
– መንግስት ከሕዝብ የሚሰበስበውን ግብር ገንዘብ አወጣጥ በተመለከተ ግልጽ የሆነ አሰራር መዘርጋቱን አስታወቀ። በዚህም መሰረት በመንግስት ጥሪ ተደርጎላቸው አገር ውስጥ ገብተው ለነበሩ የተቃዋሚ ፓርቲዎች እና ግለሰቦች ይደረግ የነበረው የእለት እና የማረፊያ ወጪ እንዲቋረጥ እና፣ ግለሰቦቹ/ቡድኖቹ ራሳቸውን እንዲያስተዳድሩ ተወሰነ።
– ዘር እና ጎጥን መሰረት አድርገው ፓሪዎች እንዳይመሰረቱ፣ ጥብቅ አዋጅ ተላለፈ።
– ተቃዋሚ ፓርቲዎች መከባበር የተሞላበት ውይይት አደረጉ። ፓርቲዎቹ በየልሳኖቻቸው ያደረጓቸው ውይይቶች እና ክርክሮችም፣ ፍጹም መከባበር እና ለአገር በሚጠቅም መልኩ መተጋገዝ የታየባቸው ነበሩ።
– አድማጭ ተመልካቾቻቸውን ለማስፋት እና ስርጭቶቻቸውን በሰፊው ለማዳረስ በጋራ በነደፉት እቅድ መሰረት፣ ኦኤምኤን እና ኢሳት የ30 ደቂቃ የዜና ሽፋን ሰዓት በቅይይር ተሰጣጡ። በወቅቱ ሚዲያ ከሚዲያ ጋር ተደጋግፎ፣ ሀሳብን የመግለጽ መብትን ለማስረጽ መስራት እንደሚያስፈልግ ተገለጸ።
– አገሪቱ ላይ ባለው የመልካም አስተዳደር ጉድለት እና ፖለቲካዊ እና ወገናዊ ጥቅመኝነት የተቆጡ የአዲስ አበባ ወጣቶች መስቀል አደባባይ ፍጹም ሰላማዊ የሆነ የተቃውሞ ሰልፍ አድርገው፣ እስር እና ወከባ ሳይገጥማቸው በሰላም ወደየቤታቸው ተመለሱ። ፖሊስም ለሰልፉ በሰላም መጠናቀቅ ከፍተኛ ጥበቃ አድርጎ ሕዝባዊነቱን አስመስክሯል።
– አገሪቱ ውስጥ እየመጣ ባለው ለውጥ አማካኝነት 3 እስር ቤቶች ተዘግተው ረዳት የሌላቸው አረጋውያን መቆያ ተደረጉ።
– በስልጣን ዘመናቸው የሕዝብን ሀብት በመበዝበዝ እና ሰዎች ላይ ኢሰብአዊ ጥቃት በማስፈጸም የተሳተፉ ሰዎች በቁጥጥር ስር ውለው በወንጀለኛ መቅጫ ህጉ መሰረት ቅጣት የተበየነባቸው ሲሆን፣ በወቅቱ ያፈሩት ሀብትም ተወርሶ ለሕዝብ ጥቅም ገቢ ሆኗል።
– ሰዎች ሀሳባቸውን ያለገደብ መግለጽ በነበራቸው ፍላጎት የተነሳ፣ በየማህበራዊ ድረ ገጹ ፌስቡክ ላይ የነበረው ትርምስ እና መሰዳደብ በመጥፋቱ፣ ወጣቶች ሀሳብን መሰረት ያደረገ ውይይት ላይ እንዲያተኩሩ እንዳገዛቸው ተናገሩ።
– ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉት ሁለቱ ብቸኛ ፓርቲዎች በቀጣዩ ምርጫ ላይ ከፍተኛ ፉክክር ያደርጋሉ። ከወዲሁ የምረጡኝ ቅስቀሳቸውን የጀመሩ ሲሆን፣ ምርጫ ቦርድም ለነጻ እና ገለልተኛ ምርጫ ዝግጅቱን ጨርሶ እየጠበቀ ነው።
– ጾታዊ ጥቃት እና ትንኮሳ የፈጸሙ ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ውለው ለተጠቂዎቹ ፍትህ በመሆኑ ደስታ የተሰማቸው ሰዎች ገለጹ።
– ኢትዮጵያ ውስጥ በተፈጠረው የስራ እድል እና ሞያን መሰረት ያደረገ ውድድር መሰረት ወደውጭ የሚሰደዱ ምሁራን ቁጥር ቀነሰ። ውጪ የሚገኙ ምሁራንም ወደ አገር ተመልሰው የተለያዩ የስራ መስኮች ላይ እየተሰማሩ ነው።
– ህብረት ለእድገት በተባለ የወጣቶች ማህበር ውስጥ ወጣቶች በተለያዩ የበጎ አድራጎት ስራዎች ላይ ተሰማርተው አስተሳሰብን የመቀየር ስራዎችን እየሰሩ ነው። በተለይም አገሪቱ ላይ ለረጅም ዓመታት ተንሰራፍቶ የቆየውን የት/ት እጥረት ለመቅረፍ፣ በክረምት እና በእረፍት ቀናቸው የማስተማር ስራዎችን ያከናውናሉ።
ወዳጄ ጋዜጠኛ ሀብታሙ ስዩም በጋበዘኝ መሰረት፥ የምናፍቀውን ዜና በስስ፣ ድፍርሱ እንዲህ አስፍሬያለሁ። እስኪ ደግሞ የምትናፍቃቸውን ዜናዎች እንድታጋራን ወዳጄ Emebet Lakewን ልጋብዝ።
Join the #mydreamnews campaign