ችግር ወልዶ ያሳደገውን ፍቅር፣ ማግኘት ይቀብረዋል!

46765716_1937122056408818_3712700478056824832_n

ችግር ወልዶ ያሳደገውን ፍቅር፣ ማግኘት ይቀብረዋል!
በአንድ ትሪ ማቅረብ ያመጣው ችግር ቢሆንም (ሲመስለኝ)፥ ለልጆች መተሳሰብን፣ አንተ ብስ አንቺ መባባልን አስተምሯል። ሁሉም ሰው ታጥቦ እስኪሰየም ድረስ እንጠባበቃለን።
ከአንዱ ቦታ እንጀራው ሲሳሳ፣ ከአንዱ ቆርሰን እናሳልፋለን። “አንቺ ብዪ፣ አንተ ብላ እንባባላለን። “ይኸው የኔን አታይም? ጥርግ አድርጌ በልቼ እኮ ትሪው ታየ። አንቺ አልበላሽም።” መባባሉ፣ ጨዋታው ሁሉ የሚገነባ ነገር ነበረው።
በአንድ ትሪ ሲበሉ ሁሉም ነገረ ስራው እንደእናት ይኾናል። ማቀራረቡም የጋራ ርብርብ አለውና መተጋገዝን ያጠናክራል።
በአንድ ትሪ በሚቀርብበት ዘበን፥ “ቤት ራት ይጠብቁኛል” ብሎ መሯሯጡም ነበር።
ማባያው ወጡ እንዲብቃቃ፣ ሌላውን ሰው ከግምት አስገብተን እንመገባለን እንጂ ጣፈጠኝ ብሎ መስገብገብ የለም። ሽሚያው ሲጀመርም በጋራ ነው። ከተሻማው ላይ ከአፉ ነጥቆ የሚያጎርስም አለ።
ደግሞ የተጎዳ የመሰለንን ጠቅልለን እናጎርሳለን። እየበሉ ሰው ሲገባም፣ “በሞቴ አንዴ ላጉርስህ” ይባልና ተጠቅልሎ ይላክለታል። ደግሞ “አንድ ያጣላል” ይባላል። “ኸረ በዛ” ቢል “ፍቅርና ጉርሻ ሲያስጨንቅ ነው” ይባላል።
መጎራረስን የወለደው ግን ማጣት፣ ወይም “አልጠገበም ይሆናል” የሚል ልባዊ ስስት ነበር። በትሪ ማቅረብን ያመጣውም የሳህን እጥረት ወይ ደግሞ የማጠብ ስንፍና ነበር። እንጂማ አሁን የት ይጠፋ ነበር?
ማጣት እየተቀረፈ፣ አንጻራዊ ማግኘት ሲመጣ፥ ትሪው ቀርቶ የቁርስ ሳህን መግዛት፤ እንጀራ መቁረጥ መጣ። ሁሉም የየራሱን ይበላል። ሁሉም የየራሱ ላይ ይደፋል።
ከፊት ለፊት እንጀራ ቆርሶ ማሻገር የለ። መጎራረስ የለ። እንግዳ ቢገባም “አቅርቡለት” ይባላል። “አንድ ቁርጥ እንኳን ያዝ እባክህ” ይባላል።
ታዲያ ሕይወት ካለትሪ አይሰለችም?
ይኽን የምዘበዝበው አብረን፣ አተራምሰን የበላን ወዳጆቼ ናፍቀውኝ ነው። ትሪ የተካበብኩባቸው ብዙ ወዳጆች ያሉኝ ዘመደ ብዙ ነኝ። የብዙ ሰው ጉርሻ ያሳደገኝ ነኝ።
በተለይ “የምስጋና ቀን” ላይ፣ ነጭ ከጥቁር ተሰባስቦ በአንድ ገበታ ቀርቦ በመተሳሰብ በሚመገብበት፣ ዘመድ በሚጠይቅበት፣ አቅመ ደካማውን በስጦታ እጅ በሚነሳበት ወቅት ወዳጅ ዘመድ ይናፍቃል።
ስንቱን ነገር ስንቀዳ የምስጋና ቀንን ያለመቅዳታችን ነገር ግን ይገርመኛል። ነው ወይስ ለጎጂ ቀረብ ካለው ጋር እንቀራረብ ሆኖ ነው?
ለማንኛውም መልካም ሰንበት!
ብትችሉስ በትሪ አቅርቡ! 😉
ፎቶ፡ ከፌስቡክ መንደር የተገኘ!