜና ዕረፍት በወቅቱ ለመደበቅ ቢሞከርም ወሬው ካንዱ ወደሌላው እየተላለፈ ነገሩን የተረዳው ሁሉ፣ «እምዬ ጌታዬ፣ እምዬ አባቴ» እያለ በየቤቱ ያለቅስ ነበር። ከአልቃሾቹ አንዱ፣
ፈረስ በቅሎ ስጠኝ ብዬ አለምንህም
አምና ነበር እንጂ ዘንድሮ የለህም፤አለ ይባላል። በንጉሠ ነገሥቱም ሞት ዋናዎቹ ሐዘንተኞች ባለቤታቸው እቴጌ ጣይቱ፣ ልጃቸው ወይዘሮ ዘውዲቱና ብዙ መኳንንት አሉ። በልቅሶውም ጊዜ እቴጌ ጣይቱ፣
ነጋሪት ማስመታት፣ እምቢልታ ማስነፋት ነበረ ሥራችን፣
ሰው መሆን አይቀርም ደረሰ ተራችን›› ብለው ገጠሙ ይባላል።
ከልጅ ኢያሱ ቀጥለው ንግሥተ ነገሥታት ዘውዲቱ ወለቱ ለምኒልክ ተብለው የነገሡት ልጃቸው ወይዘሮ ዘውዲቱ የሚከተለውን ሙሾ አወረዱ።
እልፍ ነፍጥ በኋላው፣ እልፍ ነፍጥ በፊት፣ ባለወርቅ መጣብር አያሌው ፈረስ፣
ይመስለኝ ነበረ ይኼ የማይፈርስ።
ሠላሳ ሦስት ዘመን የበላንበቱ የጠጣንበቱ፣
የትሣሥ ባታ ለት ተፈታ ወይ ቤቱ።
ብትታመም ልጅህ እጅግ ጨነቀኝ፣ ብትሞትስ አልሞትም እኔ ብልጥ ነኝ።
ወልደውኛል እንጂ እኔ አልወለድሁዎ፣ አንዠቴን ተብትበው ምነው መሔድዎ።
አሳዳጊ አላንተ አላውቅም እናት፣ ምነዋ ሞግዚቴ እንዲህ ያል ክዳት።
ቀድሞ የምናየው የለመድነው ቀርቶ፣ እንግዳ ሞት አየሁ ካባቴ ቤት ገብቶ።
እጅግ አዝኛለሁ አላቅሽኝ አገሬ፣ የሁሉ አባት ሞቶ ተጐዳችሁ ዛሬ።
ትንሽ ትልቅ አይል ለሁሉ መስጠት፣ ከጧት እስከ ማታ ያለመሰልቸት።
ድርቅ ሆኗል አሉ ዘንድሮ አገራችሁ፣ ዝናሙ ሲጠፋ ምነው ዝም አላችሁ።
አሻግሬ ሳየው እንዲያ በሰው ላይ
መከራም እንደሰው ይለመዳል ወይ።
/አቶ ተክለጻድቅ መኩርያ፥ «ዐፄ ምኒልክና የኢትዮጵያ አንድነት» ውክፔዲያ ላይ እንደተጠቀሰው።/