የልጅነት ሌቦች ሲያዙ…

የቂም ጅማታቸው፣ ስለተበጠሰ
ፍቅርና ናፍቆት አየር ላይ ነገሰ፤
ይኸው መልኳ መልኬ፥ የእናቷ የእናቴ፣
በጅል ጥል ተነጥቆ የሄደው ከፊቴ…
ያ የልጅ እውነቴ፣ ያ ጣፋጭ እውቀቴ
 
ክፉ ደጉን ሳላይ የወጋኝ ጨርሶ፣
በወተት ጥርስ ሳልጠግብ ወተት ያስለቀሰኝ
ወተት ሳላጣጥም የተጋትኩት ኮሶ፥
ይኸው ስጋ ለብሶ፣ ይኸው ስስት ጎርሶ።
36856417_1975566429121274_3222020242813222912_n
 
“ዝሆኖች ተጣልተው የሰበሩት ድልድይ” እነሆ ይፋዊ ጥገና ተደረገለት። ግሩም ድንቅ ነው! “ውጡ ውጡ” ተብለው ተዋክበው ከየከተማው ሲባረሩ ምስክሮች ነበርን። ልጅነታችን አብሮ ተሰዷል። ተዘርፈናል። እነሱ ለያዩን እንጂ፣ ሕዝቡ ልቡ አንድ ላይ ነበር። ድንበር ላይ ያለውን የታዘቡ ሰዎች ያካፈሉንን ታሪክ ማስታወስ ይበቃል። ወይ ደግሞ በሰው አገር ላይ ስንገናኝ የሚሰማን የቤተሰብነት ስሜት ዋቢ ነው።
 
“ከኽከሊት/ኸከሌ የገዛሁት” እየተባለ እንደታሪክ የሚወሩላቸው የኤርትራውያን ወገኖች ቁስ እኛ ጋር አለ/ነበር። እንዲሁ አስመራም ከእኛ የገዟቸው አይጠፉም። ጠረናቸውን በተቀባብለን ነበር። ይህችን ግጥም 2ኛው መጽሐፌ ውስጥ አካትቻት ነበር።
 
የልጅነት ሌባ
————
ገና ክንፏ ሳይጠነክር፣ የልጅነት ጫጩት ወፌ፣
“ቆመች፣ ሄደች” ሳልላት፣ ሳትነሳ ከበራፌ፣
በወጉ ሳትወጠወጥ፥ የፈጨናት ቀይ ሸክላ፣
የቅጠል እንጀራችንም ዐይኗ ሠምሮ ሳትበላ፣
ከምጣዱ ሳናወጣት፥ ያ’ፈር ጥቢኛችን በስላ፣
ቆጥረን ሳንከፋፈል፥ የወረቀት ብር ጠገራ፣
የቤት ወጪ ሳንሰጣጥ፣ ሒሳቡንም ሳንሠራ፤
 
ባባት ወግ – ሙክት ሰንጋውን፣
በናት ወግ – ጠጅ ጠላውን፣
ሳናሰማምር ሳናደርስ፣
ዳሱን ሳንጥል፣ ሳናፈርስ፤
 
ሳር፣ ቀጤማውን ጎዝጉዘን፣ ዕጣን ሰንደሉን ሳናጨስ፣
ሻይ፣ ቡናውን ሳናፈላ፥ በቆርኪ ቀድተን ሳናደርስ፣
እናት አባት፥ ተከፋፍለን፣
ባልና ሚስት ተደላድለን፣
ሌባ ፖሊስ፣ አሽከር ንጉሥ፣ ተመዳድበን ሳንጨርስ፣
ሽለላ ፉከራው ሳይደርስ፣ ‘ዘራፍ’ ብለን ሳንተኩስ፣
ከደስታችን ማማ ደርሰን፥ እቃቃችንን ሳናፈርስ፣
እንባ፣ ማሽላችን ‘ረግፎ፣ ዳቧችንን ሳንቆርስ፤
 
ነፃነቴን ቀምተኸኝ. . .
ነገር ዓለሜን ነጥቀኸኝ. . .
ሠርክ እጓዛለሁ በሐሳቤ፥
ደፍሬ መንገድ አልጀምር፣ እሟገታለሁ ከቀልቤ፣
ማጣት ማግኘቴን ሳላስብ፣ እኳትናለሁ በልቤ፤
 
ከራሴ ጋራ ስዶልት፣ በልሂድ ልቅር ሳቅማማ፣
እንኳንስ የኔን ወፍና፣ ጅብ ማልመድህን ስሰማ፣
 
ሳዝን እንዳልሞት ፈርቼ፥ ወፌ ከሌላ ለምዳ፣
ባጣትስ ብዬ ሰግቼ፥ ወፌ ከሌላ ሄዳ፣
ከኹለት ያጣ ጎመን ሆኖ፣ ድኩም ልቤ እንዳይጎዳ፣
በእንግድነቴ እንዳላዝን፣ ከሰው ቦታ ሆኜ ባዳ፥
 
መንገድህን እፈራለሁ. . .
በተስፋ ጭላንጭል ብርሃን፣ ነፃነቴን አልማለሁ።
 
ሐሳብ ካ’ሳቤ ሲማታ፣
ልቤ ሲነድድ በትዝታ. . .
ላ’መል ‘ጮሃለሁ ጧት ማታ፤
“የማያውቁት አገር፣ ድሮም አይናፍቅም፣
አርፌ ልጠብቅ፣ አልሂድበት የትም።
‘በነጠላ ጫማ፣ በእኔ አረማመድ፣
እንዴት ይዘለቃል የአስመራ መንገድ?’
 
የገባም ላይወጣ፣ የወጣም ላይገባ
__ኹሉም ቀረ ታስሮ፣
በርና መስኮቱ በጅል ጠብ ተሰብሮ።”
 
/ዮሐንስ ሞላ (2008) “የብርሃን ሰበዞች” ገጽ 104/
 
ዛሬ ይህንን ለመመስከር መብቃታችን፣ እንደያኔው እድለቢስነታችን ሁሉ እድለኛ ያሰኘናል። ሆኖም ግን ጉያችን ውስጥ፣ እርስበርስ ያለን ፍቅር እና አንድነት በዘራፊዎች እንዳንነጠቅ፣ በጥላቻ እንዳይሸረሸርና፣ ኋላ ለመመለስ ዘፈንና ግጥም ከምንደረድር በፊት እንንከባከበው።
 
“ነበር ለካ እንዲህ ቅርብ ነበር” 🤔
 

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s