ከአዋላጅ ነርስ ወዳጄ ጋር ገጠመኝ

ጊዜ ሳገኝ ስለህክምና ባለሞያዎች የማስታውሰውን እጽፋለሁ ባልኩት መሰረት፥
 
ጎሮ የሚባል ጤና ጣቢያ ስር ያሉ የጤና ኬላዎች (health posts) የCHIS (community health information system) የሥራ ላይ ስልጠና ለመስጠት ከአንዲት አዋላጅ ነርስ የስራ ባልደረባዬ ጋር እንሄድ ነበር።
 
ነገሩ፥ የትራንስፖርት ችግርም ስለሚኖርብን በአንድ ድንጋይ ብዙ ወፍ ለመግደል ተሰብስበን ነበር የምንሄደው። እዚያ ደርሰን ሁላችንም በየሚናችን እንሰማራለን።
 
የዚያን ቀን ግን ጤና ኬላው አንዲት ነፍሰጡር እናት ምጥ ላይ ሆና፣ የጤና ኤክስቴንሽኖቹም ሊረዷት እየሞከሩ ግራ ተጋብተው ሲጯጯሁ ነበር የደረስነው። እርግዝናው ከመደበኛው ትንሽ የተወሳሰበ (complicated) ነገር ነበረው።
 
“ለምን አምቡላንስ አልጠራችሁም ቀድማችሁ?” ብላ ጮኸች ባልደረባዬ
 
“ከትናንት ማታ ጀምሮ ስንሞክር ስልክ እምቢ ብሎን ነው። በትራንስፖርት ልንወስዳትም ብለን አልቻልንም።” አለች የጤና ኤክስቴንሽኗ በጭንቀት በሚቆራረጥ ድምጽ።
 
ባልደረባዬ ቀጥታ ወደ ስራው ገብታ
 
“በይ ቶሎ ጓንት አምጪልኝ፤ እናንተስ ቆማችሁ እያያችኋት ነው እንዴ ምትረዷት?” አለች
 
“ጓንት እኮ አልቆብናል። በስልክ እነግርሻለሁ ብዬ ኔትዎርክ እምቢ ስላለኝ ነው። ግራ ሲገባን ስስ ፌስታል ገዝተን ነበር፤ ፌስታል አለ።” ብላ ሁለት አዳዲስ ፌስታሎች ነጥላ ሰጠቻት።
 
(እንግዲህ አልቋል የተባለውንም ጓንት መንግስት አይደለም የሚልክላቸው። እኔ እሰራ የነበረበት መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት ነበር። አምቡላንሱንም የገዛው የእኛው መ/ቤት ነበር።)
 
ፌስታሉን እጆቿ ውስጥ አጥልቃ፣ “እሰርልኝ” አለችኝ።
 
ነገሩ ትንሽ ይጨንቅ ስለነበር አስተያየትም ሳልሰጥ የደመነፍሴን አሰርኩላትና፣ “በሉ ፀልዩ ሂዱ” ብላ ከጤና ኤክስቴንሽን ሰራተኛዋ ጋር ገብታ፣ ከብዙ ከፍ ዝቅ፣ ፀሎት እና ጩኸት በኋላ በሰላም አዋለደቻት።
 
ስትመለስ ድካም፣ እርካታ፣ መሰልቸት፣ ብዙ ነገር ነበር ፊቷ ላይ።
 
እየተመለስን “ትቀልጂያለሽ እንዴ? እንዴት እንዲህ ይሆናል? ካለጓንት እንዴት ታዋልጃለሽ? ፌስታሉስ ግን ያመቻል?” አልኳት
 
ግራ የገባው የእንትን የማይባል ሳቅ ስቃ (የፌስታሉን ነገር ማንሳቴ መሰለኝ ያሳቃት)፥
 
“ምን ላርግ? የኖርንበት ችግር ነው። ትዝ የሚልህ ራሱ መሀል ላይ ነው። ቀድሞስ ትዝ ቢልህ ምን ታመጣለህ? እንኳን እኔ አዋላጇ፣ አንተስ ብትሆን በእንዲህ ሁኔታ ላይ ሆና አግኝተሃት በማታውቀውም ገብተህ ቢሆን ለመርዳት አትሞክርም ነበር? ሕይወትህን አደጋ ላይ ጥለህ ነው የሰው ሕይወት ለማዳን ምትጥረው።”
 
እሷ ረሳችው። የሁልጊዜ ገጠመኟ፣ እንጀራዋ ነውና ብዙም አይደንቃትም ይሆናል። እኔ ግን እዚያ በሄድኩ ቁጥር የማልረሳው ገጠመኜ ነበር። ካለማጋነን ንግግራችንን ቃል በቃል የማስታወስ ያህል አእምሮዬ ላይ ታትሞ ቀርቷል።
 
አስታውሼ ስጽፈውም ትዝ እያለኝ ዘግንኖኛል። ምናልባት ይኽን ሲያነብ የሚዘገንነውም ይኖራል።
 
ለእሷ ግን ሕይወቷ ነው። የአርበኝነት ሕይወቷ። ራሷን አደጋ ላይ ጣል፣ ሌላን የመርዳት፣ የማዳን፣ የማዋለድ ሥራ።

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s