መለስ፣ በረከት፣ አብዲ ኢሌ፣ ደመቀ መኮንን፣ ሼኽ አላሙዲን፣ ጭብጨባው፣ የዛሬ ደማሪ ተደማሪው፣ የትናንት አጋፋሪው ሁሉ፣ ኢህአዴግ ወዘተረፈ…

3-199x300
☞ መለስ የዛሬ 9 ዓመት፣ ኢህአዴግ ጉባኤውን ሐዋሳ ባካሄደ ወቅት “ኢህአዴግ እቅዱን ለማሳካት ቢያንስ እስከ 50 ዓመት በስልጣን ለመቆየት አቅዷል” ነገር ብሎን ነበር።
 
በ57 ዓመቱ ክልትው አለ!
 
☞ በረከት ስምዖን የዛሬ 7 ዓመት ገደማ፣ “የሁለት ምርጫዎች ወግ” የተሰኘ መጽሐፉን በሸራተን አዲስ ባስመረቀበት ወቅትም “ኢትዮጵያ እየተጓዘችበት ባለችበት የልማት ጐዳና ቀጥላ ውጤታማ ለመሆን 30 እና 40 ዓመታት ያስፈልጋታል” ብሎ ነበር።
 
ለጊዜው ከብአዴን ማዕከላዊ ኮሚቴ ታግዶ፣ የሰይፉ ፋንታሁን እንግዳ ሆኗል!
(ሰይፉ እና ሼኹ፤ ሼኹና በረከት
እንደ ጊዜው ፀባይ እንከረባበት…?)
 
☞ በመጽሐፍ ምረቃው ወቅት ከሼኹ ጋር ሲደናነቁ፣ ሲወዳደሱ ነበር። መለስም አልቀረ። ኢህአዴግ “የሕዝብ ፍቅር ያለው ፓርቲ” ተብሎም ነበር። እነ ዶ/ር ብርሃኑም በሰፊው ተብጠልጥለው እንደነበር በወቅቱ ሰምተናል። እሱ ያሰማራቸው ኮካዎችም ፌስቡክ ላይ ይጽፍ የነበረውን ወጣት መውጫ መግቢያ አሳጥተው ነበር።
 
የአላሙዲን ክፉ ደግ እንደተዳፈነ፣ ዶ/ር ብርሃኑ ወደ አገር ቤት ሊገባ ነው!
ኮካዎቹም፥ የሰሜኖቹ ገሚሱ አብን፣ ከሚሱ ድብን ብለው ሲከፈሉ፤ የወደምህራቦቹ የመሀል አገሮቹ ደግሞ በቲሸርት አሸብርቀው “ተደምረናል” ብለውናል!
 
☞ “ደራሲዎች፣ ድምፃውያን፣ ቲያትረኞች፣ የፊልም አክተሮች፣ ሰዓሊያን፣ የማስታወቂያ ባለሞያዎች፣ ጋዜጠኞች፣ ባለሃብቶች፣ የኢህአዴግ ባለሥልጣናት እና ሌሎች ተጋባዦች አዳራሹን ሞልተውታል። …መቀመጫዎቹ በሙሉ ተነስተው እድምተኛው ቆሞ የዝግጅቱን መጀመር ይጠባበቃል።” ብላን ነበር ፕሮግራሙን የታደመችውና ሁኔታውን በአዲስ አድማስ ጋዜጣ አካፍላን የነበረችው Tsion Girma Tadesse (ጺዬ፥ ከትናንት በስቲያ ስጽፈው ጽሁፉ ያንቺ እንደነበር ስለተዘነጋኝ ይቅር በዪኝ)
 
ዛሬስ አማን ነው? ወደ ቤመ “ቦታ ቀየረ እንጂ ድሮም ሞቶ ነበር” ዓይነት ሳይሆን አይቀርም።
 
☞ በዕለቱ የክብር እንግዳው በወቅቱ የት/ት ሚኒስቴር የነበረው፣ አሁን ደግሞ “የለውጡ አጋፋሪ” አቶ ደመቀ መኮንን ነበር። “ተመራማሪዎችና የተለያዩ ተቋማት በኢትዮጵያ ዲሞክራሲያዊና የልማት ተቋማት ላይ ለመመራመር እና የዳበረ ሐሳብ ለማምጣት የአቶ በረከት መጽሐፍ መነሻ ሊሆናቸው እንደሚችል እምነታቸው እንደሆነ ገለፁ።” ተብሎም ነበር።
 
የት/ት ፍኖተ ካርታው ላይ በማጣቀሻነት ተካቷል ወይ?
 
☞ “የመጽሐፉ፤ መታሰቢያነት ለትግሉ ባለቤቶች፣ ታጋዮች፣ የልጅነት ዕድሜያቸውን ለሠላምና ለዴሞክራሲ በተለይ በትግሉ ወቅት ላሳለፉት ታላቅ ከበሬታ የሰጠ እና ለማስታወስ ያለመ ነው” ብሎም አክሏል አቶ ደመቀ! ታዛቢዋ “አቶ ደመቀ የገለጿቸው ታጋዮች በአቶ በረከት መጽሐፍ የቱ ጋር እንደተጠቀሱ ፈልጌ ማግኘት አልቻልኩም።” ብላን ነበር።
“በምን አወቅሽበት በመመላለሱ
ሲታሰር ወደ እኔ፣ ሲፈታ ወደሱ”
 
አላሙዲንም ታስሯል፤ በረከትም ከስሯል፤ አንድ ለእናቷ አላሙዲን ላይ “የተነበየችው” እህተ ማርያምም ንግስተ ነገስት ነኝ ብላለች! ሃሃሃ…
 
☞ “ኢህአዴግ አስተዋይ እና አገሪቷን ከእንቅልፏ የቀሰቀሰ ድርጅት ነው” በማለትም ፓርቲያቸውን አሞካሹ። በሕዝብ ስለመፈቀሩ እና ስለመመረጡም መወራቱን ነግሮን ነበር። ጠቅላይ ሚኒስትር አብይም ስለኢህአዴግ የተመሰከረ ዊዝደም ነግረውናል።
ኢህአዴግ ወይም ሞት!?
☞ አላሙዲንም በዕለቱ፥ “አንዳንድ ሰዎች ኢህአዴግን ትወዳለህ ይሉኛል። አዎ! እወዳቸዋለሁ አራት ነጥብ።…”
 
“አቶ በረከት እንዳለው ደቡብ አፍሪካ ሄጄ ጠይቄዋለሁ፤ የጠየኩት ግን አመፀኛ እና ልውጣ ብሎ ስለሚያስቸግር ነው። ታከም፣ እረፍ ሲባል እሺ አይልም። እኔ ደቡብ አፍሪካ ሄጄ መጀመሪያ ያደረኩት ክፍሉን በሴኪዩሪቲ ማስከበብ ነበር። እሱ ግን በኋላ የብአዴን 25ኛ ዓመት በዓል ላይ ካልተገኘሁ ብሎ አስቸገረ ቃል አስገብቼ ይዤው መጣሁ። በ48 ሰዓት ውስጥ አንጠልጥዬ መለስኩት፤ እኔን የሚያሳስበኝ የጤናቸው ጉዳይ ነው።” በማለት ሚስጥራቸውን አጫወቱን።
የድርጅት ፍቅር!?
“እንደዚያ ስወድሽ፣ አብልጬ ከራሴ
ያሰብሽው ሲሞላ፣ ከዳሽኝ ወይ ነፍሴ?
ይህቺ ናት ወይ መልሴ ዳራራራን ዳራን”
 
አብዮት ልጆቿን ትበላለች! ምጽ ምጽ
☞ “በመጨረሻም ሼኽ መሐመድ “እስከ ህይወት ፍፃሜ ድረስ አብረን ነን” ሲሉ ማሉ። አቶ በረከትም በጭብጨባ መሐላውን አፀኑላቸው። ታዳሚውም አጨበጨበ። አጨብጭቦም ወደ ቤቱ አልሄደም። “ምን ጠፍቶ” የተባለለትን የሸራተንን ድግስ እስኪበቃው ተቋደሰ።” ብላን ነበር ጺዮን።
“ሩቅ አሳቢ፣
ቅርብ አዳሪ”
 
☞ የዛሬ 7 ዓመት በ40 ዓመት እንቆያለን ወሬው በሽተንጨርጭሬቄ ይኽችን ጭሬ ነበር፤
 
እዚህ ቅርብ ነውና፣ የሩቅ አሳቢ አዳሩ፣
በምኞቱ ልክ ይሰንዝር፣ ላይቀር ሳይደርስ ማፈሩ፣
ለማይቀር ቀኑ ሲመጣ፣ በሰፈሩት መሰፈሩ፣
በገባቸው ልክ ያርዱ፣ በክሳቸው ያሸብሩ፣
ቀለም አይዝለቃቸው፣ በድንቁርና ይኑሩ።
 
ከጥፋት ውሃው ለመዳን፣ ኖህ መርከቡን ሲሰራ፣
አርባ ዓመት አለን ብሎ፥ ነበረ ህዝቡ ሚያሽላላ፤
 
ወትሮም የሰነፍ ሰው እቅድ፣ ስንፍናውን ነው ሚያጎላ፣
አለመስራቱን ነው ሚያሳይ፣ ነውሩን ገላልጦ ካውላላ፤
እንደተቀጡ ያኔ፣ የሃሰት ወሬ ሲነዙ፣ ከነዓንን ሰልለው፣
የገለሞተ በድን ላይ፣ ዛሬም እግዚአብሄር ፈራጅ ነው።
 
ስለ 1 ቀን 1 ዓመት፣ ስለ 40ው 40ዓመት መዝዞ፣
በድናቸውን ይጣለው፣ በምድረ በዳ አቅበዝብዞ።
 
☞ አሜን!! ለጊዜው የ”ተደማሪው” አብዲ ኢሌን መያዝ ሰምተናል። ፍርዱንም ፍትሃዊ ያድርግልን። ያቀላጥፍልን! ሌሎቹም እንዲሁ ወግ ወጉን ይዩ!
 
☞ በረከት ስምዖንም የዛሬ 4 ዓመት “የወደፊቱ የህዳሴ መንገድ” በሚል ርዕስ ለኢህአዴግ ካድሬዎች ባቀረቡት ጥናታዊ ጽሁፍ። “ኢህአዴግ ልማቱን ለመጨረስ ከ40 እስከ 45 አመት ያስፈልገዋል” ብሎ ነበር።
 
እንግዲህ 40/60ም ቤት የለኝም እያለ ነው፤ አርብ አምሳ እያለ ሲያዝገን የኖረው።
☞ ይልቅ፥ በመጽሐፍ ምረቃው ወቅት አላሙዲን “መጽሐፉን አላነበብኩትም ግን ለመጭው ትውልድ እንደሚጠቀም አምናለሁ” ሲሉ፥ “ሳያዩ የሚያምኑ ብፁሃን ናቸው” ብለን ተሳልቀን ነበር።
 
መቼም እስር ቤት ውስጥ ሰው ያነባልና ይኽኔ ጨርሰውት ይሆናል። በረከትም በርሳቸው አስተያየት ተበረታትቶ ይሆናል 2ኛውን መጽሐፍ ጀባ ያለን።
 
☞ ከጠፍጥፎ አዳሪነት
ወደ ጥፎ አዳሪነት ለመሸጋገርም የሚያበቃ ደግነት የለውምና፣ ፍትህ እንዲፈጸም እንናፍቃለን!
 
እስከዚያው ግን፣ እርስበርስ ለመማር እና በርትዕው ለመጓዝ ከበቂ በላይ ትምህርት እየቀሰምን ነው ያለነውና ትንሽ ጆሮ እና ልቡና ይስጠን።
ያው ኢህአዴግ እነተባለለት 50 ዓመት ፖዚሽን እየቀያየረ ያጫውተን ይሆንን? እስኪ አብረን እንከታተል!
 
ትምህርቱስ ሙሉ ነበር
የሚማረው ሰው ቢኖር!

One thought on “መለስ፣ በረከት፣ አብዲ ኢሌ፣ ደመቀ መኮንን፣ ሼኽ አላሙዲን፣ ጭብጨባው፣ የዛሬ ደማሪ ተደማሪው፣ የትናንት አጋፋሪው ሁሉ፣ ኢህአዴግ ወዘተረፈ…”

  1. ኧረ ህዝብ ሊያነበው ይገባል።መንገድ ፈልግለት ኣብዛኛው እንዲደርስ ።social network እን እእንደሆነ እነስዩም ተሾመ አጣበውታል።

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s