ያልተዘመረላቸው የኑሮ ወታደሮች

48422130_1979307308856959_8456443323358380032_n.jpgየተረሱ፣ የተዘነጉ ወታደሮች…. ያልተዘመረላቸው የሕይወት ጀግኖች፣ ከኑሮ ጋ ትንቅንቅ ገጥመው በየበረሀው የቀሩ፣ እና በየአረብ አገራቱ የሚንከራተቱ እህት ወንድሞች አሉ።
 
የእናታቸውን ነጠላ ለመቀየር የተለሙ፣ የመሶቧን ልምላሜ ለማስጠበቅ የተመሙ፣ የቤታቸውን ዳር ድንበር ለማስከበር ልጅነታቸውን የገበሩ ብዙ ወጥቶ አደር ወገኖች አሉ።
የቤተሰባቸውን የውሃ ጥም የመቁረጥ ህልም ሰንቀው ወጥተው በውሃ ተበልተው የቀሩ፤ ድህነትን ዐይኑን ለማጥፋት ሲጓጉ፣ በአረብ ዐይናቸው የጠፋ፤ ችግርን ድል ለመንሳት ሲፋለሙ ቀን የደፋቸው፣ እናታቸውን ቀና ለማድረግ ሲፍጨረጨሩ ተሰብረው የቀሩ ምስኪኖች…
 
ከኑሮ ፍላጻ ጋር ሽል ሽል እየተባባሉ የሚራኮቱ፣ ሕይወት ሰንኮፉን ሲያራግፍባቸው፣ ህመሙን ዋጥ አድርገው ጸንተው የሚቆሙ ነፍሶች ብዙ ናቸው።
 
የቤተሰባቸውን ህልውና እና የኑሯቸውን ሉአላዊነት፣ የቤተሰቡን የሆድ ዳር ድንበር ለማስጠበቅ የደከሙ፣ ከኑሮ ጋር ሲታገሉ የተረቱ እና ፀንቶ ለመቆም የሚንገዳገዱ በርካቶች አሉ።
 
በድል ተሯሩጠው መጥተው ሰንደቁን ሰቅለው፣ ከእናታቸው እግር ስር ተደፍተው ምርቃቱን ለመቀበል እና እሳት እየሞቁ ጸጉራቸውን ለመዳበስ እንደናፈቁ…. እናት አስከሬን እንዲላክላት የምትለምንላቸው ኢትዮጵያውያን ሞልተዋል።
 
የድሀ አገር ከርታቶች ሆነው ተፈጥረው፥ ኑሮ ሽምቅ እየተኮሰባቸው፣ ቁልቁል እያሳደዳቸው፣ ጥርሱን አውጥቶ ሊቀረጥፋቸው ሲታገል በእጃቸው መንጋጋውን ወደላይ ሰልቀው ይዘው የሞት የሽረት የቆሙ ከርታታ እህቶች በየአረብ አገራቱ አሉ።
 
የአናብስቱን አፍ በእምነታቸው አዘግተው፣ የአዞዎቹን መንጋጋ በእልህ ፈልቅቀው ይዘው የሚንቧቸሩ ምስኪኖች፤ የመርከብ ነጂው በባህር አውሬ የታጀበ ማዕበል ሲያስቸግረው ማስታገሻ ብሎ አንድ አምስቱን ቆንጥሮ ወርውሯቸው የቀሩ፤ ተርፈው አረብ አገር ገብተው የሚኖሩ፤ ደርሰው የተጉላሉ ብዙሀን….
 
ቤታቸው ውስጥ በቀን ሶስቴ የመብላት ተስፋን ለማስከበር ቆርጠው የተነሱ፣ ታናናሾቻቸውን ለማስተማር የሚንደፋደፉ የልማት አርበኞች፣ የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጆች፣ አረንጓዴ ስደተኞች በየአረብ አገሩ አሉ።
 
እናታቸው ለልመና እንዳትወጣ ሙግት ገጥመው፣ ከአገር ወጥተው ለጥቃት የዋሉ፤ ከኑሮ ጋር ግብግብ፣ ግንባር ገጥመው የሚራኮቱ፣ የሚታኮሱ፤ የሚናከሱ እና የሚቧጨሩ ታታሪ እህቶች አሉ።
 
ኑሮ ያቆሰላቸው፣ ኑሮ ያሳበዳቸው፣ ኑሮ ያሳደዳቸው ብዙሀን ወገኖች ሰብሳቢ አጥተው በየበረሀው ተበትነዋል። ዕድላቸውን ለመሞከር ወጥተው ቀርተዋል።
 
“ምን ይዤ ልመለስ” ብለው ለሁለት ዓመት ሄደው፣ ግራ እንደተጋቡ ከዚያ ብዙ የቆዩ አሉ። ፓስፖርታቸው በአሰሪ ተደብቆባቸው ወደ እናታቸው ቤት መመለስ የሎተሪ ያህል የማይተነበይ የሆነባቸው ሞልተዋል።
 
ያደለው የቤት ቀለም ማስቀየሪያ፣ ጤፍ ማስፈጫ ልኮ እናቱን ደግፎ፣ ልጅን ትምህርት ቤት ለመላክ፣ የኑሮ እሾህ ከበጣው እምቧይ ድህነቷ ላይ የሚፈሰውን እንባ በላቡ ጠግኖ፥ በናፍቆት እና በሰቀቀን እሾህ ተወግቶ የሚወርድ እንባ ተክቶላት፣ በአንጻራዊነት ቀና ብሎ ያልፋል። ግማሹ ባፈቀረው ወዳጁ የሰበሰበው ብር ሁሉ ተበልቶበት ሌላ ጎጆ ቀልሰው ይኖሩበታል። ያልታደለው ደግሞ በወጣበት ይቀራል።
 
ጉዳይ ተደራረተብን እና የሚያስበውም የለ እንጂ፥ “የስደተኛ እናት ታጠቂ በገመድ…” ተብሎ መዘፈን ነበረበት።
 
በዚህ ሁሉ መሀል የሚያጽናናው ግን እርስበርስ በጣም ደጎች ናቸው። የብዙ አገር ስደተኛ ሰው አይቻለሁ። የአረብ አገራት ስደተኞችን ያህል እርስበርሱ የሚደጋገፍ፣ ለቁስ ግድ የሌለው፣ ሰው አፍቃሪ አይቼ አልውቅም። ኑሮም ያደቀቃቸው፣ ድህነት የደቆሳቸው ታታሪዎች ናቸውና ርህራሄ ሞልቶባቸዋል።
 
ነግ በእኔም አያጣውም፥ ሲንፈሰፈሰፉ እንደእናታቸው ነው። ዘር ሳይመራረጡ ነው የሚጠያየቁት። ዘር ሳይቆጣጠሩ ነው ጥቁር ለብሰው ፊታቸውን እየቧጠጡ የወዳጃቸውን ሀዘን የሚቀመጡት። ከየት ናት ሳይሉ ነው ያላቸውን አዋጥተው ለሟቾች እናት ለመላክ ተፍ ተፍ የሚሉት። አንጀት ይበላሉ!
 
ይህን የማወራው አንዷ ወጥቷደር ዘመዳችን የመሞቷን ነገር ከሰሞኑ ስለሰማሁ ነው።
 
ምስኪን፣ ቀና ብላ ሰው የማታይ፣ ታጋይ… የድካሟን ያህል ያልሆነላት፣ የገጠር ድህነት ያድቀቃትና ካለአባት ጥንቅቅ አድርጋ ያሳደገቻቸውን እናቷን ለመጠገን ወጥታ የቀረች ከርታታ ወታደር ነበረች።
 
አይቻለሁ! ኑሮ ሺህ ጊዜ ቢዘርራት፣ ሺህ ጊዜ ተንገዳግዳ ቆማ መክታዋለች። ታግላ ፀንታ ቆማ በጸሎት ስቃበታለች። ጠብ ባይልላትም፣ ከትግል እና ጥረት ቆማ አታውቅም። አገር ውስጥ የምትችለውን ነገር ሁሉ ሞክራለች። ግን አንዱም ምንም አላመጣላት።
 
እናቷን፥ እናት አገሯን ደግሞ በጣም ነው የምትወዳት። እናቴ እናቴ ስትል ውላ ነው የምታድረው። መቼም ሁሉም ሰው እናቱን ይወዳል። የሷ ይለያል፤ ለአንድ ቀን እንኳን የሚያውቋት ሁሉ የሚመሰክረው ሀቅ ነው። እናቴ እናቴ እንዳለች፣ የእናቷን ነጠላ ለመቀየር ጎኗን ለማሳረፍ እንደናፈቀች፣ ከእነእድፏ ከነጉጉቷ ከነናፍቆቷ ከነስስቷ ትታት ሄደች።
 
ከዚህ ቀደም ቤሩት ሄዳ ለፍታ፣ ታግላ፣ ደክማ ምንም ሳይሰጧት ነበር የተመለሰችው። የአንዳንድ ሰው እድል እንዲህ ነው።
 
አንዴ እኛ ቤት ለእንግድነት በነበረችበት ጊዜ፣ እህቴን “ፀጉሬን ስሪኝ” ትላታለች። እህቴ ስትሰራት ጭንቅላቷ ላይ ትልቅ ስፌት አይታ ጮኻ ትጠራኛለች።
 
“ምንድን ነው ይሄ?” እኔንም እሷንም ትጠይቀናለች።
 
“አይ እሙ ትንሽ ነው እኮ። ኸረ ትንሽ ነው” ትላታለች። ወታደር ህመሙን ቻል አርጎ ነው የሚታገለው።
 
“ምን ትንሽ ነው ትይኛለሽ እንዲህ ተሰንጥቆ የተሰፋን ቁስል? ታክመሻል?”
 
“አይ ተስፋ በዛው ቀረ”
 
“እንዴት አትታከሚም?”
 
“ኽረ ትንሽ ነው እሙ”……
 
ይህ በሆነ በጥቂት ወራት ውስጥ ነው ተመልሳ ለመሄድ ጉድጉድ ማለቷ የተሰማው።
“ተዪ” ተብላ ብትለመን ብትሰራ፣ አንዴ ልቧ ተነስቷልና “ሞቼ ልገኝ። አንድ እድሌን ሞክሬ እናቴን ቀና ላድርጋት” አለች።
 
“ኸረ ተይ እዚህ እንደሆንሽው ሁኚ። እናትሽ ያንቺን ደህንነት ነው የምትፈልገው።” ብትባል
 
“በፊትም እንደሰው የሰራሁበትን አልሰጡኝም እንጂ ቢሰጡኝ ኖሮ እኮ ጥሩ ነበር ያገኘሁት። ህጋዊ ስለሆነ እድሌን ልሞክር። አሁን ይሰጡኛል። እግዚአብሔር ያውቃል። ፀልዩልኝ።”
 
ብላ በህጋዊ መንገድ በጀመረችው ፕሮሰስ ተነስታ ቤሩት ገባች።
 
አራት ዓመት ከምናምን ቆየች።
 
ከርሞ ከራርሞ ታማ አልጋ ስትይዝ እንደተሰማው፥ አሰሪዎቿ ፍራንኳን አይሰጧትም።
ለማመን ቢቸግርም፥ በአራት ዓመት ከምናምን ውስጥ አስራ ሁለት ሺህ አምስት መቶ ብር ብቻ ነው የላከችው። ያ ደግሞ ለመሄድ የተበደረችውንም ኮርቶ አይከፍልም ነበር።
“አበድሩኝና ለእናቴ ስጡልኝ” ብላ ሁላ ታውቃለች። እስትንፋሷ የተያያዘው ከእናቷ ጋ ነው። ሌላ ምንም ዓለም የላትም። እሷን ብሎ የሚመጣ ሰው የለም። ከራሷ ጋ ተማምላ የእናቷን ኑሮ ለመለወጥ ተፍ ተፍ የምትል፣ ባተሌ የኑሮ ወታደር ነበረች።
 
ቤተክርስቲያን አታጓድልም። ሄዳ ጸልያ ተለማምና ትመጣለች።
 
አረብ አገርም ሆና “ፀልዩልኝ” እና “እናቴን አደራ” ነው የምትለው። ሌላ ንግግር የላትም።
ስትኖር ስትኖር የዛሬ ሁለት ወር ገደማ ሆስፒታል ገባች አሉ። አሰሪዎቿ ሆስፒታል ወርውረዋት በዛው ጠፉ።
 
ህጋዊ ስለሆነች ኢንሹራንስም ያስገድዳቸዋልና የህክምናዋን ይከፍላሉ ተብሎ ተጠብቆ ነበር። ግን ደህና ቆንጽላ የለንም። አስከሬን እንጂ ሰው ከነነፍሱ አገሩ እንዲገባ የሚያደርግ ቆንጽላ የለንም። ከአገር ውስጥ የሰዉን ሀብት መዝብረው፣ በጭቆና እና በድህነት ረግጠው ያባረሩትን ሲሞት ይመልሱታል።
 
ደወለች የሆነ ቀን “ሁለቱም ኩላሊቴ ከጥቅም ውጪ ሳይሆን አይቀርም” አለች
ህመማቸውንም በቀጥታ ለእነሱ አይነግሯቸውም። ስለዚህ ከሰሞኑ ያለውን በሽታ ስም ይዘው ነው የሚቀጥሉት አሉ። በሰው በሰው ሲጣራ፥ ኤምባሲው “ህመሟ ጉበት ነው” አለ። በደህና ሁኔታ በሕያወት እያለች፣ የሚደረገው ተደርጎ አገር ቤት እንድትገባ እና እናቷን እንድታያት ተሞክሮ፣ ኤምባሲው ሄዶም ለማየት ፈቃደኛ ባለመሆኑ፥ ማቅቃ ማቅቃ ሞተች። በወጣችበት ቀረች።
 
ልጄ ትመጣለች ብላ ደጅ ደጁን የምታይ ምስኪን እናት አለች። ምን ተብሎ እንዴት ተብሎ ይነገራታል? ማን ደፍሮ የወታደር ልጇን ሞት ያረዳታል? ወታደሯ ልጅሽ ላንቺ ስትሟገት፣ አንቺን ሉዋላዊ እናት ለማድረግ ስትታገል ሞተች። ተረታች። የባለጌ ጥይት አረፈባት። ተብሎ እንዴት ይነገራታል?
 
እንደምንም! አዎ እንደምንም ተነገራት።
 
ግን “አስከሬኗን ካላየሁ አላምንም። እሷ አልሞተችም። አስከሬኗ ካልመጣ አልሞተችም። አንድ ቀን ትመጣለች።” አለች አሉ።
 
ለይስሙላ የተሰየመው ቆንጽላው ደግሞ የተካነበትን አስከሬን የመላክ ሚናም የተወው ይመስላል።
 
በጣም አስቀያሚ በሆነ ገጠመኝ ደግሞ፥ በአንድ ቀን የተረዳችው የሁለት ልጆቿን ሞት ነው። እሷ አረብ አገር በሞተች በሶስተኛው ቀን፣ ታናሽ ወንድሟ አዲስ አበባ ውስጥ ተከራይቶ ይኖር ከነበረበት ቤት ደጃፍ ላይ ተገድሎ ተገኘ አሉ።
 
እሱም የኑሮ ወታደር ነበር። እናቱን ሊጠግን የከተማ መብራት ተከትሎ አዲስ አበባ ውስጥ የከተመ ታታሪ ምስኪን! እሱን እናት ቀብራዋለች እና አምና ህመሟን ዋጥ አድርጋለች። የአረብ አገሯ ግን አስከሬኗ ካልመጣ አላምንም ብላለች። የትኛው ደህና ቆንጽላ ነው የሚደርስላት?
 
ነፍስ ይማር!

የጉዞ ነገር…

images.jpgሁሉም የአፍሪካ አገራት ነዋሪዎች ወደኢትዮጵያ ለመግባት፣ በደረሱ ጊዜ ቪዛ ማግኘት የሚችሉበት አሠራር፣ ከኖቬምበር 10 ይጀምራል ተብሎ ነበር። (እንዴት ሆነ እንኳን “እንኳንስ ዘንቦብሽ እንዲሁም ጤዛ ነሽ” ይላሉ። የደህንነት ሁኔታው እንዲህ በሆነበት ጊዜ ጣጣው ብዙ ነው።
 
እሱን ባሉ በ20 ስንተኛ ቀኑ፥ አሁን ደግሞ ፓስፖርት ለማውጣት ቁም ስቅል ሆኗል ተብሏል። ወዳጆች ነገሩን ሲያወሩት ይኽን ያህል የተጋነነ ችግር አልመሰለኝም ነበር። ሰው እንዴት ፓስፖርት ለማውጣት መከራውን ያያል?
 
የሚሄድበት አገር ይጭነቀው እንጂ፣ እንዴት እና በምን ተለይቶ ይስተናገዳል?
 
ማን ነው አንቺ ቱሪስት ትመስያለሽ፣ አንቺ አትመስዪም ማለት የሚችለው?
 
በምንስ መስፈርት ነው?
 
ለምንስ እንደዚያ ይደረጋል?
 
በር ዘግቶ ስደት አስቀርተናል ለሚል ሪፖርት ነው?
 
ማንኛውም ሰው ከቦታ ቦታ የመንቀሳቀስ መብት አለው።
የሚሄድበት አገር አልቀበል ካላለው በስተቀርም፣ የፈለገበት ቦታ ሄዶ የመስራት እና የመኖር መብት አለው።
 
መብት የሆነውን ነፍገው፥ ምን ሸፍጥ እንዳሰቡ እንጃ… በጎን ለጎዳና ተዳዳሪዎች እና ለረጅም ጊዜ አዲስ አበባ ውስጥ ለኖሩ ሰዎች ጊዜያዊ መታወቂያ እንሰጣለን ይላሉ። ለምን አስፈለገ?
 
በዚህ በግርግር የቀበሌ ቤቶች ከድሃ ተነጥቀው ለባለጊዜ እየተሰጡ ነው ተብሎ በሚወራበት እና ምርጫና፣ ሕዝብ እና ቤት ቆጠራ በደረሰበት ጊዜ መታወቂያ መስጠቱ ለምን አስፈለገ?
 
መታወቂያው ቀርቶ ፓስፖርት ይሰጣቸውና እንደኢዮጵያዊ ይቆጠሩ።
 
#የጉድአገር