የቀጠለ… (ከዴቪድ ጋር)

ነገሩንም ለማብሰልሰል እየሞከርኩ፥ ሳቅ ብዬ “ይገርማል! እና ከሚስትህም ጋር እንዲህ የድሮ ነገር እያስታወሰችብህ፣ መግባባት እያቃታችሁ ነው የተጋጫችሁት?” ብዬ ጠየቅኹት
 
“አይ እሱን እንኳን ነገሩን ቀድሜ ስለማውቀው ብዙም አያጣላንም። ማወቅ ረጋ እንድትል ይረዳል። ስለምረዳት አልፋታለሁ።”
 
“ታዲያ ምንድን ነው? የሚነገር ዓይነት ከሆነ ነው የምልህ… ካልሆነም አትጨነቅ”
 
“ችግር የለውም። እነግርሃለሁ። ዋናው ነገር እኔም እሷም ትንሽ እረፍት ፈልገናል መሰለኝ። አንዳንድ ጊዜ በአንዱ መኖር የሚሸፈንልህን ነገር፣ ያ ሰው ጎድሎ ካላየኸው አታመሰግንም። ሁሉንም ነገር እንደ ተራ ጉዳይ ትቆጥረዋለህ። እሷም እኔም ዋጋችንን እርስበርስ እንድንተዋወቅ ይጠቅመናል። በዋናነት የግጭት መንስኤ የነበረው፣ ተራ ነገር ነው። ምን መሰለህ፥ ያዋጣናል ብለን የሆኑ እቃዎችን ሸጠን ነበር። ሀላፊነቱ ለእኔ ነበር የተወሰነው። ልክ እኔ ከሸጥኩት በኋላ ዋጋው ተወደደ።
 
መጀመሪያ ሳማክራት በስራ ስለምትጠመድ አንተ እንደፈለግኽ አድርግ ብላኝ ራሷን ገለል አድርጋ ነበር። እኔ ደግሞ የራሴን ጥናት አድርጌ፣ ሰዎች አማክሬ ሸጥኩት። በኋላ የተሻለ ዋጋ ማውጣት የሚችል ነገር መሆኑ ተገለጠልን። እና ጭቅጭቅ ጀመረ።
 
“ሳማክረሽ ችላ ብለሽው። ልብሽ ሁሉ ስራሽ ላይ ነው ያለው።” እላታለሁ፤ “አንተ ነገሮችን እንደፈለግኽ ነው የምታደርገው፣ ግድ የለህም” ትለኛለች።
 
ነገሩ ምክንያት ነው የሆነን እንጂ ጊዜ የሚጠብቅ ነገር ነበር። ያንን አጋጣሚ ተጠቅማ እሷ ከእኔ የተሻለ አሳቢ እና አዋቂ መሆኗን ለማሳየት ትፈልጋለች። እኔም አጋጣሚውን ተጠቅሜ፣ ልቧ ስራ ላይ ብቻ መሆኑን በማስታወስ የእኔን በደል እዘረዝራለሁ።
 
ታውቃለህ፥ በስራ በጣም ስለምትጠመድ ብዙ ነገሮች ያልፏታል። ደግሞ የቤተሰብ ሀላፊነቱ፣ እናትነቱ ስላለ አያስችላትም። ቤት መሆን መሳተፍ ትፈልጋለች። ታሳዝናለች።” አለኝ ሀዘኔታ እና ግራ መጋባት የተደባለቀበት ፊት እያሳየኝ
 
“ስራዋ ምንድን ነው?”
 
“ሀኪም ናት። ኦንኮሎጂስት ናት። ከባድ ሀላፊነት አለባት። ህክምና ስራውም ይበዛል፣ እሱ ላይ ደግሞ፥ እሷ በጣም ስራ ወዳድ ናት። አሁን እኔና አንተ እያወራን ብደውልላት እንኳን ኮምፒዩተሯ ላይ ተጥዳ የታካሚዎቿን መረጃዎች ስታስተካክል፣ ወይ የነገ ኬዞችን ስታደራጅ ነው የምታመሸው። እኔ ሁሌም ልረዳት ነው የምሞክረው። በስራዋ ደስተኛ ነኝ። ህክምናውን ባውቅና፣ ብችል ባግዛትም ደስ ይለኝ ነበር። ግን ደግሞ የስራ እና የኑሮን ጉዳይ ሚዛን መጠበቅ አለብህ።”
 
“እውነት ነው”
 
“ቀላል ምሳሌ ልንገርህ። ብዙ ጊዜ የሚከሰት ነው። ከምሽቱ 12 ሰዓት አካባቢ ቴክስት ተደራርገን ወይ ተደዋውለን እየመጣሁ ነው። ትለኛለች። እኔም እሺ ብዬ ምትበላውን አዘጋጅቼ፣ ምትጠጣውን አዘጋጅቼ እጠብቃታለሁ። 1 ሰዓት፣ ወይ 2 ሰዓት ያልፋል። በመሀል መሄድ የምፈልግበት ቦታ ካለ ወይ ወዳጆቼ ከጠሩኝ የጽሁፍ መልዕክት ትቼላት እወጣለሁ። ታብዳለች። እሷን ለማናደድ ያደረግኩት ያህል ይሰማታል። እሷ ጉዳይ ካለባት ሌላ ሰው ጉዳይ የሌለበት ይመስላታል። ራሷን ብቻ ነው የምታዳምጠው። ብዙ ነገሮች እሷ ስታደርጋቸው ልክ ሆነው ይኖሩና፣ ልክ እኔ ሳደርጋቸው ስህተት ይሆናሉ።” ብሎኝ ሳቀ። በፈገግታ አጀብኹት።
 
“እህ…” አልኩኝ የምሰጠው አስተያየት ነገር ያግል፣ ነገር ያብርድ ስላልገባኝ፤ ጨዋታው እንዲቀጥል በመፈለግ፥
 
“ሌላ ምሳሌ ልስጥህ፥ ከልጆቼ ጋር ባለኝ ግንኙነት ትቀናለች። ቅድም ተደዋውለን ራሱ አንድ ሁለት ተባብለናል። ልጃችን ከኒውዮርክ ነገ ትመጣለች። ቀድመን ሁለታችንም እናውቃለን። ነገር ግን ከአውሮፕላን ማረፊያም እንድቀበላት ስለምትፈልግ ዛሬ እኔ ጋ ደወለችልኝ። ቅድም ስደውል መደወሏን ነገርኳት።
 
“ለምንድን ነው እኔ ጋር ያልደወለችው?” አለችኝ። ለምን ልበላት?
 
እኔ የስራ ፀባዬም ጊዜ ስለሚሰጠኝ፣ በተፈጥሮዬም እንደዚያ ስለሆንኩ ልጆቼ ጋር በየቀኑ አንድ ደቂቃም ቢሆን እደውላለሁ፤ ያንን ለምደው ሳልደውል ስቀር ደግሞ እነሱም ይደውላሉ። እሷም ጋር ይደዋወላሉ። ግን ያለባትን ጫና ስለሚያውቁ፣ ብዙምም ፊት ስለማትሰጣቸው አጥሯን ያከብሩላታል።
 
እኔ አብሬያቸው መሬት ላይ ስንከባለል፣ ትራስ ስወራወር፣ ስላፋ፣ ቴኒስ ስጫወት ነው ማሳልፈው። እሷ ያንን ለማግኘት እድሉም የላትም። ከስራ ጸባዩዋ አንጻር ይህንን ማድረግ ለእሷ ቅንጦት ነው። በዚህም የተነሳ ልጆቻችን እኔን የበለጠ ይቀርቡኛል። የምልህ እሷንም ይቀርቧታል፣ ግን እኔ ጋር ይበልጥ ይሆናሉ። እሷን ይረዷታል። ዝም ብለው ሄደው አይረብሿትም። ነይ እንውጣ፣ ገበያ እንሂድ፣ ሜዳ እንሂድ አይሏትም። ትልልቆች ስለሆኑ ያውቃሉ።
 
እሷ ለመታቀፍ እና ለመሳም “እኔስ” ብላ ጠይቃ ነው እንጂ ዝም ብለው ሄደው አይጠመጠሙባትም። እሷም ያን ያህል ጊዜ መስጠት ብትፈልግም አትችልም። ስራዋ በጣም ይፈልጋታል። የብዙ ሰዎች ሕይወት እጇ ላይ አለ። እና ከእኛ ጋር መሆኑ ቅንጦት የሚሆንበት ጊዜ ብዙ ነው።
 
ሀኪም ማግባት ቀላል ነገር አይደለም። በጣም ከባድ ነገር ነው። ሀኪም ካላገባህ ወይ ሀኪም ካልሆንክ አይገባህም። ከሀኪም ጋር ጓደኝነት እንኳን ከባድ ነው።
 
በብዙ ውጣ ውረድ ነው የምታልፈው እሷ። የተለያዩ ታካሚዎች ይመጣሉ። የተለያዩ ታሪኮችን ትሰማለች። በመሀል ቆዳዋ ጠንክሯል። ሞት አይደንቃትም። የምልህ፥ በግዷ ትጠነክራለች። ጠንካራ ተመስላለች። ብዙ ጊዜ ሰው ሲሞት አይታለች።
 
የረዳችው ሰው፣ ለክፉ አይሰጥህም ያለችው ሰው፣ ተስፋ የሰጠችው ሰው፣ የተላመደችው ሰው ሲሞት አይታለች። ለቤተሰብ ዓይናቸውን እያየች የሟቹን ወሬ ማርዳት አለባት። ስራዋ ያስገድዳታልና አብራም ማልቀስ አትችልም። ዓይናቸውን እያየች፣ ፊትለፊታቸው ቆማ “ስነግርህ አዝናለሁ። ሚስትህ ሞታለች” ትላለች። ቀላል አይደለም። በሀዘኑ ብዛት ድብርት ውስጥ ገብተው መልሰው እሷ ጋር ይመጣሉ። መርዳት፣ ሪፈር መጻፍ አለባት። ነገ ያንን ወሬ ከአንዱ ለማስቀረት ስትል ዛሬ ብዙ መስራት እንዳለባት ታስባለች። ቀላል አይደለም። እና አንዳንዴ ትንሽ የራሷን ቦታ ልትፈልግ ትችላለች። በአንድ መልኩ እሷንም እኔንም ለመርዳት ነው ለጊዜው ገለል ማለት እንዳለብኝ የወሰንነው።”
 
“አይዞን! (የአይዞንን ትርጉም አስረድቼው ቃሉን እሱም ይጠቀማታል) ሁሉም ጥሩ ይሆናል። በቅርቡ ሁሉም ተስተካክሎ አብራችሁ እንደምትሆኑ ተስፋ አደርጋለሁ።” አልኩት።
 
“ይመስለኛል! በቀጣዩ ወር የጋብቻ አማካሪ (marriage counselor) ጋር ለመሄድ ቀጠሮ ይዘናል። ነገሮች ጥሩ መሆናቸው አይቀርም።”
 
መልካም ምኞቴን ተመኝቼለት ሌላ ጨዋታ ቀጠልን።

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s