ስለሀሳብ ልዕልና ሲወራ…

ምርጫውን ፍትሀዊ እና ዴሞክራሲያዊ ለማድረግ የተደረገው የቃል ተስፋ መልካም ነው። እግዚግዚአብሔር ፈቅዶ ምርጫው ነጻ ሆኖ ቢከናወን ግን፣ ኢህአዴግ በምን ቁመናው ሊቀጥል ይችላል? 🤔
 
በርግጥ “ከማያውቁት መልዐክ የሚያውቁት ሰይጣን” በሚል ብሂል የሚገብርላቸው ሊኖር ቢችልም ቅሉ፥ ለክፋታቸው ሲነዙት የኖሩት የብሄር አጀንዳ መልሶ እነሱኑ ሳይሰለቅጥ የሚመለስ በማይመስል መልኩ ተቀጣጥሏልና፥
 
“ምርጫው በነጻ እና ፍትሀዊ መንገድ እንዲደረግ ፈቃደኞች/ቁርጠኞች ነን” ማለታቸውን በራሱ፣ በሰላም እንደሚለቁ ቃል የገቡ ያህል እቆጥረዋለሁ።
 
(የሚነደው ግን፥ የነጻ እና ፍትሀዊ ምርጫ ወሬ እና ምኞት እንኳን ካለነሱ ፈቃድ የማይቻል የነበረ መሆኑ ነው። ይኽንንም ውለታ እንደዋሉ እንጂ መሆን እንዳለበት አይቆጥሩትም።)
 
ኢህአዴግ “ሀሳብ ሸጠን ነው የምናሸንፈው” ሲልና ስለሀሳብ ልዕልና ሲያወራ መስማት ይገርማል። እንደው ምናልባት በታምራት ደስታ (ነፍስ ይማር)
 
አንድ ዕድል ሰጥተሽኝ ልካስሽ ደግሜ፣
ያውም አገልጋይሽ ታማኝ ባሪያሽ ሆኜ
“አንድ ዕድል ሰጥተሽኝ ልካስሽ ደግሜ፣
ያውም አገልጋይሽ ታማኝ ባሪያሽ ሆኜ”
 
ብለው ይጀነጅኑን እንደው እንጂ ምን ቀራቸው?
 
አብረው ተባብረው ዘረፉ፣ ገረፉ፣ ደፈሩ፣ አባረሩ፣ ጣት ቀሰሩ፣ ጣት እንቆርጣለን ብለው ፎከሩ፣ ከፋፍለው አባሉ፣ ቀለም ጠልተው ቀለም ደፍተው፣ የቀለም ቀንድ ሰባብረው፣ ሕዝቡን በድንቁርና አጥረው አኖሩት፣ (ከርሞ ማመናቸውም ተመስገን ነው)፣ ምኑ ቅጡ ተሰፍሮ ተዘርዝሮ ያልቅና?
 
በተጭበረበረ ምርጫ ገነው፣ አሁንም በየመሀሉ በሊቀመንበራቸው በኩል “ተፎካካሪ” ያሉትን ይወቅሳሉ። ያስጠነቅቃሉ። ላይ ላዩን ገር ሆነው፣ ውስጥ ውስጡን አሁንም በሚዛን ሲቀመጡ እነሱ እንደሚሻሉ ያስባሉ። ያሳስባሉ።
 
በምርጫ ምክንያት ለተፈጠሩ ቀውሶች በሙሉ ዋናው ድርሻ ኢህአዴግ እንጂ ማን ሆኖ፣ አሁን “ወደኋላ ሄዶ ያለፈውን ማንሳት እና በትናንት መኖር አያስፈልግም” ካሉ በኋላ፣ በጨው መታጠብ ካልሆነ በቀር፣ መለስ ቀለስ እያሉ ሌላውን ለመውቀስ እና አበክሮ ለመውቀስስ ምን አቅም ያገኛሉ?
 
የኢህአዴግ ነገርማ
ያልጠፋነው፣
ከእግዚአብሔር ምህረት የተንሳ ነው”ን
እያስዘመረን የሚኖር ጉዳይ ነው!
 
እግዜር ቸር ቸሩን ያድርግልንማ!

ቤቲ እና ደሳለኝ፡ እንደወረደ! :)

የቤቲን እና የዶ/ር ደሳለኝን ቃለ መጠይቁን አየሁት። የተባለውን ያህል የተጋነነ ሆኖ ግን አላገኘሁትም። ደሳለኝ አለመዘጋጀቱ ያስታውቃል። መዘጋጀት ሲባል፣ ለቃለ መጠይቅ ሳይሆን፣ በአጠቃላይ እንደ ፓርቲ አመራር ራሱን በብዙ ነገሮች ውስጥ ማለማመድ እና ነጥሮ የወጣ ሀሳብ/መልስ የሚሆን ነገር ማዘጋጀት ነበረበት። አባላቱም እንዲሁ ማድረግ ነበረባቸው። ለከእንግዲውም መዘጋጀት አለባቸው።
 
በዋናነት ደሳለኝን የማይሆን ነገር ውስጥ የከተተው ጋሻው እና ክርስቲያን የተባሉ ስራ አስፈጻሚ አባላቶቹ ያደረጉትን ያልተገባ እና ያልበሰለ ንግግር ለማስተባበል እና “ማለት የፈለጉት” እያለ፣ ያላሉትን ሊልላቸው እና ያሉትን ሊያለባብስላቸው ባደረገው ጥረት ነው።
 
ከዚህ የምንማረው/የምንረዳው፣ አባላቱ (እንዲሁም ሌሎቻችን) ከፌስቡክ ወጣ እያሉ ወደ መጽሐፍት ገጾች አየት ማድረግ እንዳለባቸው ነው። እሱም ዐይኑን ያፈጠጠ፣ ጥርሱን ያገጠጠ ነገርን በይቅርታ ማለፍ ቢችል ተወዳጅነት እንደሚጨምርለት ከዶ/ር አብይ ኢህአዴግ መማር ይቻላል።
 
አብን ገና የሶስት ወር ጨቅላ ፓርቲ እንደመሆኑ መጠን ክፍተቶች ቢታዩ ብዙም ባያስደንቅም፣ ችኩል ችኩል እያሉ የፈጠሩትን ስህተት፣ “ሌላው ሰው ካለበት የመረዳት ችግር የተነሳ ነው እንጂ እኛ ልክ ነን” ማለት ወዳጅ እና ደጋፊ ያሳጣል እንጂ ሩቅ አያስኬድም። ከአሁኑ ያልተጀመረ ይቅርታ የመጠየቅ እና ራስን የማረም ባህልም፣ ውሎ አድሮ ስለመቀጠሉ መተማመኛ አይሰጥም።
 
ነገሮች በግልጽ ለክርክር እና ቅሬታ ክፍት በሆኑበት ቦታዎች/ሁኔታዎች “ስህተት ነበር። ይቅርታ። እንዳይደገም እንመክርበታለን።” ብሎ ማለፍ እየተቻለ፣ ባስረዳው ቁጥር የማይሆን ነገር ውስጥ ራሱን ከቷል። በዚህም፥ ከ27 እስከ 48 ደቂቃ ያለው ጊዜ በከንቱ እና ራሱን በማሳጣት የባከነ ነው። ልክ እንደዒድ በዓል መልካም ምኞት መግለጫው “ሌላን ሰው ካስከፋ ይቅርታ” ብሎ በሰላም እና በክብር አልፎት፣ ሀሳቦቹን ማስረጽ እና ሀሳብ ላይ ማውራት ይችል ነበር።
 
ደሳለኝ ምናልባትም ፓርቲውን (የፓርቲውን ስም) ለማስተዋወቅ ያህል ጥሩ እድል አገኘሁ ብሎ የሄደ ዓይነት ይመስላል። እሱ ደንገጥ ሲል እሷ በስሜታዊነት እየተናጠች ኮስተር ማለት መጀመሯ ነጻ ጋዜጠኛ የማያስብላት ነው። ጭራሽ ልትቆጣው ሁሉ የሚያምራት ቦታ አለ። ደካማ ጎን ያገኘች እየመሰላት፥ የልብ ልብ እየተሰማት፣ እንደ ጋዜጠኛ ቴዎድሮስ ፀጋዬ ለመሆን የፈለገችባቸው ቦታዎች ብዙ ናቸው።
 
እንደ ቃለመጠይቅ አድራጊነቷ እውነቱን እና ሀሳቡን መፈልፈልና ማውጣት ላይ እንጂ፣ የእሷን ሀሳብ ወይም መከላከያ እና ቅሬታ ማከል ላይ ማተኮሯ ለመደበኛ ቃለመጠይቅ የሚያስኬድ አይመስለኝም። ያም ሆኖ ግን፣ እንደፈለገች አድርጋ መጠየቅ መብቷ ነው። ሊያሰድባት የሚያደርስ ነገር የለም።
 
የተከፋ ሰው፥ ፕሮግራሞቿን አለመስማት፣ ወይም ደግሞ እሷ ጋ ቃለ መጠይቅ አልደረግም ብሎ ሊያምጽ ይችል ይሆናል፣ እንጂ “ሊቀመንበሬን ይህን ጠየቅሽብኝ፣ አጨናነቅሽብኝ” ብሎ የተሳደበ አባል ወይም ደጋፊ፥ እድሉን ቢያገኝ ልሰር ልግረፍ ማለት አያምረውም አይባልም እና “ሳይቃጠል፣ በቅጠል!” ነው መሆን ያለበት።
 
በየመሀሉ እየገባች በተነሳው ነገር ላይ ሁሉ ከኦሮሞ ጋር ማነጻጸሯም በአስፈላጊ ቦታ የሆነ አይደለም። ራሷንም ወደ ኦሮሞ ብሔር ያዘነበለች አድርጎ ያሳያታል።
 
ነገሬ ብላ ፓርቲውን ማሳጣት ላይ ወይም ራሷን እነደሀይለኛ ማስቆጠር ላይ ማተኮሯን የሚያሳይ፣ መሀል ላይ በቃለመጠይቁ ወቅት ያለተጠቀሰ እና ካለደሳለኝ እውቅና የተሰነቀረ የልማታዊ አርሶአደሮች ምስል አለ። በመንግስት የሚደገፈው የአማራ ክልል ቴሌቪዥን (መቼቱ አልተጠቀሰም) ለፕሮፖጋንዳ ያደረገውን ቃለ መጠይቅ እንደማስረጃ መሰንቀሯ ሳያንስ፣ እሱ ተመልክቶት ምላሽ እንዳይሰጥበት ማድረጓ የሙያን ስነምግባር ያጓደለ መሰለኝ።
 
ደሳለኝም ቢሆን “ውሻ በቀደደው ጅብ ይገባል” እንዲሉ፣ እሷ በጀመረችው ማነጻጸር ገብቶ ‘ፓርቲው የተቋቋመው፣ እና የምናደርገውን ሁሉ የምናደርገው ሌሎች ስላደረጉት ነው’ ዓይነት ገደምዳሜ ላይ እንድንደርስ የገፋፋን ይመስላል።
 
የአማራ ፓርቲ ሊቀመንበርነት፣ ፓርቲው ለመደራጀት ገፊ የሆነውን ምክንያት የስሙን ያህል፣ በጥናት እና ንባብ ተደግፎ አጣፍጦ ማስረዳት ይጠበቅበታል/ት ነበር። ቢያንስ ስለፕሮግራም ሲጠየቅ መደናገጥ የሚጠበቅ እና አስፈላጊ አልነበረም። እንጂ፣ ቢያንስ አማራ ኢትዮጵያን በመገንባት ሂደት ያበረከተውን ነገር ለመጥቀስ፣ ስነጥበቡን እና ኪነ ጥበቡን መጥቀስ ብቻውን ይበቃው ነበር።
የእድገት እና የስልጣኔ ጠቋሚ የሆኑትን የወሊድ ቁጥር መቀነስ እና ተያያዥ ዴሞግራፊክ ነገሮችን፣ እንደበደል ማቅረቡም ከምሁርነቱ አይጠበቅም። ከዚያ ይልቅ በቅርቡ እንኳን በአማራ ቴሌቪዥን ላይ የቀረቡትን የእስር ቤት አያያዝ ፕሮግራሞች ጠቅሶ መናገር ይችል ነበር።
 
የአካባቢውን የማህበራዊ እና ፖለቲካዊ ሁኔታ፣ በጊዜ መዳርን ጨምሮ ሌሎች ልማዳዊ ድርጊቶች ያበረከቱትን አስተዋጾ፣ ት/ት እንዳይስፋፋ እና መሰረተ ልማቶች እንዳይከናወኑ በመደረጉ የደረሱትን ጥፋቶች፣ እንዲሁም ብዙ መውለድ ለመቀንጨር የሚያድርገውን አስተዋጽኦ እና ያም የሚያመጣውን የአእምሮ ውሱንነት ማሰብና፥ ጉዳዩን በተሻለ ማስረጃ ማቅረብ ነበረበት።
 
ወይ ደግሞ እንደ ኢህአዴግ/ብአዴን፥ ፓርቲው ዋና ዒላማ ያደረገው ገበሬውን ሆኖ፣ በአሉሽ አሉሽ እንፍሽፍሽ ማለፍ ፈልገው ይሆናል።
 
በዚህ የተነሳ፣ ማህበረሰቡ ሊደነቅበት በሚገባው ነገር ክስ ማጠናከሪያ አድርጎታል። (ልክ መስታወት ሲሰበር ይቆርጣል፤ ካዩበት ያሳያል እንደማለት ያለ፥ ነገሩን ከብዙ አንግል ማየት እና ትክክለኛ መከራከሪያ ማቅረብ ይቻላል። እኔ እንኳን ከሱ የተሻለ ይህንን ጉዳይ ማስረዳት የምችል ይመስለኛል።)
 
እሷም ጉዳዩ ላይ ንባብ ጠገብ ብትሆን ኖሮ፣ እዚህ ጋር ጥሩ ውይይት ያደርጉ ነበር። ባይሆን ግን የማዕከላዊ ስታትስቲክስ ሪፖርቶች ላይ የአማራው ቁጥር አንሶ እንዲዘገብ የሚደረግበትን ምክንያት ማህበረ ፖለቲካዊ አድርጎ ማቅረብ እና ነጥብ ማስያዝ ይችል ነበር።
“በአብን ስም ያልተገባ ነገር የሚያደርጉ ስላሉ፣ ግለሰቦች ስለሚጽፉት ነገር ፓርቲው ሊወቀስ አይገባውም” ዓይነት ነገር ባለበት አንደበቱ፣ ስለእነ ግንቦት 7 ሲናገር ርግጠኛ ሆኖ “ደጋፊዎቻቸው” አባባሉም ከወገንተኝነት ያልጸዳ አቋም እንዳለው ነው የሚያሳየው።
 
ደግሞ በአብን ስም ለተደረጉ ስህተቶችስ፣ ፊት ለፊት ቀርቦ የእኛን ፓርቲ አይወክልም ብሎ ወዳጅንም ማረጋጋት፣ ጠላትንም ማስደንገጥ አይቻልም ወይ? ወይስ እንደ ኦነግ ሰው ተገድሎ፣ ሰው ተባሮ “አባላቶቼ አይደሉም። በስሜ ነው ይህን የሚያደርጉት።” ለማለት ነው የሚጠበቀው?
 
ሲመስለኝ፡
 
የአብን ነገር እንደ ትኩስ ሽልጦ “ጠዋት ተመርቶ፣ ከሰዓት መርካቶ” ዓይነት ይመስላል። ምናልባትም ዋና ግብ ያደረጉት ለመጪው ምርጫ መሳተፍ ነው።
 
የምር ለአማራው የሚቆረቆሩ ከሆነ ግን ከሕዝባዊ ስብሰባዎች እና ውይይቶች እኩል፣ ውስጣዊ ውይይቶች፣ የንባብ እና የርስበርስ ስልጠና፣ የመጽሐፍ ተዋውሶ ማንበብ ዝግጅቶችን ማድረግ ይኖርባቸዋል። ያድርጉ አያድርጉ ባላውቅም ከሚናገሯቸው እና ልዩነትን ከሚይዙባቸው ነገሮች ተነስተን፣ ክፍተት እንዳለ በግልጽ መናገር ይቻላል።
ነገሩን ጠቅለል ስናደርገው፡
 
ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ አብንን ሳይወክል፥ ስለአብንም ሆነ አማራ መደራጀት ቢጠየቅ ከዚህ የተሻለ ቃለመጠይቅ ማድረግ ይችል ነበር ብዬ አስባለሁ! ይህም የሚሆነው ከእርጋታ እና ነገሩ ላይ ከመብሰል እንጂ፣ ከግል አቅም አይደለም። ዶ/ር ደሳለኝ እርጋታውን እና ቅንነቱን አሳይቷል።
አብን እንደሶስት ወር ዕድሜው በጣም ጥሩ እየሰራ ነው! እንደ አማራ ሕዝብ ግን ገና ነው! ለሰፊው እና ስልጡኑ አማራ ሕዝብ አብን ይጠበዋል።
 
ባልተያያዘ ወሬ ደግሞ፡
 
እሱ “አብን ለሕብረ ብሔራዊ ድርጅቶች ስጋት ነው” ያላትን ወስጄ፥ ሕብረ ብሔራዊው ግንቦት 7፣ ለአብን ስጋት እንዳይሆን እንደሚፈሩ፤ አባላቱም በዚህም ስጋት የተነሳ ግንቦት7ን ማጥላላት ላይ እንደተጠመዱ ብነግረው አልጠላም።
 
በቅንነት ተደራጁ! የተደራጃችሁም በቅንነት ተራመዱ! በርቱ!
ሰላም!

ከማዕበሉ ባሻገር…

እንደሚታየው፥ ሁላችንም በፍስሀ እና በእርካታ፣ በስሜት ማዕበሉ ላይ ጡዝ ፍንጥዝ እያልን ያለበት ሁኔታ ነው ያለው። ይኽን ያሳየን አምላክ ክብር ምስጋና ይግባው!
 
ሚዲያዎቹም፣ አክቲቪስቶቹም፣ ፖለቲከኞቹም፣ ጋዜጠኞቹም… ሁሉም በአንድ ዓይነት አጀንዳ ተወስዶ፣ በአንድ ዓይነት ግብር ተጠምዶ …ደፈር ብሎ የህግ የበላይነት ይከበር የሚል እና ስለፍትህ የሚጮኽ፤ ስሜታችንን ደርዝ በማስያዝ፥ ለነገ የጋራ ጉዳዮች እንድንዘጋጅ አቅጣጫ የሚጠቁም፤ የንግግር ባህላችን እንዲሻሻል የተለያዩ ዝግጅቶችን የሚያቀርብ፤
 
ቢያንስ ፍቅርን እና አንድነትን በሚያደረጅ መልኩ፥ ድሮ እነ ሂሩት መንግስቴ በ”ከሴቶች አድማስ” በ”ከያቅጣጫው” ዓይነት ፕሮግራሞች ዙሪያ ገባውን ያስቃኙን እንደነበረው፣ የገጠር እና የከተማ ማሕበረ – ባህላዊውን መስተጋብር፣ እና የጋራ እሴቶቻችንን ዓይነት እንኳን በማሳየት፥ የእርስበርስ ትስስራችንን በማውሳት፣ ለውጡን የሚያቀላጥፉ ተግባራትን የሚያደርግ ጠፍቶ፥ ሁላችንም በውዳሴ ላይ የማተኮራችንን ምክንያት ሳሰላስል እኒህን 3 ምክንያት መስለው ታዩኝ።
 
1) አጀንዳውን ሁሉ ኮካዎች ያረክሱታል!
 
በተወሰነ መልኩ ከውዳሴ መስመር ወጣ ተብሎ የሚሰጥ አስተያየት፣ ለሕወሃት ኮካዎች የሰርግና ምላሽ ያህል የሚያስቦርቅ መሆኑን ታዝበናል። በዚህም የተነሳ ምንም ዓይነት አጀንዳ ቢነሳ፣ ምንም ዓይነት ነቀፋ እና ትችት ቢከናወን ‘ይደሰታሉና’፣ ብሎ የመፍራት ነገር አለ። ለዚህ አስተዋጽኦ የሚያደርገው፥ የለውጥ ፈላጊው ወገን መካከል፥ አንዳንዶች ከሌሎቻችን የተሻልን አገር ወዳድ፣ አጋዥ፣ ሰላም እና ለውጥ ፈላጊ መስለን በመታየታችን በምናሳየው የተሟጋችነት እና አፋችሁን ዝጉ ባይነት መታገላችን ነው። ፍሬ ሀሳቡ ቀርቶ፣ ብሽሽቁ ላይ እናተኩራለን።
 
ሆኖም ግን፥ ማገዝ ፈርጀ ብዙ ነውና፣ የተሰራውን በማድነቅ ከመደሰት እኩል (ወይም በላቀ ሁኔታ) ለተራማጅ መንግስት፥ ነቀፋ ትልቅ እገዛ ያደርጋል።
 
2) አሁን ከጊዜው ጋር የሚዜመውን ካላዜምኩ፣ የሚጣጣለውን ካላጣጣልኩ፥ ኋላ ተከታይ/አድማጭ/ተመልካች ባጣስ የሚል ነገር ሊኖርም ይችላል!
 
ሲሆን፥ ማህበራዊውንም ሆነ መደበኛውን ሚዲያ ተከታታዮች ከምንቃኘው ይልቅ፣ ሚዲያው የሕብረተሰቡን ስሜት በመቃኘት ረገድ ሚና መጫወት ይጠበቅበታል። አሁን እየሆነ ያለው ግን በተገላቢጦሽ ነው። ከሕዝብ ጋር ለመቆም፤ ሰው ስለሚከፋ በሚል፣ በይፋም ባይሆን ውስጥ ውስጡን ማባበል/ማስመሰል/መመሳሰል አለ። ይህም በተለይ የኢመደበኛው ሚዲያ መሰረት አድማጭ/ተመልካቹ ስለሆነ ነው። በዚህ የተነሳ፣ ደፈር ብሎ ሀሳቡን የመግለጽ ነጻነቱን ለመጠቀም የሚሞክረውን ሳይቀር በማሸማቀቅ የምንጫወተው አሉታዊ ሚና አለ። ስድብ አስታጥቆ በብሎክ የሚያሰናብተውም ብዙ ነው።
 
ይህ ደግሞ ጭራሽ የለውጡን ጽንሰ ሀሳብም የሳተ ነው!
 
3) ፍቅራችን እና ፈንጠዝያችን መሰረት ያደረገው፥ ምሬትና ጥላቻን እንጂ፣ እውነተኛ የለውጥ ፍላጎትን አይመስልም! ስለዚህም፥ ስለምንነቅለው እንጂ ስለምንተክለው ነገር ቸልተኞች ነን።
 
ይህንን ለማለት ያስደፈረኝ፥ ገና ካሁኑ የሰለቹን ነገሮች በዝተው በማየቴ ነው። ገና ካሁኑ ትናንት ከሕዝብ ጋር ሆነው ድምጻቸውን በማሰማታቸው ክብርና ተቀባይነትን ያተረፉትን ሀጫሉን እና ቴዲን በራሳችን የልብ ምት መዝነን “ዐይናችሁ ለአፈር” ለማለት በመውተርተራችንም ፍንትው ብሎ ይታያል። አምባገነኑን ኢሳያስን ባቆላመጥንበት ዕለት እና መድረክ ላይ መሆኑ ደግሞ ይበልጥ ያስገምተናል። እንደሚነዳ ፍሪዳ ለዛሬው የስሜት ነውጥ መስዋዕት ልናደርጋቸው ስንንጋጋ ፍጹም ቅሬታም ያለብን አይመስል። ስንደመር ለመቀነስ የምንሯሯጠው ነገር ብዙ ነው።
 
ይህችን አንጻራዊ ሰላም እና ነጻነት ለማግኘት የፈሰሰውን ደም፣ የጠፋውን ሕይወት፣ የተዘጋውን ልሳን፣ የተሰደደውን ሕብረተሰብ፣ የጎደለውን አካል፣ የጨለመበትን ሕይወት፣ የወረደውን እንባ በማጣጣል ውስጥ ብዙ ርቀት መጓዝ እንደምንችል እንጃ።
 
ባለፈው “ቀሪ የፖለቲካ እስረኞችም ይፈቱ” ሲባል፥ “ኸረ ባካችሁ ዘንድሮም እስረኛ ይፈታ ፖለቲካ ላይ ናችሁ። ተደመሩ” የሚሉ አፍላ ካድሬዎች አይተን በግነናል። ሶማሌ ክልል ውስጥ ሕዝብ ሲያልቅ፣ ጌዲኦ ተፈናቅሎ ሲያልቅ፣ ሀዋሳ እርሰበርስ ተባልቶ ሲያልቅ፥ ካፉ ቃል ሳይወጣ በፌሽታ ውስጥ የነበረ “ቂሊንጦ እስረኞቹ አመጹ” ሲባል፣ “ለምን እርምጃ አይወሰድም” ሲል ታዝበናል። ሰው በላው አብዲ ኢሌ ጌታቸውን አማው ብለን “ጀግና” ሲባል ሰምተን “ቦ ጊዜ ለኩሉ” ብለን ተገርመናል።
 
(የሆኑት ነገሮች ሌላ ጊዜ ቢሆን ኖሮ ፕሮፋይል ምስል የሚያስቀይሩ፣ ዘመቻ የሚያስደርጉ ነበሩ። ጠቅላይ ሚኒስትሩም ትናንት ያስተላለፉትን የማረጋጋት ተግባር፥ ቀደም ብለው በማድረግ በመካከል የጠፉት ሕይወቶች የመትረፍ እድል ነበራቸው) የኢትዮ ኤርትራ ሰላም ወሬ እንኳን ገና ካሁኑ የሰለቸው አለ።
 
ቸልተኝነታችን ዋዛ ቢመስልም፣ ውሎ አድሮ ስር ከሰደደ አሳሳቢ ነውና እስኪ ሀሳብ እንጨዋወትበት!
 
ሰላም!

3 ወሩ እና አብዮት ጥበቃው…

ዋዜማው፥ በጠቅላዩ ፍቅር በጨበጣ የተነደፉ ሰዎች አላስ ሆኑብን። መተንፈሻው፣ መላወሻው ቸገረን። ከምንግዜውም በላይ ሀሳብን የመግለጽ መብት እና ነጻነት አደጋ ውስጥ እንደወደቁ ተሰማን። ነገሩን ይበልጥ አስደንጋጭ ያደረገው፥ አፋችንን ለመዝጋት ላይ ታች የሚሉት የገዛ ወዳጆቻችን እና፣ ትናንት በክፉም በደግም አብረን የጮኽን መሆናቸው ነው። የመታፈንን ህመም ያውቁታል፣ ዝም የማለትን እዳ ይረዱታል… የምንላቸው መሆናቸው ነው።
 
“ኀዘንሽ ቅጥ አጣ
ከቤትሽ አልወጣ፤
ገደለው ባልሽ፤
የሞተው ወንድምሽ!”
ዓይነት ሆነ።
 
ኮካው ማረኝ ማረኝ
ኮካው ማረኝ ማረኝ
የዘንድሮስ ካድሬ ጭራሽ አላማረኝ
ብለን ለመጫወት እና ነገሩን ለማዋዛት ሞከርን።
 
ሰውዬው አፈወርቅ ጮሌ ነው። ይናገራል፣ ይናገራል… እንደ ጥዑም ምላሰኛ አፍቃሪ፥ አታላይ የሚባል ዓይነት ነው። ምነው ሲያወራ ውሎ፣ ሲያወራ ቢያድር ያሰኛል። ቢፈልግ ከጸሀይ ጋር ይነጋገራል፤ ቢፈልግ ጨረቃን ለቅሞ ቤታችን ያሳድራታል። አንጀታችንን ቅርጥፍጥፍ አድርጎ በላው፤ በተስፋ ተሞላን፤ ደስም አለን። በየምኩራቡ ተጸለየለት (አሁንም ቢሆን የአገር ጠላት ካልሆነ በቀር፥ የማይጸልይለት፣ መልካም የማይመኝለት የለም) በተለይ ለአመታት በነገር ከመቁሰላችን አንጻር፣ በንግግር አለመደሰት እንዴት እንችላለን?
 
ቀድመው ቀብድ ፍቅር አስይዘው ያቀነቀኑለት በኩራት ሆነው፣ ስጋት እና ጥርጣሬ ያደረብንም ከነጥርጣሬያችንም ቢሆን ማረጋጋቱን ወደነዋል። ‘ወሬው ወደተግባር ይለወጥ፣ ተቋማዊ ይሁን’ ስንል፥ እኛ ጊዜ የመስጠትና የመንጠቅ አቅም ያለን ይመስል፥ ግማሹ “ጊዜ ስጡት” ይላል። ግማሹ “ፖለቲካ ስለማታውቁ ነው” ይላል። ግማሹ ዝም ብሎ “እሽሽ” ይላል። ቀድመው ስም በመስጠት ማሸማቀቅ ተያዘ።
 
አገሩ ከደረ፣
መንደሩ ከደረ
አበል መክፈል ቀረ
አልን።
 
ፓርላማ ላይ ቀርቦ የፓርቲውን አሸባሪነት ያመነ ጊዜ፥ ሁላችንም ቁስላችን ታኮልናልና እጅ ሰጠን። እንዳንጠላው ሆነን ወደድነው። (ሲፈጥረን ፈርዶብን፥ የምንደነቅበት እና የምንጠይቀው አናጣም መቼስ። “እንዲህ ዓይነት ልብ እያለው፣ እንዴት ሲረገጥ እና ሲሾም ኖረ?” ብለን ጠየቅን። “ግን እንኳን ችሎ ኖረና፣ ይህን ቀን አየን” ብለን ተደስትን።)
 
ካድሬነቱን እንደርስት የሚቆጥሩትም ኖሩና፥ ቀድመው ባልከደሩት ላይ ሙድ መያዝ ያማራቸው ሁላ ነበሩ። ለነገሩ የእኛ ሰው ጸባይ አስቸጋሪ ነው። ጠዋት ቀድሞ ስለተነሳ እና ማታ አርፍዶ ቤቱ ስለገባ፥ ጸሐይና ጨረቃ የተሻለ ዘመዶቹ የሚመስሉት ደነዝ ሁሉ አለ። ከእነዚህም ጋር ነው የምንደመረው።
 
“ከጎኔ ቁሙ! አብዮቱን አጣብቁኝ! አግዙኝ! ተደመሩ” ብሎ ነዳን… ተደምረን ተነዳን። ሆ ብለን ወጣን! “እንኳን ዘንቦብሽ፣ እንዲሁም ጤዛ ነሽ” አፍላ ካድሬዎቹ ሰበኩን፥ ሁሉም አብዮት ጠባቂ ሆነ። “በህልሜ ነው በእውኔ” አልን። ህልምም ከሆነ ምነው ከዚህ ህልም ዘላለም ባልነቃን ብለን ተመኘን።
 
ቦንቡ ሲፈነዳ፣ እንቡጡ ፍቅራችንም አብሮ ፈነዳ። “ባሌን ጎዳሁ ብላ” አለች አሉ። ጭራሽ ፍቅር በፍቅር አደረጉት። አዲስ አበባ አበባ ሆነ። እንዳዲስ አማረበት። “ከሱ ያስቀድመኝ” አልን። “አብይ ድረስ” ብለን ማልን። ጠላትም ደስ እንዳይለው፣ ሁሉም ሰው ከአብይ ጋር ነኝ አለ። እኛም ፈንጥዘን ሁለት ሽንጣም ግጥሞች አዋጣን። ለሰፊው ሕዝብ ጥቅም ስንል፥ “ከ60 ክፍል በላይ የጫርናት ባይገርምሽ መዝጊያም ይሁን” አልን። “ተመስገን የሰራዊት ጌታ! ስራህ ግሩም ድንቅ ነው!” አልን። አሁንም በዚያው ስሜት ነን! በ3 ወር ውስጥ የተመለከትነው ተአምር ነው!
 
(በበኩሌ፣ በመንግስት ደረጃ አንድ ሰው ብቻውን ቆሞ ሲታይ ደስ አይለኝም። አምባገነን ከማድረግ ግብ የዘለለ ጥቅም አለው ብዬም አላስብም። ስንንሰፈሰፍለት፣ ውሎ አድሮ ስዩመ እግዚአብሔር ነኝ ቢል ይፈረድበታል? ያኔ እኔ ነኝ ጠበቃ/ተሟጋች የምሆንለት!
 
በአመራር ደረጃ አንድ ሰው ብቻ ሲታይ፥ ለጠላትም ከልብ አያስደነግጥም፤ ለወዳጅም አያስተማምንም። እሱ አንድ ነገር ቢሆንስ? ብሎ መሳቀቅ አለ። በርከት ብለው ስለቡድን፣ ስለግብረ ሀይል ቢያወሩ ግን፥ ሕዝብ ነገሩን የአንድ ሰው ህልውና ጉዳይ ብቻ አያደርገውም ነበር። አንድ ሰው ላይ የተንጠለጠለ ነገር ሁሌም ሰቀቀን ነው ትርፉ። መቼስ ማልጎደኒ? እሱ ደሞ ለጉድ ተመችቶታል!
 
የእናቱን ትንቢት የሚያምን ሰው መሆኑ ሲታሰብ ደግሞ የስጋቱን ዙር ያክረዋል። እናቱ ግን የንግስና ዘመኑን ዕድሜ ነግረውት ይሆን? እሱን ማወቅ ተስፋ ሊሆነን ይችላል። …ልጅ ሆነን፣ ኢሳያስ አፈወርቂ በሞተር ሳይክል ሄዱ፣ ከሕዝብ ጋር ፓስቲ ጠብሰው በሉ፣ አጋጭተው ጨበሱ፣ ከአብሯደጋቸው ጓዳቸው ጋ አንጓ በድንጋይ ፈንክተው ጋጡ ዓይነት ወሬዎችን ስንሰማ፣ አፋችንን ከፍተን በቅናት እናርር የነበረው ሁሉ አሁን ትዝ አለኝ።)
 
ያም ሆነ ይህ፥ ሰዉ በደቦ ሆ ብሎ ወጣ። ካናቴራው ተለበሰ፣ ተጮኸ፣ ባንዲራው በየቀለሙ ወጣ! አይናችን እያየ ጠላት አይኑ ደም ለበሰ። አብዮት ጥበቃው ተጠናክሮ ቀጠለ! እሱም በመናገር ላይ ነው።
 
በድግሱ ማግስት፥ ሁላችንም አብዮት ጠባቂዎች ነን እንዳላልን፣ የተሻልን የቅርብ አብዮት ጠባቂዎች ነን የሚሉ ከእግር እግር እየተከተሉ አላናግር አሉን። መንግስት ሲባል፥ “አብይን አትናገሩት” ይላሉ። የህግ የበላይነት ሲባል፥ “አብይን ለቀቅ” ይላሉ። ህዝብ አለቀ ሲባል፤ “የወያኔ መጠቀሚያ አትሁኑ” ይላሉ። ይህቺ ናት ጨዋታ! ይህቺ ናት አብዮት ጥበቃ!
 
“ከጌዲኦ ከ8 መቶ ሺ ሰው በላይ ተፈናቀለ” ሲባል፥ የአብይ ስም ምን እንደሚሰራ አላውቅም። “አብይን አትተቹ፤ ጊዜ ስጡት” ይሉናል። “ከጎኑ ቁሙ” ይሉናል። ከዚህ በላይ ከጎን መቆም አለ? (ነገሩ እናንተ እና እኛ መባሉም ያበግናል) እንግዲህ እግዜርም ሰይጣንም እንደሚያውቁት፣ አብይን ሁላችንም ልብ ውስጥ ጉዝጉዝ ብሎ ገብቷል። እንወደዋለን።
 
(በበኩሌ፥ ፓርላማ ላይ በሀቅ ወቅት (moment of truth) በተናገረው ንግግሩ ብቻ፣ ከእንግዲህ ምንም ቢያደርግ በማይነቃነቅ መልኩ ልቤ ውስጥ ቦታ አግኝቷል። “እስካሁን ምን ነክቶት፣ እንዴት ችሎ ነበር ከነሱ ጋር የቆየው?” እንዳልኩ ሁሉ፣ “ምን ነካውና እንዲህ ሆነ” እል ይሆናል እንጂ በፍጹም አልረሳውም።)
 
አብይን መውደድ ግን እውነትን እንዲጋርድብኝ አልፈልግም። አብይን መውደድ፣ ረዳት አጥቶ በክረምት ከቤቱ የተፈናቀለን ሰው ለቅሶ ባላየ/ባልሰማ ማለፍ አልፈልግም። ገና ለገና አብዮት አይጠበቅም ብዬ ሕዝብ ላይ መጨከን አይሆንልኝም። ለአብዮት ጥበቃ የሚደረጉ ነገሮች ጎጂነትንም በታሪክ የማውቀው ነውና፣ በአብዮት ጥበቃ ስም፣ ህሊናዬን ማቁሰል አልፈልግም። ሁላችንም ቆም ብለን ማሰብ ያለብን ጉዳይ ነው።
 
ኢህአዴግ ከአእምሮ በላይ በሆነ መልኩ፣ በማይታመን ሁኔታ፣ በአረመኔነት ግብሩ የተጫወተባቸው ሰዎች ሰቆቃ በገዛ በኢህአዴግ ቲቪ ነው የሚቀርበውና የምናየው። ተሳታፊዎቹ በተናጥል፣ ድርጅቱ እንደአሸባሪ ድርጅትነቱ መጠየቅም አለበት። ጭራሽ ይህን ሁሉ በደል አድርሰውባቸው፣ በመንግስት ይቅርባይነት/ምህረት ነው የተፈታችሁት ሲባል ያበሽቃል።
 
ትናትንና “ኸከሌ ታሰረ” ሲባል “አርፈው አይቀመጡም ነበር፤ ሳይነካኩማ አይሆንም” ያልን፣ የመብት ጥሰቶችን ያዩ ሰዎች ሲያሰሙን “እንደዚህማ አይደረግም፤ ተጋነነ” ስንል የነበርን “አርፋችሁ ተቀመጡ። አትጻፉ” ያልን ሁሉ በራሳችን ፊት ልናፍር እና ንስሃ ልንገባ ይገባናል። ይህን የፈጸሙ፣ ያስፈጸሙ፣ አቅም እያላቸው ሲፈጸም አይተው ዝም ያሉ ሁሉ በይቅርታ ሊታለፉ ቀርቶ፣ በህግ ሊጠየቁ ይገባቸዋል።
 
እፈራለሁም፥ አብዮት ጠባቂነታችን እና የአብዮት ጥበቃው ፍላጎታችን፣ የዶ/ር አብይን መንግስት አምባገነንነት ገና በአፍላነት እንዳያደርገው።
 
የለውጥ ሳይሆን፣ የጭካኔ እና የፍርሃት ስርወ መንግስቱን (fear regime) አጠናክሮ የማስቀጠል ዓላማ ያለው ከሆነ፥ አብዮቱ ፍግም ይበል። ካልሆነ ደግሞ፣ በአስተያየቶች ይጠናከራል፣ ደካማ ጎኑን ፈትሾ ይበረታል እንጂ፣ በትችት እና በጥያቄ፣ በድረሱልኝ ጩኸት የተነሳ ምንም አይሆንም። በአስተያየት የሚበላሽ ከሆነ ግን፣ ችግሩ ከተፈጥሮው ነው እንጂ ከአስተያየቱ አይደለም!
 
እግዚአብሔር አገራችንን ይጠብቅ! ለመሪዎቹም ለተመሪዎቹም ልቡና ይስጠን!

ዋና ጠላቶቻችን ወዳጆቻችን ናቸው!

ወዳጆቻችን በፍቅር ስም ከነነውራችን፣ ከነጉድፎቻችን እንድንኖር ይፈርዱብናል። ሰው ግድ ሰጥቶትም ሆነ፣ በተፈጥሮው የመመልከት እና የመተቸት ዝንባሌ ኖሮት አስተያየት ሲሰጥ፣ “ቅናት፣ ጥላሸት፣ ምቀኝነት” የመሳሰሉ ኮተቶች ተጠቅመን ስም በመስጠት ዝም እንዲል እናሸማቅቀዋለን። “እሽ እሽ” እንላለን። ሁነኛ ወዳጆችን ሁሉ እናሳጣለን።
 
የወደድነው ሰው የተነቀፈ ስለመሰለን ብቻ ፍቅራችን ተንጣፎ ያልቅ፣ የዚያም ሰው የአገልግሎት ዘመን ያከትም እናስመስለዋለን። ‘ምናልባት ቢፈተን ይወድቃል’ የሚል የምንወደውን ሰው አቅም የመናቅ እና፣ ብቃቱን የማቃለል ቅድመ ስጋት ስለሚያድርብን፣ በተወዳጁ ሰው ዙሪያ የሚኖር የተለየ ንግግር ሁሉ የጠላት ድምጽ ይመስለናል። በዚህ ባህርያችን የተነሳም፣ ለምንወደው ሰው ውዳሴ እንኳን ተጽፎ ካልተረዳነው፣ አፋፍ ለማለት እና አትንኩት ለማለት እንሽቀዳደማለን።
 
በተለየ ዐይን ተመልክቶ አስተያየት የሚሰጠው ወይም የሚተቸው ሰው “ምን ቸገረኝ” ብሎ ነገር ዓለሙን ቢተወው፣ እኛ የምንወደው ሰው ስላልተተቸ ደስ ይለናል፤ ለጊዜው አሸንፊ መስለን እንረጋጋለን። ነገር ግን፥ የምንወደው ሰው ማግኘት ሲገባው ባሳጣነው ትችት የተነሳ፣ መገንባት የሚችለውን ያህል ላይገነባ፣ ወይም ባለበት ቁመና ጸንቶ ላይቆይ ይችላል። በአሳዛኝ ሁኔታ ግን፥ ወዳጆች በውድቀት ተባባሪነት ሲጠቀሱ እና ሲወቀሱ አይታይም። ልብ ብለን ካጤንነው፥ ከተኮፈሰ እኔነት (ego) ቀጥሎ፥ ዋና ጠላቶቻችን ወዳጆቻችን ናቸው።
 
ለምሳሌ፥ በጣም የተወደደን ሙዚቀኛ የሚተቹ ሰዎችን ገፍተን ጠላት እናደርጋቸዋለን። የትችታቸውን መሰረት መርምሮ ከመሟገት ይልቅ፣ በጠላትነት ኩታ ጠቅልለን ዳር ለማስያዝ እንጥራለን። በዚህም የተነሳ፣ የተወዳጁን ሙዚቀኛ ተሳትፎ በእኛ የኑሮ ክልል እና ማዕቀፍ ብቻ እንወስነዋለን። በዓለም መድረክ፣ በብዙ ቋንቋ ተናጋሪዎች ዘንድ ሳይቀር መታወቅ እና መወደድ የመቻሉን ነገር ከስር እናስቀርበታለን።
 
ከዚህ በላይ ጠላትነት ከወዴት ይመጣል?
ከጠላት ክፉስ የወዳጅ ጠላት፣
‘አትንኩት’ ብሎ፣
ያፈቀረ ሰው… ያገዘ መስሎ፥
ትጋት እድገትን የትም ‘ሚጥላት
ዕንደጠባቂ ከአዳኝ ‘ሚያስጥላት!
 
/ዮሐንስ ሞላ/
 

…ዝናሽ ለምን ተሰደደች?

“እንደምን ነሽ ሸገር
የእነ ሮቤል ኪሮስ፣ የኮካዎች አገር”

ካለነገር አይደለም ሮቤልን (aka the whale) ጠቅሼ ነገሬን መጀመሬ። ስለስፖርት እና ስለዓለም አቀፍ ውድድሮች ውክልና ሲወራ፥ ያለውን የተበላሸ አሰራር መልክ በሱ ልክ ለዓለም ያሳየ የለምና ነው። ያው ኮካ ኮካ ነው። ድራሹ ይጥፋ!

ሰበቤ ደግሞ ፈረንሳይ ውስጥ በምትኖርበት አፓርትመንት ውስጥ በኤርትራዊ ወጣት በትራስ ታፍና፣ በተሸለመችው ዋንጫ ጭንቅላቷን ተመትታ የሞተችው የ27 ዓመቷ ኢትዮጵያዊት ዝናሽ ገዝሙ ናት። ሞቷ/አሟሟቷ እጅግ በጣም ያንገበግባል። 😥 ነፍሷን ይማረው! ለቤተሰቦቿም መጽናናት ይኹን!

ግን ለምን ተሰደደች?? እሷ ብቻ ሳትሆንም ብዙ አትሌቶች ለምን ተሰደዱ/ይሰደዳሉ? አሸንፈው በቴሌቪዥን እስኪታዩ ድረስስ እንዲህ ባለ ውጣ ውረድ ውስጥ እንደሚያልፉ ስንቶቻችን አስበነው እናውቃለን? አገር ውስጥም በሶ መበጥበጫ ካቅሙ ብርቅ ሆኖባቸው በታጠፈ አንጀት ልምምድ የሚያደርጉ ስንት ተስፈኛ ወጣቶች አሉ!? እንደዜጋ ቢቀር፥ መንግስት እንደ ኢንቨስትመንት ቆጥሮት፥ ከድሀው ሕዝብ የተሰበሰበውን፣ ከገደላ ገደሉ ቀፈቴ ቆንጥሬ እንዴት “ቀለብ ልስፈርላቸው” አይልም?

24129742_2033573766659094_7074890654497629838_n.jpg

 

(ሌላ ሞያ ላይ ያሉትን ዜጎች ትቼ ስለአትሌቶቹ መጠየቄ፥ ዕድሉን ካገኙ፣ የልፋታቸው ውጤት የትም ተሁኖ በንጹህ ላብ የተጠራቀመ ጠቀም ያለ ገንዘብ፣ ክብርና ዝና መሆኑ ስለሚታወቅ ነው። እንዲህ ያሉ ለሀገር ሀብትም፣ ክብርም መሆን የሚችሉ ብርቅዬዎች፥ የውጭው በር የሚከፈትላቸው የውስጡ በር እንዴት እንዴት ተዘግቶባቸው ውጭ ውጭ ቢያሳያቸው ይሆን? ብዬ ነው።)

በርግጥ እንደ ፈይሳ ሌሊሳ ያሉ ግልጽ በሆነ ፖለቲካዊ አመለካከታቸው የተነሳ የሚሰደዱ አሉ። አብዛኞቹ ግን ችሎታ እያላቸው፥ ዘመድ ስለሌላቸው ውድድሮች ላይ የመሳተፍ በሮች እየተዘጉባቸው እንደሆነ ይፋዊ በሆነ መልኩ ባይሆንም በገደምዳሜ ይሰማል። ሯጮቹ ገጽታ ላይም የሚታይበት አጋጣሚ ብዙ ነው። በተለይ ውድድሮችን አሸንፈው ለሽልማት ሲበቁ የሚጎርፈው እንባቸው ዝም ብሎ የደስታ ብቻ አይመስለኝም።

ከጀርባ የነበረው መገፋት እና ትግል፣ ልፋትና ጥረት ሁሉ ተደራርቦ ድል ማድረግ እንደ ደራሽ ወንዝ የሚፈጥረውና፣ ቁጭት የሚያባብሰው ይመስለኛል። (የመሰረትን የለንደን ኦሎምፒክ ዕንባ ያስታውሷል።) ከጥረታቸውና ልፋታቸው ጎን ለጎን ደራርቱና እልፍነሽ ቀድመው ከቤተሰቡ ባይኖሩ ኖሮ ገንዘቤ እና ጥሩነሽን የመሰሉ ብርቆች ላናውቃቸው፣ ወይም ደግሞ ተሰደው የሰው አገር ጌጦች ሆነው ልናውቃቸው… በነሱ ምትክ ደግሞ ቦርጫም ሯጮች ልናይ እንችል እንደነበር አስበነው እናውቃለን?

ግን ዝናሽ ለምን ተሰደደች??

ዝናሽ በዋናነት፥ ለመኖር እና፣ ወላጅ እናቷን ለመጦር ተስፋ ያደረገችው አትሌቲክሱን እንደነበርና፥ የአትሌቲክስ ልምምዷን ላለማቋረጥ እና፣ እሳቸውንም ለመደገፍ በሳምንት እስከ 270 ዶላር ድረስ የምታገኝበትን ሆቴል የማጽዳት ሥራ እየሰራች፣ ከሌሊቱ 11 ሰዓት እየተነሳች ሥራ ከመሄዷ ቀድማ፣ እንዲሁም ምሽት ከሥራ ስትመለስ ጧትና ማታ ልምምድ ታደርግ እንደነበርና፥ ይኽ ጥረቷ እና ጥንካሬዋም ቡድኗ ውስጥ ከነበሩ በርካታ አትሌቶች ለየት እንደሚያደርጋት ጠቅሶ ስለልዩ ጥንካሬዋ የቀድሞ አሰልጣኟ ኒኮላስ ቫላት ተናግሯል።

አትሌት ኃይሌ ገ/ሥላሴ በጀርመን ድምጽ ሬድዮ ላይ በሙስና እና የዘመድ አሰራር ዙሪያ ተጠይቆ ሲናገር “የዝምድናው፣ የሙስናው፣ የመሳሰሉት በየትም ቦታ አሉ፤ ግን ልዩ የሚያደርገው በስፖርቱ የምታየው ሙስና እና የዝምድና የመሳሰሉት ነገር ሜዳ ላይ ቁልጭ ብሎ ለሚሊዮኖች ይታያል። ያ ደግሞ ያጋልጥኻል ማለት ነው። ምንም የፖሊስ ምርመራ ሳያስፈልገው የሚጋለጥ ነገር ነው። እኔ የምጥረው ያ እንዳይኾን ነው።” ማለቱም ይታወሳል።

እንግዲህ እሱ ከውስጥ ሆኖ በዚህ ደረጃ ከገለጸው፥ በውጭ ያለነው ሰዎች ስለአትሌቶች ስደት ሲወራ፣ እንደ ዋና ምክንያት የአሰራሩ ብልሹነት ነው ብንል ልክ አይደላችሁም አንባልም ማለት ነው።

ሆኖም “ሞተች” የተባለችን ምስኪን “ለምን ተሰደደች?” ብሎ መጠየቁ፥ ሌሎች የሞያ አጋርና እኩዮቿ እንዲጠበቁ ጥሪም ጭምር ነውና፥ በእሷ ሞት የተነሳ አንድ እንኳን ተስፋ ያለው አትሌት፣ አገሩ ላይ ተለማምዶ አገሩን ወክሎ መወዳደር እየፈለገና እየቻለ፥ ባለጊዜ ካለመሆን የተነሳ ብቻ ዕድል እንዳይነፈገው ቢቻል፣ ለከርታታ ነፍሷም ጥሩ እረፍት ይሆን ይመስለኛል። መታሰቢያዋም ሁሌ ይኖራል።
.
.
ከልፋቷ ለማረፍ ላይ ታች ስትል መቀጨቷ ያሳዝናል። እግዚአብሔር ነፍሷን ይማረው። ለቤተሰቦቿም መጽናናት ይስጥ። አገዳደሏም በጣም ያሳዝናል። ገዳይዋም ተገቢውን ፍርድ እንደሚያገኝ እናምናለን። ዝናሽ በዋናነት የማራቶን ሯጭ ብትሆንም፥ በ10ሺ፣ ግማሽ ማራቶን እና ሌሎች የቤት ውስጥ ውድድሮች ፈረንሳይ ውስጥ ብዙ ጊዜ ማሸነፏ ተገልጿል።

ነፍሷ በሰላም ትረፍ!

ልደ ቱ!

23519141_2009666822383122_4032006682889241508_nጋሽ ስብሀትን አንድ ጋዜጠኛ
“ከቅርብ ጊዜ ዘፋኞች የምትወደው” ሲለው
“ይኼ ነይልኝ…የሚለው ልጅ ይመቸኛል“
ጋዜጠኛው ቀጠል አድርጎ
“የማይመችህስ ዘፋኝ?” ሲለው
“ከእሱ እየተቀበለ “ነይለት” የሚለው አቃጣሪ” አለው አሉ።

ይኼን ያስታወስኩት ዮሴፍ ገብሬ (ጆሲ) እና ያ ቀልማዳ ልደቱ አያሌው ያወሩትን ዞር ዞር ብዬ ተመልክቼው፥ አንዴ ጆሲን፣ አንዴ ልደቱን እያልኩ መመዘኑ ሰለቸኝና ነው።

ቃለ መጠይቁ ሲጀምር እና “የፍቅር እስከ መቃብር ደራሲ ማነው?” በሚል ጥያቄ ነው። ተመልካቾች በ2 ብር (?) የጽሁፍ መልእክት ሰዎች ምላሽ እንዲሰጡና፣ ከመካከላቸው አንዱ ስጦታ እንደሚበረከትለት ይገልጻል። ማስታወቂያው በየመሀሉም ለብዙ ጊዜ ይደጋገማል። የመጀመሪያው መላሽ ለሚሸለም ያን ያህል መደጋገሙስ ለምን አስፈለገ? ማለቴ አልቀረም። በሁለተኛው ክፍል ደግሞ ጥያቄው “ይኽች አርቲስት ማን ትባላለች” ብሎ የእንግዳዘርን ምስል ነው የሚያሳየው።

ብቻ ሕዝቤ በነፍስ ወከፍ ሁለት ሁለት ብሯን አዋጥታ ታበረክታለች። ይመቻቸው!

የመጽሐፍ ነገር ሲነሳ፥ የሁለተኛ ዓመት ተማሪ ሳለው መምህሬ የነበረና፣ አሁን የቅርብ ወዳጄና አማካሪዬ ጋር ከሳምንታት በፊት ስናወራ በጨዋታ መሀል ያነሳብኝ ነገር ትዝ አለኝ።

ከወዳጄ ጋር የነበረን ጨዋታ፥ እንደአገር ስላለመታደላችን፣ ይኽ ነገር የሚቆምበት ጊዜ እንደሚናፍቀን፣ እንዲሁም ድርሻችንን ለመወጣት በየዙሪያችን ራስን ከመለወጥ አንስቶ መሞከር እንጂ፥ የሚታይ የሚሰማው ነገር ሁሉ ተስፋ አስቆራጭ ስለመሆኑ ነበር። ነገርን ነገር አንስቶት ወዳጄ ጆሲን አስታወሰው።

“በጣም ነው የሚያሳዝነው። የሚዲያ ባለቤት እንኳን ለእፍረት ብሎ ስለንባብ የሚገነባ ነገር አያወራም።

አሁን ባለፈው ጆሲ የሚሉት ልጅ ከአንድ ሌላ ጋዜጠኛ ጋር ያወራል። ጋዜጠኛው “መጽሐፍ ታነባለህ ወይ?” ብሎ ይጠይቀዋል።

“አሁን አላነብም። ድሮ ግን አነብ ነበር።” አለው ኮራ ብሎ።

“እስኪ ድሮ ካነበብካቸው መጽሐፍት ያንዱን ርዕስ ንገረን” ሲለው፥

“አሁን ትዝ አይለኝም።” አለው።

ምናለ የአንዱን መጽሐፍ ርዕስ እንኳን ቢጠራ? ቢቀር ፍቅር እስከ መቃብር አይልም ሰው? እንግዲህ ይኽ የሚዲያ ባለቤት፣ ጋዜጠኛ እና ዘፋኝ ነኝ የሚል ሰው ነው። ሌላውን ደግሞ አስበው።” ተባባለን፣ መዓዛ ብሩን አወድሰን አለፍን። (ባይጠቅመኝም ሌላ ቃለ መጠይቁን የሰማ፥ ወይ ከማን ጋ እንደሆነ የሚያስታውስ ካለ ቢነግረኝ እና ብሰማው ደስ ይለኛል።)

መዓዛ ብሩን ስናወሳ ስለእንግዶቿ ያላትን ጥልቅ እውቀት እና፣ ስለሰሩት ነገር ለማወቅ ጥናት/ምርምር ስለማድረጓም ጭምር ነው።

ይኽን ማንሳቴ ደግሞ ጆሲ ስለእንግዳው እንዴት ጥናት አያደርግም? ቢያንስ ከጻፋቸው መጽሐፍት አንዱን በወፍ በረር ቃኝቶ ማውራት ቢቀር፥ እንዴት ስለመጽሐፎቹ እሱ እንዲናገር እንኳን የመጽሐፉን ወሬ አያነሳበትም?

ጭራሽ ስለመጽሐፍና ንባብ፣ ስለጻፈው ልብወለድ ሲያነሳበት ሁሉ፥ የጆሲ ልብ ፔጆዋ ላይ ነው ጆፌ ብላ የቀረችው።

ብቻ ያው ነው።

ጆሲ “ሰማሁ… አሉ…”

ልደቱ “አልኩ… አደረግኩ… እኔ መሲሁ ነኝ። ልወደድ አልልም። ሕዝቡ ይወደዋል አይወደውም አልልም። እኔ ካመንኩበት እናገረዋለሁ።”

ያው መበጣረቅ ነው!

ሕዝብ ካልወደደው ለአገር ምኑን ጠቀመ? “አገር ማለት ሰው ነው” እንደሚባል አያውቅም ማለት ነው? ለነገሩ፥ ቤቴ ውስጥ ይሉኝታ ያጠቃኛል። በፖለቲካ ግን ይሉኝታ አላውቅም ብሎ ነገሩን ሲጀምር ነበር ማቆም የነበረብኝ።

የተቸገርነው እኮ አገሪቱን እንደቤታቸው አላከብር እያሉን ነው። ሕዝቡን እንደወገናቸው አልቆጥር እያሉን ነው።

ይኽን ስጽፍ ፌስቡክ “የዛሬ ዓመት ምን ብለህ ነበር” ቢለኝ ጥሩ ነው?

እንደው… የሞት የሽረት “ግድ መምረጥ አለብህ” ብባል፥ አይደለም ከሌላ ሌላው…

“መለስ ዜናዊ ከልደቱ አያሌው ብዙ ጊዜ ይሻለኛል!” እላለሁ! Period! ብለህ ነበር ይለኛል።

ምድረ አተቲያም፥ “የአረም እርሻ” ገበሬ! ጆሲን ግን ጥሩ ለጎም ለጎም፣ ጎተት ጎተት አድርጓታል። ሃሃሃ…

እኔማ ከ1992 ዓ/ም (ለመጀመሪያ ጊዜ ቲቪ ላይ ካየሁት ጊዜ) “ሆኜ፣ ተደርጌ” ሲል ሰምቼው እንደቀፈፈኝና ቀልማዳነቱ ብቻ እንደሚታየኝ አለ። He is one of the persons/things that time and time prove my instinct right.

ሃሌሉያ!

ንጽጽር ይሸክከኛል!

ሀበሻን ሁሉ አይቶ የጨረሰ፣ ፈረንጅን መርምሮ ደህናነቱን ለክቶ ያወቀ ይመስል፥ “ውይ ከሀበሻ ጋር! …ሀበሻ ክፉ ነው! …ከሀበሻ ጋርማ በሩቁ ነው!” ምናምን እያሉ ራስ ሀበሻ ሁነው ሳለ በራስ ላይ መሳለቅ ያሳቅቃል። ሀበሻንም ሆነ ፈረንጅን፥ ማን አይቶ ጨርሶት ነው?
* * *
አንዲት ምስኪን ኢትዮጵያዊት እናትን፣ ከአንዲት ፈረንጅ እናት ጋር አንድ ላይ አድርጎ፥ ከላይ ‘ልጅ ብርጭቆ ሲሰብር’ የሚል ጽሁፍ ከላይ አስፍሮ:
 
Foreign mom: “Son, are you okay??” ትላለች፥
ኢትዮጵያዊቷ ደግሞ “አንተ ከይሲ ብርጭቆው ተረፈ??” ትላለች ተብሎ የቀረበ ለዛዛ የፌስቡክ ፖስተር አለ።
 
ምስሉ ላይ ሲታይ፥ የውጭ አገሪቱ እናት ደንግጣ፣ ኢትዮጵያዊቷ እናት ደግሞ ዘና ብላ እንደተናገሩ ሆኖ ነው የቀረበው።
 
በርግጥ ያስቃል። ግን ያሳቅቃል። “አቦ አታካብዳ” የሚለው ብዙ ነው። ግን አልችልም። ወግ አጥባቂ አለመሆን የማልችልባቸው ጉዳዮች አሉ!
 
ኢትዮጵያዊ እናቶች ሲሉን የምናስታውሰው ነገር ስለሆነ፣ ኢትዮጵያዊቷ አለች ተብሎ የቀረበው ካለምንም ንጽጽር እና አጀብ ብቻውንም ቢቀርብ፣ የብዙ ሰው ትዝታ ነውና የማሳቅ አቅም አያንሰውም። በንጽጽር ሲቀርብ ግን ‘foreign mom’ ለተባሉት (ከኢትዮጵያውያን ውጭ ላሉ እናቶች በሙሉ) የተሻለ የተንከባካቢነት፣ ለልጅ አዛኝነት እና ሰብዓዊነት ካባ እያላበሰ፥ ለኢትዮጵያውያን እናቶች ደግሞ ግድ የለሽ እንደሆኑ ያስመስላል። ይሸክካል!
 
ማሳቁ ብቻውን ጋርዶን እንዲህ ያሉ አደገኛ ድንጋዮችን በራሳችን ላይ የምንወረውር ከሆነ “ስም ይወጣል ከቤት ይከተል ጎረቤት”ን እንተርታለን እንጂ ምንም አናመጣም። በበኩሌ፥ ይህንን ቀልድ ለአንድ ነጭ ወዳጄ ከማስረዳ፣ ዲዳ ብሆን እመርጣለሁ።
 
ማነው the so called ‘foreign moms’ን አይቶ የጨረሰ እና ከልጆቻቸው ጋር የነበራቸውን ግንኙነት የሰማ/የፈተሸ? እናቶቻችንስ ቢሆኑ፥ በእኛ ፊት እንጂ፣ በዓለም ፊት እና በልባቸው ባላሉት ነገር ከሌላ ጋር ተመዝነው ለቀልድ ሲውሉ አይከብድም? ልብ አርጉ፥ አያስቅም አላልኩም። ያሳቅቃል እንጂ!
 
“አያ በሬ ሆይ
ሳሩን አየህና ገደሉን ሳታይ” ነው የሚተረትብን፥ ከእኛው ለእኛው!
 
በዚህ “ምን ታካብዳለህ?” የሚለኝ ቢኖር፥ ብሔር ላይ የተቀለዱ ቀልዶችስ ያስቃሉ እና ብንቀባበላቸው፣ ብንለጥፋቸው ምን ችግር አለው ታዲያ የሚል ጥያቄ አለኝ። አንዲት ኢትዮጵያዊት እናትን ከሌላ እናት ጋር አነጻጽረን መቀለድ ሞራላችን ከፈቀደ፣ አንዱን ብሔር ከሌላው፣ አንዱን ሀይማኖት ከሌላው ጋር ለማድረግስ ታዲያ ለምንድን ነው ሞራላችን የማይፈቅደው?
* * *
ዓለማቀፍ ዝና ያለው ሰው ሲሞት ጠብቆ፥ በረሀብ ከተጠቁ ህጻናት ፎቶ ጋር አድርጎ፥ “ሚሊዮኖች ሲሞቱ ማንም አላለቀሰም፣ 1 ሰው ሲሞት ዓለም አለቀሰ” ብሎ ትዝብት ሲለጠፍ ይጨንቀኛል። ያሳክከኛል። ሰውን ከመርዳት ይልቅ ይበልጥ ጨካኝ ያደርገዋል እላለሁ። የተራቡት ትዝ እንዲሉን ታዋቂ ሰው መሞት ነበረበት? ለምን የሰዎችን ኀዘን እንቀማለን?
* * *
አንድ ሰው በቅንጡ ሰርግ ሲጋባ፥ “ለምን ድሀ አይረዳበትም ነበር?” ብሎ ንጽጽር ይበላኛል። ድሀ መርዳት እንዳለ ሰው በውድ ሰርግ ሲያገባ ትዝ የሚለን ጉዳይ ነው? ለምንስ የሰውን ደስታ እንቀማለን?
* * *
“ተክሉ የተባለ ሳክስፎኒስት ለአሸናፊ ከበደ ገቢ ማሰባሰቢያ በተደረገ የሙዚቃ ዝግጅት ላይ፥ ሁሉም በነጻ ሲሰሩ እሱ ግን አሸናፊን ከማንም በላይ እየቀረበው፥ 200 ብር ተቀበለ። ሆዳም ነው። እንዲህ ነው፣ እንዲያ ነው። ኅሊናው ይፍረደው።”
 
ብሎ ከሌሎች ጋር በንጽጽር አውርቶ፣ አንድን ባለሞያ ወደሞያው ለመመለስ በተደረገ ዝግጅት ላይ፣ ሌላኛውን ባለሞያ ከሞያው መግፋት ያሳስባል። አንድን ሰው ለመርዳት ተብሎ ሌላን ሰው አደጋ ላይ የሚጥል ስርዓት ለምን እንፈጥራለን? እሱ ያለበትን ወጪ እና የኑሮ ስንክሳር ያውቃልና ለሰራበት ስራ ከተከፈለው በኋላ ስም ማንሳት ለምን ያስፈልጋል?
 
አሸናፊ ከበደ ጥሩ ድምጽ እና ችሎታ እያለሁ፣ መስራት ባለመቻሉ ምክንያት እርዳታ እየተሰበሰበለት ነው። ተክሉም ቢሆን ሳክስፎኒስት ስለሆነ ብቻ እና ቆሞ ስለሄደ ስላለበት የኑሮ ጫና መናገር አይቻልም። አልሰረቀም ይኼ ልጅ፣ ወሰደ ማለትን ምን አመጣው? የገንዘብ ችግር እንደሌለበትም ተፍተፍ ሲል ስላየን ብቻ መፍረድ አንችልም። ያለበት የሕይወት ጣጣ (commitments) ይኖራሉ።
 
ያንን እንዳያደርግ ያስቻለውን ምክንያት ራሱ ብቻ ነው የሚያውቀው። እነኧከሌ በነጻ ስለሰሩ እሱም በነጻ አልሰራም ብሎ እያነጻጸሩ መዝለፍ ያስጨንቃል።
 
ነገሮች ስለሚነጻጸሩ ብቻ ሳይሆን፣ የመነጻጸራቸውን አስፈላጊነት በማወቅ ብናነጻጽር ይሻላል እላለሁ!
 

ሱስቆት…

facebook1ፌስቡክ ከናፍቆት መወጣጫ፣ ከመረጃ መለዋወጫ እና ከድድ ማስጫ ተግባሩ ጋር ፍቅር አስይዞን፣ ዞር ሲሉ ናፍቆት ቢጤ እየወዘወዘንና ቢያስመስለውም፣ ነገሩ ከፍቅር እና ናፍቆት በራቀ መልኩ ሱስ መሆኑ ሲሰማኝና፣ ችግሩን ለመቅረፍ መለማመድ እንዳለብኝ ወስኜ የነበረ ቢሆንም ቅሉ፥ እስኪ ይህንን “ልጻፍ እስኪ” ብዬ ፌስቡክ ላይ ለመቆየት ጥሩ መላ ዘየድኩኝ። ይህን ጽፌም ላሽ ብል ኖሮ፥ ጥሩ! ግን የስራው ጸባይ፥ ተመላልሶ አስተያየት ማንበብንና፣ ባለጌዎችን እያሳደዱ ማስወገድም ያካትታልና መክረማችን ነው። ሄሄሄ…
 
ሰሞኑን አገር ቤት ኢንተርኔት ከመቋረጡ ጋር ተያይዞ፥ ወዳጆች የፌስቡክ እና የሌሎች ማኅበራዊ ድረ ገጾች “ናፍቆት” እንዴት እንዴት እንዳደረጋቸው እያየን ነው። እኔም “መቼም የሸገር ጓዶቼ በሰፊው ብትን ያላሉበት ፌስቡክስ ቢቀር ይሻላል” ብዬ፥ ከፌስቡክ ለመራቅ ያደረግኩት ሙከራ ባጭሩ ሲከሽፍብኝና፣ ጣቴን እየበላኝ በባዶ ሜዳም… “ሄድኩ” ስል ስመለስ ከራሴ ጋር እየተሳሳቅኹኝም
 
“ኧረ ይኼ ነገር የከፋ ሳይሆን አልቀረም።” ብዬ “ከፌስቡክ ሱስ መላቀቂያ መንገዶች”ን በመፈለግ፣ በዚያውም ስለፌስቡክ እና ስለሱሱ ማንበብ ቀጠልኩ። (ሱስ የመሆኑ ብዛት፥ ሰው ሁሉ መጠቀም ቢያቆም እንኳን ብቻችንን መጥተን እንድናውደለድል የሚገፋፋን ስሜት አለ።) የሚገርመው ነገር ግን፥ መላቀቂያ መንገዶቹን እያነበብኩ ራሱ፣ በየመሀሉ ስንት ጊዜ ፌስቡኬን ቼክ እንዳደረግኩ እኔና እግዜሩ እናውቃለን። ሃሃሃ…
 
የተጠቆሙትን መንገዶች ሁሉ ሳነብ፥ በልጅነት “እስክሪብቶዬ የዛሬን ጻፊልኝ፣ ለነገ አስገዛለሁ” ብለን ቁልቁል ዘቅዝቀን እንደምናራግፋት፣ “ቆይ አሁን፣ ቆይ በኋላ፣ ቆይ ነገ” ስል፥ ባህሩ እሹሩሩ እያለኝ እንደሆነ በደንብ ገባኝ። “ወደ ሲዖል የሚወስዱ መንገዶች በማስተባበያ የተጠረጉ ናቸው።” (the road to hell is paved with excuses) እንዲል ፈረንጅ፥ ሳልቦዝን፥ ለማስተባበያዎቼ ሳይቀር ማስተባበያ ስፈልግ ቆየሁ።
 
በንባቤ መሀል “ድረ ገጾቹን ብሎክ ማድረግ” የሚል ጥቆማ ሳገኝ፥ “wow, this must be working” ብዬ blocksiteን ተጠቅሜ ብሎክ አደረግኩት። ችግሩ እየረሳሁት ብቅ ስል፥ አውቶ ፖፓፑ ሲያላግጥኝና ስስቅ ዋልኩ። ስቄም አላባራሁ። ከዚያም ቆይ የፌስቡክን ሱስ ለማስታመም እና ቀስ በቀስ ለመተው ብዬ፣ ተያያዥ ነገሮችን እያየሁ ለመቆየት ወሰንኩና፥ ‘how to unblock a site blocked by a blocksite’ ብዬ ፈለግኩና ማብሪያና ማጥፊያዋን (the switch) አገኘኋትና፥ ይኸው ቀጥታ ከመጠቀም በማብሪያና ማጥፊያ ወደመጠቀም ተዘዋውሬያለሁ።
 
“ሲጋራም ቢሆን ባንዴ ማቆም ጥሩ አይደለም። ከፓኬት ወደ 10፣ ከ10 ወደ 5 ነው” የሚሉትን አስታውሼ፥ ብሎክሳይቷን በፈረቃ አብቃቅቼ ለመጠቀም ወሰንኩና “ቆይ የዛሬን” ብዬ off አደረግኩት። 🙂
 
ታሪኩ በአጭሩ ሲነገር፥
 
“አልሆንልህ አለኝ እጄ፥
እናንተን ጥዬ ሄጄ
ጉድ ብሆንስ አብጄ” ነው (በ“አልሆንልህ አለኝ እግሬ” ዜማ)
 
እያጨስን ነው ወዳጄ! ፈተናው ከባድ ነው! እየተጨሰብን ነው!
 
ለአፍታ ዞር ስል፣ መንግስት ተገልብጦ፣ ጓደኞቼ ተድረው፣ የማይዳሩት ፂማቸውን ላጭተው ጨርሰው ቆዳቸውን ጨርሰው፣ ሰማዩ ዝቅ ብሎ፣ ምድሩ ከፍ ብሎ፣ የሆኑ የሆኑ ዓይነት ብርቅዬ እና ድንቅዬ እንስሳዎች ተፈጥረው… የሚጠብቀኝ፣ ዓለም የሚያልፈኝ እየመሰለኝ ያለበት ሁኔታ ነው ያለው። ሃሃሃ… ሰሞኑን በኢንተርኔት መቋረጥ የተነሳ “ናፍቃችሁኝ ነበር” የምትሉትንም አንሰሜክስ ብለናል። ሱስ ነው፥ ታከሙት! 😀
 
እስኪ የዛሬውን በግጥም እንዝጋውና፥ “ካለፌስቡክ ስንት ቀን መኖር እንደሚቻል” እንፈትሽ! ሃሃሃ…
 
እትት እያስባለ ሲያናውዘኝ
የደረብኩለትን ማታ፣
በል አሁን ጣል ኩታ ሲለኝ
ከሙቀት ጋራ ሊፋታ፣
 
መስሎኝ የነበረ ናፍቆት
ነፋስ ሽቶ፣ ገላ ሞቆት፥
ላህብ አጥልቆ ወብቆት
 
ለካስ ኖሮ ከራስ ስርቆት፣
ለስራ ፈትነት ግምጃ
ለባተሌነት መጋረጃ፥
የተጠመቀ ደረቆት፣
የመራቋቆት ሱስ ቆት።
 
/ዮሐንስ ሞላ/
 
ቆት: በትግራይ ጨለቆት አውራጃ ውስጥ ይገኝ የነበረ/የሚገኝ ትልቅ ዛፍ ስም ሲሆን፣ በስልጥኛ ደግሞ “ኃይል” ማለት ነው።
 
ሰላም!