
ቤቱ ሲዝረከረክ “ለምን አንዷን አትጠቀልልም?” ብሎ መካሪም አለ።
ወንድ ልጅ ራሱን የጎዳ፣ ውጭ ውጭ ያበዛ እንደው “ኧረ በዚህ ኑሮ ላይ ትችለዋለህ? አንዷን ባለሞያ ፈላልገህ ማታገባ?” ይባላል።
ሸሚዙ የተወቀጠ የመሰለ እንደው “ኧረ ግድ የለህም አንዷን አግባ።” ተብሎ ይመከራል። ብዙ ነው ዐውዱ። ግን ያው ሁሉም “የምትገባው ሴት ሚስት ናት? ወይስ ሰራተኛ?” የሚል ጥያቄን የሚያጭሩ ናቸው።
ለዝርክርክ ወንዶች እንደ መድኃኒት የምትታዘዘው ሴት፣ ስትገባ አያያዟ የሚታወቅበት አይመስልም መበዳደሉ ለጉድ ነው።
በርግጥ “ለአንድ ብርቱ ሁለት መድሃኒቱ” ነው። የሴቶችን የማደራጀት እና የማዘጋጀት አቅምና ችሎታ ማጣጣልም አይቻልም። (ሆኖም ያ ችሎታቸው በተፈጥሮ ብቻ የሆነ ነው ብዬ አላስብም። የኑሮ ጣጣ እና ማኅበራዊ ሁኔታችን የጫነባቸው ይመስለኛል። አብዛኞቻችን፥ ከልሂቅ እስከ ደቂቅ በሴቶች ትከሻ ላይ ነው ቆመን የምንሄደው። አሁን አሁን የሰለጠኑ አባቶች እየመጡ ነው እንጂ፥ ለልጅ የሽንት ጨርቅ መቀየር አንስቶ ምግቡን እስከማሰናዳት ድረስ የእናቶች ድርሻ መሆኑን እናውቃለን። እናቶቻችንና እህቶቻችን ካልሲዎቻችንን ሳይቀር አጥበውልን፣ ልብሶቻችንን ፈትገው ቦታ ቦታ አድርገውልን ነው ያሳደጉን። እኛ ቀና ብለን አምረን እንድንጓዝ፥ እነሱ ጎንበስ ብለው ኖረዋል። አመስግነናቸው አናባራም!!)
ከኑሮ ጫና የተነሳ የሚያድርብን የማግባት ሀሳብ ቤቱን ቤት ያደርገዋል? ለልጃችን “እናትህን ያገባኋት ኑሮ ከብዶኝ እንድታስተካክልልኝ፣ ቤቱን መላ መላ እንድትለው ነው።” የማለት አቅም ይኖረናል? ልጆቻችንን ጊዜያቸው ደርሶ ስንድር፥ የተወቀጠ ሸሚዙን እንድትተኩስ የታሰበችበት ቤት እንድትገባ እንፈቅዳለን? የዘመመ አጥሬን ያቃናልኛል ብላ የትዳር ጓደኛ የምትፈልግ ሴት ብትኖርስ ሳይጎረብጥ ይዋጥልናል?
ይኽን ይኽን ሳስብ፥ ወዳጃችን ጋዜጠኛ እና ደራሲ Tewodros Teklearegay “የእኔ ሳሎን!” ብሎ በራሱ አንደበት ጭምር “ግራ የሚያጋባውን” ያለውን እጅግ የተዝረከረከ ሳሎኑን አስጎብኝቶን ነበር። በወቅቱ ስድብም ጭምር ለመቀበል ዝግጁነቱን ገልጾ ስለነበር፥ እኔም ፈቃዱን ተገን አድርጌ የበኩሌን ተንፍሼ ነበር። የማከብረው ወዳጄ እና የማደንቀው ባለሞያ ነውና አስተያየቴ ፎቶው የጫረው ነው እንጂ ሌላ አልነበረም። የሚያዝናኑ አስተያየቶችም ጭምር ሰፍረው ነበርና፣ ዝርዝሩን ለመዝናኛ ለመመልከት እነሆ ማስፈንጠሪያው። በዚያው ወዳጁ ሆናችሁ ቤቱን ተቀላቀሉ።
የእኔን ትኩረት የሳበው ግን ከአስተያየቶቹ መካከል በርከት ያለው ጎራ ውስጥ የሚመደበው ከላይ ያነሳሁት የ“ለምን አታገባም?” ዓይነት መሆኑ ነው። የተጀመረውም “ርዕሱን ሚስት የሻትን (ተኪላ ሳንል) ለት ቢባል ቴዲ” ከሚል ፈገግታ አጫሪ አስተያየት ነው።
“ሳሎንህ የሚስት ያለህ እያለ ይመስላል”
“You need to have a decent Habesha woman!”
“የምታገባህ ፈረደባት። ይብላኝ ለእሷ”
“አግባ ግድ የለህም”
“ቺኳ የታለች?”
“አይ የሠው ነገር እኔ የምመክርህ አግባ ብዬ ነው”
“አግባ አግባ”
“…ቶሎ ብለህ አግባ ግን ያው ከከተማ ፅዳትና ውበት ቢሮ እንደሚሆን ላንተ አይመከርም”
“ቴዲ ይሄ ሁሉ የሆነው አነተ ያዝረከረከውን ወጣ ስተል የምትሰበስብልህ በለማዘጋጀትህ ነው…”
“….ከትዳር በፊትና በሆላ ብለህ ደሞ ትዳር ስትይዝ የቤትህን ሁኔታ ብታሳየን ደስ ይለኛል።”
“የባለትዳር ቤት አይመስልም”
“አለማግባትህን ወደድኩት”
“ሴትዮዋ ብትኖር እንዲህ አይሆንም ነበር፤ አስብበት።”
“ምንድን ነው መዝረክረክ? አንዷን አስገባ እንጂ…”
“…አየህ ሚስት እንኳን የለህም…”
“ሚስትህስ የለችም ወይስ….”
“ሚስት የለህም ማለት ነው?” ብሎ የጠየቀና፥ ማርከሻውን “የእሷ የሆነ ነገር ስላልጻፍክ ነው” ብሎ ያስከተለም አለ።
“ሚስት የቤት ሰራተኛ ነች??” ብሎ የጠየቀ እና “ለማለት የፈለገችው ብታገባ እንድትዝረከረክ እድል አትሰጥህም፤ ቆማ አንድ በአንድ ታስለቅምሀለች ለማለት ነው እንጂ እሱ ያዝረከረከውን እሷ ታስተካክላለች ለማለት አይደለም፡፡” ብሎ ያስተባበለ አዎንታዊ አስተያየት ሰጪዎችም አሉ።
እንዲሁም “ሚስት የለኝም ለማለት ነው በጣም ሚገርመው ኮሜንቶችህ ላይ አግባ ያሉ ብዙዎች ናቸው ለሰራተኝነት ነው ምትመጣው ወይስ ለሚስትነት? ደሞ ቤት ሲዝረከረክ ነው ሚስት ምትታወሰው” ያለ ሌላ አያዎ አስተያየትም አለ። “ሚስት የለኝም ለማለት ነው” አባባሉ ያው ሚስቶች ሚናቸው ቤት ማስተካከል እንደሆነም ጭምር ማውሳቱ ይመስላል። ቀጥሎ ደግሞ “ለሰራተኝነት ነው የምትመጣው ወይስ ለሚስትነት?” ብሎ ይጠይቃል።
“…በጊዜ አግብተህ ቢሆን እንዱህ አትሆንም ነበር ጓደኛዬ አሁንም አረፈደም ግን እንዲህ አዝረክርከህ እንዳትጠብቃት” ያለ አስተያየት ሰጪም አለ። ይኼም ያው አያዎ ነው።
በመሀል ቴዲም “ኧረ ጎበዝ ሰው እንዴት ተጨካክኗል? ወንዶቹስ ግድ የለም የራሳቸውን ቤት ደብቀው ይሳደቡ። ከሴቶቹ ግን እንዴት አንድ እንኳን “ልምጣና እናስተካክለው” የምትል ትጠፋለች ? ትዝብት ነው።” ብሎ እንደ ቀልድ ጽፏል።
እንዴት ነው ነገሩ?
ሚስቶቻችንን የምናገባው ለምንድን ነው? ለተዝረከረከ ቤታችንን እንዲያስተካክሉ የምናምናቸው እና እነሱን የምንጠብቅ ከሆነ፣ በሌሎች ጉዳዮቻችን ላይስ ላለማሳተፍ (to be inclusive) ምንድን ነው የሚያግደን? ማኅበረሰቡ ግማሽ በግማሽ ጎራ ለይቶ የሚበዳደልበት ጉዳይ ነውና ያሳስባል።
ሰላም!
#Ethiopia