Category: ከእለታት በአንዱ ቀን…
የቀጠለ… (ከዴቪድ ጋር)
“ሴቶች አስቂኝ ናቸው”
ከአዲሱ ክፍል ተጋሪዬ ጋር
ከአዋላጅ ነርስ ወዳጄ ጋር ገጠመኝ
ከዚያስ…?
“እሺ፥ እንዴት ነው? ሁሉ ሰላም?” አልኩት አፍሪካ አሜሪካዊውን አዲስ ወዳጅ
“ማለት?” እኔ ከዝምታዬ ጋር ስደራደር፣ በሀሳብ ጭልጥ ብሎ ስለነበር ተደናግጦ ጠየቀኝ
“አይ፣ እንዲያው ሁሉ ሰላም ነው ወይ? ቤተሰብ? ኑሮ እንዴት እየወዘወዘህ ነው? ለማለት ያህል ነው።” ቀልጠፍ ብዬ በፈገግታ ታጅቤ መለስኩ። የምሸሸው ጭንቀት ስለነበረብኝ ዝምታውን አልፈለግኩትም።
“ኦህ፥ ሁሉም ሰላም። ሰላም ነው። …እሁድ የትልቁ ልጄ 29ኛ ዓመት ልደት ነበር።”
“እየቀለድክ መሆን አለበት። 29? አንተ ራስህ ከዚያ የምታልፍ አትመስልም እኮ።”
“አዎ። ሁለተኛዋ 26 ዓመቷ ነው።”
“በጣም ደስ ይላል። እጅግ በጣም ደስ የሚል ነገር ነው። ይኽኔ ከኮሌጅም ወጥተው ቦታ ቦታ ይዘውልሃላ…”
“አይ አይ! ቢሆን በምን ዕድሌ። ግን አይደለም። የቀድሞዋ ሚስቴ ዕድላቸውን መወሰን ነበረባት። ሲጥልብህ ልጆቿ ላይ ክፉ ፍርድ የምታሳልፍ እናት ጋር ያጋባሃል።”
“እንዴት ማለት? የማይሆን ርእስ ካነሳሁ ይቅርታ” ራሴን ስለቀለብላባነቴ እየወቀስኩ ጠየኩት።
“ግድየለም ኧረ። ….እናታቸው ከገንዘብ ጋር ያላት ቁርኝት እጅግ የተለየ ነበር። በእርሷ የብድር መክፈል ታሪክ የተነሳ ልጆቼ ብድር ማግኘት አይችሉም ነበርና ወደ ኮሌጅ አልሄዱም።”
“አዝናለሁ።”
“ተመስገን ነው። ይኽችኛዋን እናታቸውን ይወዷታል።”
“እንዴት? ከእሷ በኋላ አግብተሀል?”
“አዎ። ጥሩ ሰው ናት። 12 ዓመታት አብረን ቆየን።”
“ደስ ይላል። በተለይ ልጆች እንጀራ እናታቸውን ሲወዱ ማየቱም ያጽናናል።”
“በጣም። አፍሪካ አሜሪካዊት ናት እሷም። ግን ጀርመን ነው የተወለደችው። ያደገችው ደግሞ ጣልያን። ሆኖም ዓያቶቿ ከሜክሲኮ እና ስፔይን አሉ። ድብልቅልቅ ሲል ሆደ ሰፊነት ይጨምራል መሰለኝ።”
“ኦህ ደስ ይላል።”
“በጣም። ይገርምሀል፥ እኔ ቤተሰብ ውስጥ ስብጥሩ የተለየ ነው። አሜሪካ፣ አፍሪካ፣ ኢስካሞ፣ ፣ ብራዚል፣ ፣ ጀርመን፣ ኢትዮጵያ፣ ማሊ… የተባበሩት መንግስታት በለው” ብሎኝ አብረን ሳቅን።
“ኢትዮጵያዊም ቤተሰብ ካለህ እኔም ዘመድህ ነኝ ማለት ነው” አልኩት እንደጨዋታ።
“እንዴታ፥ የአጎቴ ልጅ ኢትዮጵያዊት በጉዲፈቻ ያሳድጋል።”
“አሃ…ደስ ይላል።”
“በጣም። ዓለም ላይ ካለው ሰላም የተሻለ እኛ ቤተሰብ ውስጥ ሰላም እንዲኖር እንሞክራለን።”
“ጥሩ አድርጋችኋል። ሰዉ ሰው ለመበደል ምክንያት ሲፈልግ ነው የሚመሽ የሚነጋለት።”
“አዎ። ሁሉም ጋ የዘረኝነት እና ሌላውን የመናቅ መንፈስ አለ። ሰው ለምን እንደዚህ እንደሚያደርግ አላውቅም። እናንተ ጋ አንድ ነው ብሄራችሁ?” አለኝ።
“ኧረ ብዙ ነን። 80 ምናምን ነን።” አልኩት። ምናምኗ ሁሌም ታስቀኛለች።
“ሰዉ ስለብሔሩ ብዙም ግድ አልነበረውም። ግፉም በጅምላ ነበር። አሁን ያለው መንግስት የዘውግ ፖለቲካ ስርዓት ነው የሚከተለው። በዚያ የተነሳ መታወቂያ ካርድ ላይ ሳይቀር ከመጻፍ ይጀምራል። በየቦታውም ሰዎች እርስበርሳቸው እንዲጋጩ በማድረግ ለራሳቸው እድሜ ይፈልጋሉ። እኛም ሞኝ ሆነን አጀንዳቸውን እንቀበላቸዋለን።” ብዬ ቀጠልኩ።
“ያው እንደሁሉም አፍሪካ መንግስታት ነው። ያሳዝናል።”
“በጣም”
“ይገርምሃል ባለቤቴ ከሜክሲኮም ትዛመዳለች ብዬህ የለ። እሷ ያለችው ሰሜኑ ክልል ላይ ነው። እዚያ የሀብታም እና የድሀ ስም በሚል ከባድ የሆነ የዘረኝነት ስሜት አለ። ሰዎች ስማቸው የድሀ ስለተባለ ብቻ ለጋብቻ እስከመከልከል ይደርሳሉ።”
“እየቀለድክ መሆን አለበት።”
“እንደዚያ ነው። እኔም በጣም ገርሞኝ ነበር። በጣም ይገርማል።”
“እንዴ በጣም እንጂ። ስም ሊቀየርም ይችላል እኮ። ቢያንስ ደግሞ አዲስ ለሚወለዱት ልጆች የሀብታም የተባለውን ስም በመስጠት ትውልድን ማቅናትም ይቻላል።” አልኩኝ።
“አዪ። እሱንማ አንተ ነህ የምታስበው። ትውልድ ስለማቅናት ቢያስቡ ቀድሞስ በስም ይጣሉ ነበር?”
“እሱስ ልክ ነህ።”
“ደግሞ አለልህ። ፊሊፒን ውስጥ በቁመታቸው ነው ጥቃት የሚፈጽሙት። አጭር ከሆንክ አለቀልህ። ትገለላለህ። ስራ ማግኘት አትችልም፣ ለጋብቻ አይፈቀድልህም፣ ብዙ ነው በደሉ።”
“ኧረ ሰውዬው እየቀለድከኝ ነው የሚሆነው።”
“እውነቴን ነው። ፈላልገህ ልታነብም ትችላለህ። ለማመን የሚከብድ ነው። ግን ያው እንደዚያው ነው። ሰዎች እርስ በርስ ለመበዳደል ሰበብ ነው የሚፈልጉት። በጾታ ለመበዳደል አላመች ሲል፣ በሀይማኖት፣ እሱ ሲያቅት በቆዳ፣ እሱም እምቢ ሲል በቁመትና በስም ሁሉ መበዳደል አለ።”
“በጣም የሚገርም ነገር ነው። ውስብስቦች ነን።”
“በጣም። እኔ በዚህ እድሜዬ የደረስኩበት ነገር ሁሉም ነገር ዝም ብሎ ተራ ሩጫ እንደሆነ ነው። የእኔ ወንድም ልንገርህ አይደል? ዝም ብለህ ኑር። ሕይወት ያሉህን መልካም ነገሮች ለማጣጣምም አጭር ናት። በፍጹም ሌላን ሰው ስለመናቅ አታስብ።” ብሎ ሌላ የሀሳብ መስኮት ከፈተልኝ።
የእሱን ወሬ እና ምክር ይዤ ያለንበትን ሁኔታ ማውጣት ማውረድ ጀመርኩ። ግን ለምን እንደዚህ እንሆናለን? ያሉንን መልካም ነገሮች እንዳንቋደስ ማን አዚም አደረገብን?
እሺ ከዚያ በኋላስ?
‘የአስተማሪ ምግብ…’
የወዳጅን ሞት ሰምቼ ስባዝን…
