የለበስሽው ቀሚስ እገላሽ ላይ ነትቦ፣
የለበስሽው ሸማ፥ ልጅ ኑሮ ያሳደፉት፥ ከላይሽ ተስቦ
ወልደሽ ባሳደግሽው፣ ደም ጡት በቀለብሽው
ከመሶብ እንጀራ ባላጎደልሽበት፣ ጉያሽ በሸሸግሽው፣
በአብራክ ክፋይ እብሪት፣ ፊት ጀርባሽ ተነክሶ
ተስቦ ከመሬት የባንዲራው ጥበብ የነጠላሽ ጥለት፣ በደም ተለውሶ
ዘንግሽ ተቀንጥሶ፣ ክንድሽ በእንባ ርሶ
የማዕዘን ደንጊያሽ በቀን ጅብ ፈራርሶ…
ከሰው ፊት አዋለሽ፥ ቁጭት ኀዘን ትዕግስት ጽዋው ሞልቶ ፈስሶ
መከራ አስጨበጠሽ፥ የጊዜ ፍርድ ገንኖ፣ ኮረት አሳፍሶ
ዛሬ በልጅ ታየሽ ወጣሽ ከጎዳና
ምናል ቢያስከብርሽ መርቶት የእግርሽ ዳና?
ሁሉ እንዳገሬ ነው የነገርሽ ኩነት
ጥያሜ ግርጣትሽ፣ የጠጉርሽ ሽበት…
(ፀአዳ ገጻችን ላይ፥ ማድያትሽ ታይቷል
ልስልስ ገላችን ላይ ኩበት ገላሽ ጎልቷል
ከመጉበጥሽ እኩል ቀንተን ተራምደናል)
የቆዳሽ ሽብሽባት ጽፏል መከራውን
ኮስማና ገላሽም ከትቧል ግፉን ክሱን
ማን ችሎት አንብቦ ይስጥሽ ንጹህ ፍርዱን?
ምን አንጀት ራርቶ፣ ይታደግሽ ክንዱን?
ጥያሜሽ የአገሬ፣ መልክሽ የሰፈሬ
ኀዘንሽ የአገሬ፣ ገጽሽ የመንደሬ
ያደግኩበት ቀዬ ከወንዙ ከጨፌው
ከተጎነጨሁት ከምንጩ ጨልፌው
ከሜዳ ተራራው፣ ከድፍን ኢትዮጵያ
የተቀዳው ገላሽ፥ ሁኔታው የአገሬ
አዞረው ደም ሥሬን፥ ነገርሽ ነገሬ
አገርሽ አገሬ…
መች ቦታ አለው ለሰው?
ሰርክ ይወዛወዛል፣ ከባለጊዜ እጅ፥ የመከራ አለንጋ
በንጹህ ሰው እንባ፣ በምስኪን ደም እጥበት ይታደሳል ወንበር፣ ይታደሳል አልጋ
ከአንድ አገር ሊሴስን ሲቃትት ሲያነጋ፣
ለነውሩ ግልድም በዘር ዘር አዋርዶ፣ ይበልታል ስጋ
እርስ በርስ ሊያጋድል፣ በሰውነት ዋጋ እርስ በርስ ሊያዋጋ።
/ዮሐንስ ሞላ/