ወዳጆቻችን በፍቅር ስም ከነነውራችን፣ ከነጉድፎቻችን እንድንኖር ይፈርዱብናል። ሰው ግድ ሰጥቶትም ሆነ፣ በተፈጥሮው የመመልከት እና የመተቸት ዝንባሌ ኖሮት አስተያየት ሲሰጥ፣ “ቅናት፣ ጥላሸት፣ ምቀኝነት” የመሳሰሉ ኮተቶች ተጠቅመን ስም በመስጠት ዝም እንዲል እናሸማቅቀዋለን። “እሽ እሽ” እንላለን። ሁነኛ ወዳጆችን ሁሉ እናሳጣለን።
የወደድነው ሰው የተነቀፈ ስለመሰለን ብቻ ፍቅራችን ተንጣፎ ያልቅ፣ የዚያም ሰው የአገልግሎት ዘመን ያከትም እናስመስለዋለን። ‘ምናልባት ቢፈተን ይወድቃል’ የሚል የምንወደውን ሰው አቅም የመናቅ እና፣ ብቃቱን የማቃለል ቅድመ ስጋት ስለሚያድርብን፣ በተወዳጁ ሰው ዙሪያ የሚኖር የተለየ ንግግር ሁሉ የጠላት ድምጽ ይመስለናል። በዚህ ባህርያችን የተነሳም፣ ለምንወደው ሰው ውዳሴ እንኳን ተጽፎ ካልተረዳነው፣ አፋፍ ለማለት እና አትንኩት ለማለት እንሽቀዳደማለን።
በተለየ ዐይን ተመልክቶ አስተያየት የሚሰጠው ወይም የሚተቸው ሰው “ምን ቸገረኝ” ብሎ ነገር ዓለሙን ቢተወው፣ እኛ የምንወደው ሰው ስላልተተቸ ደስ ይለናል፤ ለጊዜው አሸንፊ መስለን እንረጋጋለን። ነገር ግን፥ የምንወደው ሰው ማግኘት ሲገባው ባሳጣነው ትችት የተነሳ፣ መገንባት የሚችለውን ያህል ላይገነባ፣ ወይም ባለበት ቁመና ጸንቶ ላይቆይ ይችላል። በአሳዛኝ ሁኔታ ግን፥ ወዳጆች በውድቀት ተባባሪነት ሲጠቀሱ እና ሲወቀሱ አይታይም። ልብ ብለን ካጤንነው፥ ከተኮፈሰ እኔነት (ego) ቀጥሎ፥ ዋና ጠላቶቻችን ወዳጆቻችን ናቸው።
ለምሳሌ፥ በጣም የተወደደን ሙዚቀኛ የሚተቹ ሰዎችን ገፍተን ጠላት እናደርጋቸዋለን። የትችታቸውን መሰረት መርምሮ ከመሟገት ይልቅ፣ በጠላትነት ኩታ ጠቅልለን ዳር ለማስያዝ እንጥራለን። በዚህም የተነሳ፣ የተወዳጁን ሙዚቀኛ ተሳትፎ በእኛ የኑሮ ክልል እና ማዕቀፍ ብቻ እንወስነዋለን። በዓለም መድረክ፣ በብዙ ቋንቋ ተናጋሪዎች ዘንድ ሳይቀር መታወቅ እና መወደድ የመቻሉን ነገር ከስር እናስቀርበታለን።
ከዚህ በላይ ጠላትነት ከወዴት ይመጣል?
ከጠላት ክፉስ የወዳጅ ጠላት፣
‘አትንኩት’ ብሎ፣
ያፈቀረ ሰው… ያገዘ መስሎ፥
ትጋት እድገትን የትም ‘ሚጥላት
ዕንደጠባቂ ከአዳኝ ‘ሚያስጥላት!
/ዮሐንስ ሞላ/