በሬ ተንኳኳ።
የከፈትኩትን ሙዚቃ አስቁሜ፣ “ማነው?” እያልኩ ተነሳሁ፣ ከሩምሜቶቼ (ክፍል ተጋሪዎቼ) ውጭ ሌላ ማንም እንደማይሆን ልቤ እያወቀው።
አዲሱ ክፍል ተጋሪዬ ዴቪድ ነው። ጠርሙስ እና ሲኒ ይዞ፣ ፈገግታ ተሞልቶ “ሰላም” አለኝ።
“ሰላም ዴቪድ። እንዴት ዋልክ?” አልኩት
በቀኝ እጁ የአረቄ ጠርሙስ፣ በግራ እጁ ሲኒ ይዞ እንደመቅዳት እያቀባበለ፥
“ምናልባት አረቄ ትፈልግ እንደው ብዬ ነው? ትወደዋለህ። አሪፍ የስፔይን ረም ነው።”
“ኦህ፥ መልካም ነህ። አልጠላም። ለነገሩ እኔም ወይን እየጠጣሁ ነበር።” ብዬው የቀዳልኝን አረቄ ተቀብዬው፣ አመስግኜ ገባሁ።
ሳልቀመጥ ተጎነጨሁለት። የምር አረቄ ነው። ቁንዱፍቱዬ። ጵጣ ጵጣ እያልኩ አንድ ሁለት ጊዜ ከተጎነጨሁለት በኋላ፣ ምናልባት ሰው ፈልጎ ይሆናል እኮ፥ ጠርቼው ወይኑን አብረን የማንጠጣው? የሚል ሀሳብ አደረብኝና ውጥቼ በተራዬ በሩን አንኳኳሁ።
“ሰላም ዴቪድ። ወይን አብረን እንድንጠጣ ትፈልግ እንደው ታች እየወረድኩ ነው፣ መምጣት ትችላለህ” ብዬው ወደ ሳሎን ሄድኩኝ።
ይሁንታውን ስለገለጸልኝ ሁለት ብርጭቆ አለቅልቄ ተሰየምኩ።
እጅ ነስቶ ተቀላቀለ። ከአፍታ ቆይታ በኋላ መጥቶ ቀዳሁለት እና አጋጭተን ተጎነጨን።
* * *
በ60ዎቹ መጀመሪያ የሚገመት ነጭ ነው። ደልደል ያለ ሰውነት፣ መልከ መልካም ገጽታ ያለው፣ መላጣ ነው። ፊቱ ላይ የሚታይ እርጋታ እና ብስለት አለ። ያለው ጥቁር ፀጉር የቅንድቡ ብቻ ነው።
የእኛን መኖሪያ ከተከራየ ገና ሳምንቱ ነው። ከ3 ቀናት በፊት እንዲሁ፣ ለምሳ ቤቴ ስገባ፥ “ሰላም ዮሐንስ፣ ቡና ትፈልግ እንደው አታፍላ። እኔ ያፈላሁት አለ።” ብሎኝ ሲያስደንቀኝ ነበር። ያልተለመደ ጸባይ ነው። የእናቴን ጓደኞች፣ የአገሬን አኗኗር ያስታውሰኛል።
እንደሚታየው ሰው ይወዳል። ሰው ይፈልጋል።
ቀድሞም ቡና አለ አታፍላ ሲል፣ የቀደመ ታሪኩን የማወቅ ፍላጎቴን ቀስቅሶት ነበር። የአረቄ ግብዥ ማንኳኳቱ ደግሞ ይበልጥ አባሰብኝና፣ ጥያቄዎችን አግተለትልለት ዘንድ ወሰወሰኝ።
“እሺ ባክህ። ብዙ ቆየህ እዚህ?”
“አዎ። ከአርባ አመታት በላይ።”
“ከየት ነህ?”
“ከስፔን ነኝ”
“አንተ ከየት ነህ?”
“ከኢትዮጵያ። ይገርማል። ብዙ ቆይተሃል። ብቻህን ነበርክ ይሄን ሁሉ ጊዜ?”
“ቤተሰብ መስርቻለሁ። ልጆች አሉኝ። ሁለት ልጆች አሉኝ። አንደኛው ልጄ እንደውም ኦሀዮ ዩኒቨርስቲ አሁን እየገባ ነው። እናቱ ናት ልታደርሰው አብራው የሄደችው። እዚያው ኦሀዮ ናት። ትልቋ ልጄ ሬዚደንሲ ላይ ናት።”
“ደስ ይላል። አብራችሁ አትኖሩም ማለት ነው?”
“ያው እንደምታየው እኔ ከእናንተ ጋር ነው ምኖረው ከዚህ በኋላ” ብሎ ሳቀ
“ይቅርታ ዴቪድ። ዝርዝሩን መጠየቄ ሳይሆን፣ ነገሩን እያሰብኩት ስለነበር ነው።”
“ገብቶኛል። አትጨነቅ። ሳምንት ሆነን ከተለያየን።”
“አዝናለሁ። በሰላም? ልትፈቱት የማትችሉት ጉዳይ ሆኖባችሁ ነው?”
“እንፈታዋለን። ግን ትንሽ የየራሳችንን ቦታ ፈልገናል መሰለኝ። እንደምንመለስ ተስፋ አደርጋለሁ።”
“እኔም አብራችሁ ትሆኑ ዘንድ ምኞቴ ነው። እርግጠኛ ነኝ በአጭር ጊዜ ወደቀደውም ሕይወትህ ተመለሳለሕ”
“አመሰግናለሁ። ጥሩ ሰው ነሕ። እኔም ተስፋ አደርጋለሁ።”
እንዲህ እየተባለ ብዙ ነገሮች ስናነሳ ስንጥል፣ ስንጎነጭ አመሸን።
ያልለመድኩት፣ ያልጠበኩት ዓይነት ሰው ነው። የኑሮን ብልሀት ያውቅበታል። ስለብዙ ነገሮች ተጨዋወትን። ብዙ ቦታዎችም ሊያሳየኝ ፍላጎት እንዳለው ነገረኝ።
አፀፋውን ለመመለስም ተቅበዝብዤ፥
“ዴቪድ፥ ምናልባት የምታወራው ሰው ትፈልግ እንደው በሬን ማንኳኳት ወይ ቴክስት ማድረግ ትችላለህ። ከሞቀ ቤት ስለወጣህ ሊከፋህ ይችላል። ግን አደራ፣ ብቻህን እንደሆንክ እንዳታስብ።” አልኩት
ደስታ ስሜታዊ አደረገው። “እንደዚህ መባል ነበር የናፈቀኝ። በጣም አመሰግናለሁ። አሁንም አሁንም እየመጣሁ አልረብሽህም። ግን አሁን ቢያንስ ሰው አለ፣ ብቻህን አይደለህም ስትለኝ ደስ አለኝ። እዚህ ስቆይ ያንን ስለማስብ እኔም ጥሩ እሆናለሁ፣ አንተንም አልረብሽህም”
“ኧረ ችግር የለም። እንደ ልጅህ ልታየኝ ትችላለህ። ምንም ዓይነት እርዳታ ስትፈልግ አለሁ። ባልረዳህ እንኳን፣ ቢያንስ አንተን ሳልፈርጅ እሰማሃለሁ።”
“ይሄ ከእርዳታ በላይ ነው ለእኔ። ሰው ትናንት ላይ ተቸንክሮ ይቀራል። አልረባም ይላል። እኔ በአንድ ጊዜ አንድ ቀን ለመኖር እየታገልኩ ነው የኖርኩት። አሁን ደግሞ ባላሰብኩት ጊዜ እዚህ መምጣት ነበረብኝ። ልትቆጣጠረው አትችልም። ቢያንስ ግን ርቄም ሰው እንዳለ ማወቄ ደስ ብሎኛል። ከባለቤቴ ጋር የምንታረቅ ይመስለኛል።”
“መች ነው ለመጨረሻ ጊዜ ያወራሃት?”
“አሁን ከ20 ደቂቃ በፊት፣ አንተ ሳትጠራኝ። የልጁን ዶርሚታሪ አልወደደችውም። እና ስለሱ እየነገረችኝ ነበር። በፊት አብሬ ላይ ታች እል ነበር። አሁን ብዙም ያንን የምትፈልግ አልመሰለኝም። ሃኒ፥ አይዞሽ፣ የምትፈልጊው ማድረግ የምችለው ነገር ካለ ንገሪኝ አልኳት”
“ሃኒ ትላታለህ አሁንም?” ተገርሜ ጠየኩኝ
“አሁንም እወዳታለሁ። ታወደኛለች። ልጆች አሉን። በህግ አልተለያየንም። አብረን ነን ማለት ነው። ያላስማማን ትዕቢት ነው። ኢጎ።”
“አብራችሁ እንደምትሆኑ ተስፋ አደርጋለሁ” ብዬ መልካም ምኞቴን ተመኝቼ ወደሌላ ጨዋታችን ቀጠልን።