3 ወሩ እና አብዮት ጥበቃው…

ዋዜማው፥ በጠቅላዩ ፍቅር በጨበጣ የተነደፉ ሰዎች አላስ ሆኑብን። መተንፈሻው፣ መላወሻው ቸገረን። ከምንግዜውም በላይ ሀሳብን የመግለጽ መብት እና ነጻነት አደጋ ውስጥ እንደወደቁ ተሰማን። ነገሩን ይበልጥ አስደንጋጭ ያደረገው፥ አፋችንን ለመዝጋት ላይ ታች የሚሉት የገዛ ወዳጆቻችን እና፣ ትናንት በክፉም በደግም አብረን የጮኽን መሆናቸው ነው። የመታፈንን ህመም ያውቁታል፣ ዝም የማለትን እዳ ይረዱታል… የምንላቸው መሆናቸው ነው።
 
“ኀዘንሽ ቅጥ አጣ
ከቤትሽ አልወጣ፤
ገደለው ባልሽ፤
የሞተው ወንድምሽ!”
ዓይነት ሆነ።
 
ኮካው ማረኝ ማረኝ
ኮካው ማረኝ ማረኝ
የዘንድሮስ ካድሬ ጭራሽ አላማረኝ
ብለን ለመጫወት እና ነገሩን ለማዋዛት ሞከርን።
 
ሰውዬው አፈወርቅ ጮሌ ነው። ይናገራል፣ ይናገራል… እንደ ጥዑም ምላሰኛ አፍቃሪ፥ አታላይ የሚባል ዓይነት ነው። ምነው ሲያወራ ውሎ፣ ሲያወራ ቢያድር ያሰኛል። ቢፈልግ ከጸሀይ ጋር ይነጋገራል፤ ቢፈልግ ጨረቃን ለቅሞ ቤታችን ያሳድራታል። አንጀታችንን ቅርጥፍጥፍ አድርጎ በላው፤ በተስፋ ተሞላን፤ ደስም አለን። በየምኩራቡ ተጸለየለት (አሁንም ቢሆን የአገር ጠላት ካልሆነ በቀር፥ የማይጸልይለት፣ መልካም የማይመኝለት የለም) በተለይ ለአመታት በነገር ከመቁሰላችን አንጻር፣ በንግግር አለመደሰት እንዴት እንችላለን?
 
ቀድመው ቀብድ ፍቅር አስይዘው ያቀነቀኑለት በኩራት ሆነው፣ ስጋት እና ጥርጣሬ ያደረብንም ከነጥርጣሬያችንም ቢሆን ማረጋጋቱን ወደነዋል። ‘ወሬው ወደተግባር ይለወጥ፣ ተቋማዊ ይሁን’ ስንል፥ እኛ ጊዜ የመስጠትና የመንጠቅ አቅም ያለን ይመስል፥ ግማሹ “ጊዜ ስጡት” ይላል። ግማሹ “ፖለቲካ ስለማታውቁ ነው” ይላል። ግማሹ ዝም ብሎ “እሽሽ” ይላል። ቀድመው ስም በመስጠት ማሸማቀቅ ተያዘ።
 
አገሩ ከደረ፣
መንደሩ ከደረ
አበል መክፈል ቀረ
አልን።
 
ፓርላማ ላይ ቀርቦ የፓርቲውን አሸባሪነት ያመነ ጊዜ፥ ሁላችንም ቁስላችን ታኮልናልና እጅ ሰጠን። እንዳንጠላው ሆነን ወደድነው። (ሲፈጥረን ፈርዶብን፥ የምንደነቅበት እና የምንጠይቀው አናጣም መቼስ። “እንዲህ ዓይነት ልብ እያለው፣ እንዴት ሲረገጥ እና ሲሾም ኖረ?” ብለን ጠየቅን። “ግን እንኳን ችሎ ኖረና፣ ይህን ቀን አየን” ብለን ተደስትን።)
 
ካድሬነቱን እንደርስት የሚቆጥሩትም ኖሩና፥ ቀድመው ባልከደሩት ላይ ሙድ መያዝ ያማራቸው ሁላ ነበሩ። ለነገሩ የእኛ ሰው ጸባይ አስቸጋሪ ነው። ጠዋት ቀድሞ ስለተነሳ እና ማታ አርፍዶ ቤቱ ስለገባ፥ ጸሐይና ጨረቃ የተሻለ ዘመዶቹ የሚመስሉት ደነዝ ሁሉ አለ። ከእነዚህም ጋር ነው የምንደመረው።
 
“ከጎኔ ቁሙ! አብዮቱን አጣብቁኝ! አግዙኝ! ተደመሩ” ብሎ ነዳን… ተደምረን ተነዳን። ሆ ብለን ወጣን! “እንኳን ዘንቦብሽ፣ እንዲሁም ጤዛ ነሽ” አፍላ ካድሬዎቹ ሰበኩን፥ ሁሉም አብዮት ጠባቂ ሆነ። “በህልሜ ነው በእውኔ” አልን። ህልምም ከሆነ ምነው ከዚህ ህልም ዘላለም ባልነቃን ብለን ተመኘን።
 
ቦንቡ ሲፈነዳ፣ እንቡጡ ፍቅራችንም አብሮ ፈነዳ። “ባሌን ጎዳሁ ብላ” አለች አሉ። ጭራሽ ፍቅር በፍቅር አደረጉት። አዲስ አበባ አበባ ሆነ። እንዳዲስ አማረበት። “ከሱ ያስቀድመኝ” አልን። “አብይ ድረስ” ብለን ማልን። ጠላትም ደስ እንዳይለው፣ ሁሉም ሰው ከአብይ ጋር ነኝ አለ። እኛም ፈንጥዘን ሁለት ሽንጣም ግጥሞች አዋጣን። ለሰፊው ሕዝብ ጥቅም ስንል፥ “ከ60 ክፍል በላይ የጫርናት ባይገርምሽ መዝጊያም ይሁን” አልን። “ተመስገን የሰራዊት ጌታ! ስራህ ግሩም ድንቅ ነው!” አልን። አሁንም በዚያው ስሜት ነን! በ3 ወር ውስጥ የተመለከትነው ተአምር ነው!
 
(በበኩሌ፣ በመንግስት ደረጃ አንድ ሰው ብቻውን ቆሞ ሲታይ ደስ አይለኝም። አምባገነን ከማድረግ ግብ የዘለለ ጥቅም አለው ብዬም አላስብም። ስንንሰፈሰፍለት፣ ውሎ አድሮ ስዩመ እግዚአብሔር ነኝ ቢል ይፈረድበታል? ያኔ እኔ ነኝ ጠበቃ/ተሟጋች የምሆንለት!
 
በአመራር ደረጃ አንድ ሰው ብቻ ሲታይ፥ ለጠላትም ከልብ አያስደነግጥም፤ ለወዳጅም አያስተማምንም። እሱ አንድ ነገር ቢሆንስ? ብሎ መሳቀቅ አለ። በርከት ብለው ስለቡድን፣ ስለግብረ ሀይል ቢያወሩ ግን፥ ሕዝብ ነገሩን የአንድ ሰው ህልውና ጉዳይ ብቻ አያደርገውም ነበር። አንድ ሰው ላይ የተንጠለጠለ ነገር ሁሌም ሰቀቀን ነው ትርፉ። መቼስ ማልጎደኒ? እሱ ደሞ ለጉድ ተመችቶታል!
 
የእናቱን ትንቢት የሚያምን ሰው መሆኑ ሲታሰብ ደግሞ የስጋቱን ዙር ያክረዋል። እናቱ ግን የንግስና ዘመኑን ዕድሜ ነግረውት ይሆን? እሱን ማወቅ ተስፋ ሊሆነን ይችላል። …ልጅ ሆነን፣ ኢሳያስ አፈወርቂ በሞተር ሳይክል ሄዱ፣ ከሕዝብ ጋር ፓስቲ ጠብሰው በሉ፣ አጋጭተው ጨበሱ፣ ከአብሯደጋቸው ጓዳቸው ጋ አንጓ በድንጋይ ፈንክተው ጋጡ ዓይነት ወሬዎችን ስንሰማ፣ አፋችንን ከፍተን በቅናት እናርር የነበረው ሁሉ አሁን ትዝ አለኝ።)
 
ያም ሆነ ይህ፥ ሰዉ በደቦ ሆ ብሎ ወጣ። ካናቴራው ተለበሰ፣ ተጮኸ፣ ባንዲራው በየቀለሙ ወጣ! አይናችን እያየ ጠላት አይኑ ደም ለበሰ። አብዮት ጥበቃው ተጠናክሮ ቀጠለ! እሱም በመናገር ላይ ነው።
 
በድግሱ ማግስት፥ ሁላችንም አብዮት ጠባቂዎች ነን እንዳላልን፣ የተሻልን የቅርብ አብዮት ጠባቂዎች ነን የሚሉ ከእግር እግር እየተከተሉ አላናግር አሉን። መንግስት ሲባል፥ “አብይን አትናገሩት” ይላሉ። የህግ የበላይነት ሲባል፥ “አብይን ለቀቅ” ይላሉ። ህዝብ አለቀ ሲባል፤ “የወያኔ መጠቀሚያ አትሁኑ” ይላሉ። ይህቺ ናት ጨዋታ! ይህቺ ናት አብዮት ጥበቃ!
 
“ከጌዲኦ ከ8 መቶ ሺ ሰው በላይ ተፈናቀለ” ሲባል፥ የአብይ ስም ምን እንደሚሰራ አላውቅም። “አብይን አትተቹ፤ ጊዜ ስጡት” ይሉናል። “ከጎኑ ቁሙ” ይሉናል። ከዚህ በላይ ከጎን መቆም አለ? (ነገሩ እናንተ እና እኛ መባሉም ያበግናል) እንግዲህ እግዜርም ሰይጣንም እንደሚያውቁት፣ አብይን ሁላችንም ልብ ውስጥ ጉዝጉዝ ብሎ ገብቷል። እንወደዋለን።
 
(በበኩሌ፥ ፓርላማ ላይ በሀቅ ወቅት (moment of truth) በተናገረው ንግግሩ ብቻ፣ ከእንግዲህ ምንም ቢያደርግ በማይነቃነቅ መልኩ ልቤ ውስጥ ቦታ አግኝቷል። “እስካሁን ምን ነክቶት፣ እንዴት ችሎ ነበር ከነሱ ጋር የቆየው?” እንዳልኩ ሁሉ፣ “ምን ነካውና እንዲህ ሆነ” እል ይሆናል እንጂ በፍጹም አልረሳውም።)
 
አብይን መውደድ ግን እውነትን እንዲጋርድብኝ አልፈልግም። አብይን መውደድ፣ ረዳት አጥቶ በክረምት ከቤቱ የተፈናቀለን ሰው ለቅሶ ባላየ/ባልሰማ ማለፍ አልፈልግም። ገና ለገና አብዮት አይጠበቅም ብዬ ሕዝብ ላይ መጨከን አይሆንልኝም። ለአብዮት ጥበቃ የሚደረጉ ነገሮች ጎጂነትንም በታሪክ የማውቀው ነውና፣ በአብዮት ጥበቃ ስም፣ ህሊናዬን ማቁሰል አልፈልግም። ሁላችንም ቆም ብለን ማሰብ ያለብን ጉዳይ ነው።
 
ኢህአዴግ ከአእምሮ በላይ በሆነ መልኩ፣ በማይታመን ሁኔታ፣ በአረመኔነት ግብሩ የተጫወተባቸው ሰዎች ሰቆቃ በገዛ በኢህአዴግ ቲቪ ነው የሚቀርበውና የምናየው። ተሳታፊዎቹ በተናጥል፣ ድርጅቱ እንደአሸባሪ ድርጅትነቱ መጠየቅም አለበት። ጭራሽ ይህን ሁሉ በደል አድርሰውባቸው፣ በመንግስት ይቅርባይነት/ምህረት ነው የተፈታችሁት ሲባል ያበሽቃል።
 
ትናትንና “ኸከሌ ታሰረ” ሲባል “አርፈው አይቀመጡም ነበር፤ ሳይነካኩማ አይሆንም” ያልን፣ የመብት ጥሰቶችን ያዩ ሰዎች ሲያሰሙን “እንደዚህማ አይደረግም፤ ተጋነነ” ስንል የነበርን “አርፋችሁ ተቀመጡ። አትጻፉ” ያልን ሁሉ በራሳችን ፊት ልናፍር እና ንስሃ ልንገባ ይገባናል። ይህን የፈጸሙ፣ ያስፈጸሙ፣ አቅም እያላቸው ሲፈጸም አይተው ዝም ያሉ ሁሉ በይቅርታ ሊታለፉ ቀርቶ፣ በህግ ሊጠየቁ ይገባቸዋል።
 
እፈራለሁም፥ አብዮት ጠባቂነታችን እና የአብዮት ጥበቃው ፍላጎታችን፣ የዶ/ር አብይን መንግስት አምባገነንነት ገና በአፍላነት እንዳያደርገው።
 
የለውጥ ሳይሆን፣ የጭካኔ እና የፍርሃት ስርወ መንግስቱን (fear regime) አጠናክሮ የማስቀጠል ዓላማ ያለው ከሆነ፥ አብዮቱ ፍግም ይበል። ካልሆነ ደግሞ፣ በአስተያየቶች ይጠናከራል፣ ደካማ ጎኑን ፈትሾ ይበረታል እንጂ፣ በትችት እና በጥያቄ፣ በድረሱልኝ ጩኸት የተነሳ ምንም አይሆንም። በአስተያየት የሚበላሽ ከሆነ ግን፣ ችግሩ ከተፈጥሮው ነው እንጂ ከአስተያየቱ አይደለም!
 
እግዚአብሔር አገራችንን ይጠብቅ! ለመሪዎቹም ለተመሪዎቹም ልቡና ይስጠን!

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s