“ሴቶች አስቂኝ ናቸው”

ከ2 ሩም ሜቶቼ ጋር፥ ፒንች ውስኪ በ3 ብርጭቆ ቀድተን አጋጭተን ተጎነጨን። ከጥቂት ቆይታ በኋላ አንደኛው ‘ኖርዝ ካሮላይና የሚሄድ ልጄን አውሮፕላን ማረፊያ አደርሳለሁና ልሂድ’ ብሎ ተሰናብቶን ወጣ። ሬሜ ይባላል። ስለእሱ ሌላ ቀን እንጫወታለን።
 
ከዴቪድ ጋር ለጥቂት አፍታ ዝም ተባብለን ስለሚስቱ ጠየቅኹት።
 
“ታውቃለህ ዮሐንስ፥ ሴቶች በጣም የሚያስቁ ፍጥረቶች ናቸው” ቀጥሎ ያለውን ለመስማት በመጓጓትም፣ በደምሳሳው የደመደመው እንደው ለመከላከል በመሻትም
 
“እንዴት?”
 
“ናቸዋ!”
 
“ቀላል ነው? እንዲህ ብለን ማጠቃለል እንችላለን ዴቪድ?”
 
“ታውቃለህ? በጣም ነው የሚያስቁት። አስቂኝ ፍጥረቶች ናቸው። የዛሬ 20 ወይ 25 ዓመት ያደረግኸውን ነገር በፈለጉት ጊዜ ያስታውሱታል። ከወሸቁበት ያወጡታል። መቼም ቢሆን ነገሮችን አይረሱም። ባልጠበቅኸው ጊዜ፣ ባላሰብኸው ሰዓት አሳቻ ቦታ ላይ አንተን ለማጥቃት ወይ አሸናፊ ለመሆን ይጠቀሙበታል።”
 
ከት ብዬ ሳቅኹኝ!
 
“ሳቅ! ጊዜው እስኪመጣልህ ሳቅ!” ብሎ አብሮኝ ሳቀ
 
“የምር ግን ነገሩ ስላልገባኝ ነው”
 
“ለምሳሌ እኔ የሆነ ጊዜ የሆነ ነገር እላለሁ። ለምሳሌ በጭቅጭቅ መሀል “ገደል ግቢ” እላታለሁ። ከ15 ዓመት በኋላ ‘በእንዲህ በእንዲህ ጊዜ፣ እንዲህ እንዲህ ስናወራ፣ እንዲህ ስል ገደል ግቢ ብለኸኝ ነበር። እህ?’ ትለኛለች። እኔ አላስታውሰውም። ዛሬ ብለኸው በመነጋውም ትዝ ላይልህ ይችላል። በዚህ በጣም ተናደህ ‘እና ምን ይጠበስ ያልኩ እንደው?’ ትላታለህ። ነገሩ ጭራሽ ይግላል…”
 
“ለሁሉም ሴቶች ላይሰራ ይችላል” አልኩኝ ነገሩን ለማስቀጠል እና ትንታኔውን ለመስማት በመጋበዝ
 
“ቀልዴን አይደለም። ሴቶችን ለማሳነስ ብዬ አይምሰልህ። በዚህ ዙሪያ ያለኝን ግንዛቤ እና ልምድ እነግርሃለሁ። እረዳቸዋለሁ። በአብዛኛው የራሳችን የወንዶቹ ችግር ነው፤ ግድ እናጣለን። ስለሚስቴ ወይ ቀድመው ስለነበሩ ሴቶች አይደለም ማወራው። ማነጻጸሪያዬም እነሱ ብቻ አይደሉም። ከእህቶቼ ጋር፣ ከእናቴ ጋር፣ ከአያቴ ጋር፣ ከሚስቴ እናት ጋር፣ ከአጎቶቼ/አክስቶቼ ልጆች ጋር ያወራሁበት እና ያየሁት ነገር ነው። 4 እህቶች አሉኝ። ሁሉም በዚህ ጉዳይ ይስማማሉ።”
 
“ይገርማል። ግን ለምን እንደዚህ ይሆናል?”
 
“በአብዛኛው ነገሮችን በግል እንደተደረገባቸው ነው የሚወስዱት (they take things personally)። እንዲህ ስልህ ሴቶችን ከወንዶች ላሳንስ ወይ ልክ አይደሉም ልል አይደለም። ግን ተፈጥሮአቸው ይመስለኛል። በርግጥ ስለሁሉም ሴቶች እያወራሁ አይደለም። ላወራም አልችልም። ግን ከጓደኞቼም ከቤተሰቦቼም ከስራ ባልደረቦቼም ጋር በተለያየ ጊዜ አውርተነዋል። ወንዶችም ሴቶችም እንስማማበታለን። ብዙ ምርምር አድርጌያለሁ። (ሳቀ)
 
እድሜህ ሲገፋ ከሴቶች ጋር ብዙ ግጭት ስታስተናግድ፣ ምንድን ነው ችግሩ ማለትህ አይቀርም። ዙሪያህን ስታጤን ይገባሃል። ችግሩንም ስታወሩ ማወቅህ አይቀርም። አንተ ብዙ ስላልኖርክ ብዙ ላይገጥምህ ይችላል። ከፍቅረኛህ ጋር ተጋብታችሁ 10 ወይ 20 ዓመት ስትኖሩ የምለው ይገባሃል። ለምን አሁን አትጠይቃትም? ትነግርሃለች። ደግሞ ሲወዱህ እና አንተ አሪፍ ስትሆን ድብቅ አይደሉም።
 
ዛሬ የምትላትን ሁሉ የምትመዘግብበት ቦታ አላት። አስባው አይመስለኝም። እንዲሁ ተፈጥሮዋ ነው። ታውቃለህ ሴቶች ከወንዶች የበለጠ ስሜት (feelings) አላቸው። መኖር ይፈልጋሉ። ቁም ነገር እንጂ ቀልድ አይፈልጉም። ያምኑሃል። በቁም ነገር ይሰሙሃል። ስለዚህ አይረሱትም።
 
አንተ በ30 ቀናት 30 ጊዜ ፋክ ዩ ትላለህ። ብርጭቆው ሲወድቅ፣ ቀጠሮ ሲረፍድብህ፣ ጓደኛህ ሲያስቀይምህ በተለያዩ አጋጣሚዎች ተናደህ ምታወጣው ቃል አለ። ጓደኞችህን ሃምሳ ጊዜ ትላቸዋለህ። ጉዳያቸውም አይደለም። ሚስትህን ግን ልትሸውዳት አትችልም። ለእሷ ያልክበትን አጋጣሚ አትረሳውም። በግጭታችሁም ጊዜ ሁሉ ወደ ኋላ የሆነ ዓመት ተጉዛ የሆነ ትውስታ ትመዛለች።”
 
አሁንም ከት ከት ብዬ ሳቅኹኝ።
 
“ሳቅ አንተ። አሁን ሳቅ።” ብሎኝ ሳቄን ተቀብሎኝ ቀጠለው።
 
አባባሉ አስቆኝ እንደገና ሳቅኹኝ።
 
“ምሳሌ ልንገርህ” ብሎ ቀጠለ። በሚያወራው ነገር ሁሉ ምሳሌ አያጣም። የእናቴን በነገር ሁሉ የሚነገሩ ተረቶች ያስታውሰኛል።
 
“አንዴ የሚስቴ እናት ጉዞ ነበራት እና አውሮፕላን ማረፊያ እንዳደርሳት ጠየቀችኝ። ለጉዞዋ መገኘት ያለባት ከሰዓት 8 ሰዐት ነው። ላደርሳት ከተስማማሁ በኋላ ከሰዓቱ እንዳላረፍድባት አስጠንቅቃ ነግራኛለች። እንደተቀጣጠርነው ከቀኑ 6 ሰዐት ተኩል ላይ ቤቷ ደረስኩ።
 
‘እንሂድ’ ስላት፥
 
‘ቆይ አንዴ፣ እንዲህ ተዝረክርኬ እንዴት እሄዳለሁ?’ ብላ መኳኳል መቀባባት ጀመረች (በእጁ ፊቱ ላይ አቀባቧን እያሳየኝ)
 
‘በቃ ምንም አትሆኚ እዚያ ስትደርሺ ሆቴልሽ ትስተካከያለሽ፣ ይረፍድብሻል’ ብላት
 
‘እምቢ አሻፈረኝ! እኔ ነኝ ተጓዧ አንተ?’ አለች። ሰዐቷን አይታ ችግር የለም እንደርሳለን አለችኝ።
 
በመከራ ሰባት ሰዐት ላይ ወጣች እና ጉዞ ጀመርን።
 
የባለቤቴ እናት በሁሉም ነገር ላይ አውቃለሁ ባይ ናት። ምንም ነገር ብታደርግ አስተያየት ትሰጥሃለች። ምንም ነገር!
 
እንደልማዷ ገና ስነሳ፥ “ኧረ ቀስ!” ብላ ጀምራ አነዳዴን መተቸት ጀመረች። በርግጥ ሰዐቷ እንዳይረፍድ ብዬ እየተዋከብኩ ነበር። ፈጥኜ ለመንዳት ሞክሬያለሁ።
 
መሀል ላይ ምንጭቅ ብላ ደጋግማ ቀስ እንድል ትነግረኛለች፤ ‘መድረስ አለብሽ በሰዐትሽ’ ብዬ ላስረዳት እሞክራለሁ። በጣም ጨንቆኛል ለእሷ።
 
እሷ ደግሞ ዘና ብላ ‘ገና ነው እንደርሳለን’ ትለኛለች።
 
መሀል ላይ ጭቅጭቋ ከአቅም በላይ ሆነብኝ። ካላስቆምኳት አደጋ ላይ ሁሉ ልትጥለኝ በምትችል መልኩ ትናገራለች።
 
ዳር አቁሜ ‘የእኔ እናት፥ ካልፈለግሽ ውረጂና ታክሲ ጠርተሽ ሂጂ።’ አልኳት።
 
አበደች። እንዴት ብትደፍረኝ አለች።
 
‘ነግሬሻለሁ ምርጫው ያንቺ ነው።’ አልኳት። የምር ተናድጄ ነበር።
 
አማራጭ ስለሌላት የግዷን ተሳፍራ አፏን ዘግታ ሄድን። ስንደርስ 20 ደቂቃ አርፍደናል። እድለኛ ሆና ግን አውሮፕላኑ አረፈደና ተሳፈረች።
 
ከዚያ ምን ቢሆን ጥሩ ነው? ከ10፣ ልክ ድፍን 10 ዓመት በኋላ የሆነ ክርክር ይዘን መሀል ላይ፥ ‘ግን ለምን ነበር ወደ ፈረንሳይ ስሄድ ከታክሲ ላይ እንዲያ ያበሻቀጥከኝ?’ አለች። (አብረን ሳቅን)
 
ምን አገናኘው? ምን ልበላት? እኔ ከዚያ ቀን በኋላ ትዝ ብሎኝም አያውቅም። ያልኩትን ብያት አብቅቷል። ያን ያለችው የተነሳውን ክርክር በባሌም በቦሌም ለማሸነፍ ስለፈለገች ነው። የሚስትህ እናት ስለሆንኩ፣ እንዲህ ስለሆነ፣ ያኔ ታክሲ ያዢ ስላልኸኝ ብላ ልታሸማቅቀኝ ስተፈልግ ነው።
 
አይገርምም? እንደዚህ ዓይነት ነገሮች ይገጥሙሃል። የፈለግኸውን ባለትዳር ጠይቅ ይነግሩሃል።”
 
ሳቅ ብዬ፥ “ይገርማል፤ ግን…” ስለው
 
“ሌላ ምሳሌ ልንገርህ፥ እናቴ እስክትሞት ድረስ ከአንድ ወንድሟ ጋር እስከዚህም ነበሩ። 20 ዓመታት ተደባብረው ነው ያሳለፉት።
 
ምክንያቱን ገምት! እናታቸው በጣም ውድ የሆኑ ዘርፍ ያላቸው፣ የእምፑል ማቀፊያዎች ነበሯት። እጅግ በጣም ውድ ነበሩ። እና ለእናቴ እንድትወስዳቸው ቃል ገብታላት ነበር። እናቴ ስትሞት ወንድሟ ልቡ እያወቀ በጉልበቱ ወሰዳቸው።
 
የእርሷ እንደሆነ ነግራው ልታስረዳው ሞክራ ነበር። ግን ብዙም ግድ ያለው ዓይነት አልነበረምና ዝም ብሏት ወሰደው። ተቀየመችው። ግንኙነታቸውም እስከዚህም ሆነ። እሱ ለምን እንደሆነ አያውቅም ነበር። አይገባውም።
 
ከ20 ዓመታት በኋላ እሱም በሰል ብሎ፣ እሷም ደከም ብላ ግድ ሲነጋገሩ አስታወሰችው። ፀፀቱ ሊገድለው ደረሰ። በጣም አዘነ።”
 
ነገሩንም ለማብሰልሰል እየሞከርኩ፥ ሳቅ ብዬ “ይገርማል! እና ከሚስትህም ጋር እንዲህ የድሮ ነገር እያስታወሰችብህ መግባባት እያቃታችሁ ነው?” ብዬ ጠየቅኹት
 
ይቀጥላል…
 
እውነት ነው ወይ? 🙂

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s